“ሰው ፍሬ ማሳየት አለበት፤ ፍሬ የማይሰጥ ሰው በብጹኡ መንፈስ (ክርስቶስ) ቃላት ፍሬ እንደሌለው ዛፍ ነው፤ ፍሬ የሌለው ዛፍ ለእሳት ይገባል።” (ባሃኦላህ በወርድስ ኦፍ ፓራዳይስ)
ኽርበርት ስፔንሰር አንድ ጊዜ፥ በምንም ዓይነት ቅመም ከእርሳስ ባሕርይ ወርቅ ጠባይ ለማግኘት አይቻልም። እንዲሁም በምንም የፓለቲካ ቅመም እያንዳንዱን የእርሳስነት ባሕርይ ያለውን ግለሰብ ወደ ወርቅ ኅብረተሰብ መለወጥ አስቸጋሪ ነው ሲል ተናግሯል። ባሃኦላህም እንደሁሉም ቀደምት ነቢያት ይህንኑ እውነት በማወጅ የእግዚአብሔን መንግሥት በዓለም ላይ ለመመሥረት በቅድሚያ በሰዎች ልብ መመሥረት እንዳለበት አስተምሯል። ስለዚህ የባሃኦላህን ትምህርቶች ስንመራመር ባሃኦላህ ስለእያንዳንዱ ጠባይ በሰጠው መመሪያ በመጀመር ባሃኢ መሆን ምን እንደሆነ በግልጽ ለማስረዳት እንሞክራለን።
ኑሮውን መኖር
አንድ ጊዜ ‘ባሃኢ ምንድነው?’ ተብሎ ሲጠየቅ አብዱል-ባሃ እንዲህ ሲል መለሰ፦ ‘ባሃኢ በቀላሉ ዓለምን በሙሉ መውደድ ማለት ነው፥ ሰውን መውደድና ለማገልገል መሞከር፥ ለዓለም ሰላምና ለዓለም ወንድማማችነት መሥራት ማለትም ነው።’ ሌላ ጊዜ ደግሞ ባሃኢን ሲገልጽ ‘አንድ በማንኛውም ሰብዓዊ ሥራው ምንም ዓይነት ጉድለት የሌለበት ሰው ማለት ነው።’ ሎንዶን ባደረጋቸው ንግግሮቹ ውስጥ አንዴ፣ ምንም እንኳን አንድ ሰው ስለ ባሃኦላህ ባይሰማም ባሃኢ ሊሆን ይችላል፤ሲል ተናግሯል።
ከዚህም በመቀጠል፦
“ማንም ሰው በባሃኦላህ ትምህርት መሠረት የሚኖር በቅድሚያ ባሃኢ ነው። በአንድ በኩል ደግሞ አንድ ሰው ለሃምሣ ዓመት ባሃኢ ነኝ ብሎ ብቻ ኑሮውን ባይኖር እርሱ ባሃኢ አይደለም። መልከ ጥፉ ሰው እራሱን መልከ መልካም ነኝ ይል ይሆናል። ግን ማንንም አያታልልም፤ እንዲሁም አንድ ጥቁር ሰው ነጭ ነኝ ቢል ማንንም አያታልልም፥ እራሱንም እንኳን ቢሆን።” (አብዱል-ባሃ ኢን ሎንዶን ገጽ 109)
ሆኖም፥ አንድ የእግዚአብሔርን መልእክተኛ የማያውቅ ሰው በጥላ ውስጥ እንደሚያድግ ተክል ነው። ፀሐይን ምንም እንኳ ባያውቅ እድገቱ በፍጹም በፀሐይ ላይ የተመሠረተ ነው። ታላላቆቹ ነቢያት የመንፈስ ፀሐዮች ናቸው። ባሃኦላህም የዚህ እኛ የምንኖርበት ዘመን ፀሐይ ነው። በቀደምት የነበሩት ፀሐዮች ዓለምን አሙቀዋል ሕይወትም ሰጥተዋል። እነዚያ ፀሐዮች ባይወጡ ኖሮ መሬት ይሄኔ ቀቃዛና በድን ነበረች፤ ግን በቀደምት ፀሐዮች ሕይወት የተሰጣቸው ፍሬዎች ሊበስሉ የሚችሉት በአሁኑ የፀሐይ ብርሃን ብቻ ነው።
READ MORE: http://www.bahai.org/