ባሃኡላህ ከጥንት ጀምሮ እንደሚመጣ ይጠበቅ የነበረው መለኮታዊ መምህር ነው። ወንዞች በውቅያኖሶች ውስጥ እንደሚዋሐዱ ሁሉ ከአሁን በፊት ለነበሩት ሃይማኖቶችም አዋሐጅ መሆኑን ደጋግሞ በግልጽ አስታውቋል።
በዓለማችን በሚገኙ በሺዎች በሚቆጠሩ ቦታዎች፣ ግለሰቦችና ማህበረሰቦች የራሳቸውን ህይወት ለማሻሻልና ለሰው ልጅ ስልጣኔ መራመድ አስተዋጽኦ ሲያደርጉ ከባሃኢ እምነት ትምህርቶች መነቃቃትን ያገኛሉ፡፡ የአምላክና የሃይማኖት አንድነት፣ የሰው ዘር አንድነት እና ከከንቱ ጥላቻ መላቀቅ፣ በአምላክ የተቸረው የሰው ልጅ ክቡርነት፣ የሃይማኖት እውነት እያደገ በሚሄድ መልኩ መገለጽ፣ መንፈሳዊ ባህሪያትን ማሳደግ፣ የአምልኮና ለሰው ዘር የሚሰጥ ግልጋሎት ጥምረት፣ የወንድና የሴት መሰረታዊ እኩልነት፣ የሃይማኖትና የሳይንስን ስምምነት፣ በሰው ልጆች ጥረቶች ሁሉ የፍትህን አስፈላጊነት፣ የትምህርትን ጠቀሜታ፣ የሰው ዘር ወደ ጋራ የብስለት ደረጃው ሲገሰግስ፣ የግለሰቦች፣ ማህበረሰቦችና ተቋማትን የእርስ በእርስ ግንኙነት ተለዋዋጭ መስተጋብርን የመሰሳሉ ዋና ዋና መልዕክቶች በባሃኢ እምነት ትምህርቶች የተካተቱ ናቸው፡፡
በመጠኑና በዓላማው ወደር የሌለው መልእክቱ በሚያስገርም አኳኋን ከዘመኑ ምልክትና ፍላጎት ጋር የተስማማ ነው። የሰው ልጅ እንደአሁኑ ጊዜ እጅግ የጎሉና የተወሳሰቡ ችግሮች ከዚህ በፊት ከቶ አልገጠሙትም። ለእነዚህ ችግሮች እንደ መፍትሄ የቀረቡት አስተያየቶች ደግሞ እንደዚህ የበዙና እርስ በእርስ የሚጣረሱ ሆነው አያውቁም። የአንድ ታላቅ የዓለም መምህር አስፈላጊነት እንደዚህ ጊዜ ኃይሎ አያውቅም። ምናልባትም ይህን የመሰለው መምህር የመምጣት ምኞት እንደዚህ እጅግ በርትቶ አያውቅም።
ስለትንቢቶች መፈጸም
የማየት ኃይል ያላቸው ሁሉ ፀሐይ ለራሷ ምስክር መሆኗን ይረዳሉ። ፀሐይ በወጣች ጊዜ ብርሃን እና ሙቀት ትሰጣለች የሚል ጥንታዊ ማረጋገጫ አያስፈልጋትም። የእግዚአብሔር መልእክተኛም መገለጽ እንደዚሁ ነው። ጥንታዊ ትንቢቶች ሁሉ ጠፍተው ቢሆን እንኳን መንፈሳዊ ስሜታቸው ንቁ ለሆኑት ሁሉ የእግዜብሔር ቅዱሳን ነቢያት ለነቢይነታቸው ማንነታቸው ራሱ የላቀ ማስረጃ ይሆናል። ሆኖም የነቢይነት መለዮዎችን ሁሉ ሳንመረምር በጭፍን መቀበልን ባሃኡላህ አላዘዘም። እንዲያውም ሰዎች ትምህርቱን ሳይመረምሩና እውነተኛነቱን ሳይረዱ በጭፍን እንዳይቀበሉት በጥብቅ ከማስገንዘቡም በላይ እያንዳንዱ ሰው እውነቱን አጣርቶ ለማወቅ እንዲችል፤ ጆሮዎቹን እንዲከፍትና ያለፍርሃት በነፃነት እንዲያመዛዘን ሲል ይህን ትእዛዝ በቀዳሚነት አስፍሮት ይገኛል። መርምሮ መረዳትን የእያንዳንዱ ሰው ግዴታ ከማድረጉም በላይ፣ የነብዩ ዋና ማስረጃ እርሱ ራሱ የሰውን ልጅ ባሕርይና ኑሮ የመለወጥ ኃይል ያለውቃሉና ሥራው መሆኑንን አልሸሸገም።
ባሃኡላህ ለነብይነቱ ማስረጃ እንዲሆኑ ሲል የሰጣቸው ምልክቶች ከሱ በፊት የነበሩት ታላላቅ ቀደምት ነቢያት ከሰጡዋቸው ማስረጃዎች ጋር አንድ ናቸው።
ለምሳሌ ሙሴ እንዲህ ሲል ጽፏል፦
“እግዚአብሔር ያልተናገረውን ቃል እናውቅ ዘንድ እንዴት ይቻለናል? ብትል፤ ነብዩ በእግዚአብሔር ስም በተናገረ ጊዜ የተናገረው ነገር ባይሆን፣ ባይመጣም ያ ነገር እግዚአብሔር ያልተናገረው ነው፣ ነብዩ በድፍረት ተናግሮታል፤ እርሱን አትፍራው፡፡ ” (ኦሪት ዘዳ. 18፡ 22)
ክርስቶስም እንዲህ ሲል ጽፏል፥
“የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውሥጣቸው ገን ነጣቂዎች ተኩላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ፡፡ ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ፡፡ ከእሾህ ወይን ከኩርንችትስ በለስ ይለቀማልን? እንዲሁ መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያደርጋል፣ ክፉ ዛፍም ክፉ ፍሬ ያደርጋል፡፡ መልካም ዛፍ ክፉ ፍሬ ማፍራት ወይም ክፉ ዛፍ መልካም ፍሬ ማፍራት አይቻለውም፡፡ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል፣ ወደ እሳትም ይጣላል፡፡ ስለዚህም ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ፡፡” (ማቴዎስ 7፡15-20)
ነገርግን በየዘመኑ የተገለጹት የእግዜብሔር ክስተቶች ምንም እንኳን የሰውን ዘር እንደ አዲስ ለመፍጠር አቅም ያላቸውን ለዋጭ ቃሎች ቢገልጹም፣ በኑሮዋቸውም መልካም ፍሬን ቢያፈሩም እንዳንቀበላቸው ያደረገን ምንድን ነው?
አብዱል-ባሃ እንዲህ ሲል ጽፏል፦
“በወንጌል እንደተጻፈው ክርስቶስ ከሃያ ምዕተዓመት በፊት በተገለጸ ጊዜ ምንም እንኳን አይሁዶች እያለቀሱ ‘አምላክ ሆይ የመሢህን መምጣት አፋጥንልን’ እያሉ በየዕለቱ ሲጸልዩ የነበሩ መሆናቸው ቢታወቅም፣ የእውነቱ ፀሐይ በመጣ ጊዜ ጠንካራ ጠላቶች ሆነው ተነሱበት፣ በመጨረሻውም ክፉው ብኤልዜቡብ በሚል መታወቂያ ጠርተውት፣ ያን መለኮታዊ መንፈስ፤ ያን የአምላክን ቃል ሰቀሉት። አይሁዶች እንደሚሉት ክርስቶስን የሰቀሉበት ምክንያት እንደሚከተለው ነው፦ በኦሪት መጻሕፍት ትርጉም መሠረት የክርስቶስን መገለጽ አንዳንድ ምልክቶች ሊፈጸሙ ይገባል፤ እነዚህ ምልክቶች ሳይፈጸሙ እኔ መሲህ ነኝ የሚል ሁሉ አታላይ ነው። ከምልክቶቹም አንዱ መሲህ ካልታወቀ ቦታ ይመጣል የሚል ሲሆን፣ ይህ ሰው ከናዝሬት መምጣቱን ሁላችንም እናውቃለን። ‹ከናዝሬት ደግሞ መልካም ነገር ሊመጣ ይችላልን?› ሌላኛው ምልክት ደግሞ በኃይልና በሥልጣን፤ ማለትም በሠይፍ ይገዛል የሚል ሲሆን ይህ መሢህ በትር እንኳን አልነበረውም። ከሌሎች ምልክቶችና መለያዎቹ አንዱ ደግሞ በዳዊት ዙፋን ላይ ተቀምጦ የዳዊትን መንግሥት ያጸናል የሚል ነው። ይህ ሰው እንኳንስ በዳዊት ዙፋን ላይ ሊቀመጥና የሚያርፍበት ምንጣፍ እንኳን አልነበረውም። ሌላው ምልክት ደግሞ የእግዚአብሔር መሢህ መጥቶ የኦሪትን ሕግ ያጸናል የሚለው ነበር። ነቢይም ቢሆንና ብርቱ ተአምራትም ቢሠራ የቀዳሚትን ቀን ከሻረ ለሞት የተገባ ነው ተብሎ ይታመን ነበር። ይህ ሰው ግን በድፍረት በኦሪት ያለውን ቃል የቀዳሚትን ቀን ሻረ። ሌላው ምልክት ደግሞ በዚህ ሰው ዘመነ መንግሥት ርትዕ ከልክ አልፎ ከመብዛቱ የተነሣ በጎ አድራጎት ከሰዎች ተርፎ ወደ እንስሳትም ስለሚያልፍ እባብና አይጥ አንድ ጉድጓድ ይጋራሉ። ንስርና ድርጭት ባንድ ጎጆ ይተኛሉ። አንበሳና ድኩላ ባንድ ሜዳ ይሰማራሉ። ተኩላና የፍየል ግልገል ከአንድ ምንጭ ይጠጣሉ የሚለው ሲሆን በሱ ዘመን ፍርድ በመጉደሉና ጭካኔ ከመብዛቱ የተነሣ እሱን እራሱንም ሰቀሉት! ሌላው ምልክት ደግሞ አይሁዶች ይበለጽጋሉ፤ የዓለምን ሕዝቦች ሁሉ ድል ይነሣሉ የሚለው ሲሆን በእሱ ዘመን ግን እጅግ በተዋረደ ሁኔታና በሮም ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ባርነት ሥር ይኖሩ ነበር። ስለዚህ በኦሪት እንደተሰጠው ተስፋ ይህ መሢህ ነው ለማለት ይቻላልን?
“ምንም እንኳን በኦሪት የተሰጠው ተስፋ ለዚህ ለእግዚአብሔር መንፈስ ቢሆንም በዚህ ዓይነት መንገድ የእውነትን ፀሐይ ካዱት። የእነዚህ ምልክቶች ሚስጢር ስላልገባቸው አይሁዶች የእግዚአብሔርን ቃል ሰቀሉት። የኦሪት ቃል የተነገረው በምሳሌ ስለሆነ አይሁዶች በገመቱት መንገድ ሳይሆን በክርስቶስ መገለጽ ምልክቶች ሁሉ ተፈጽመዋል ሲሉ ባሃኢዎች ያምናሉ። ለምሳሌ ከምልክቶቹ አንዱ ንጉሥነት ስለሆነ የክርስቶስን ንጉሥነት ለጥቂት ጊዜ ደምቆ እንደትቢያ በኖ እንደሚጠፋው እንደናፖሊዎን ያለ ንጉሥነት ሳይሆን ዘለዓለማዊና ሰማያዊ መንግሥት በመሆኑ ይህ ምልክት ተፈጽሟል ሲሉ ባሃኢዎች ያምናሉ። የክርስቶስ መንግሥት ከተጀመረ ሁለት ሺ ዓመት ሆኗል። እንዲያውም ዓለም ሳይፈጠር የነበረና እስከ ዛሬ ድረስም በመንግሥቱ ላይ ያለ እስከ ዘለዓለምም ከዙፋኑ የሚቀመጥ ቅዱስ ስሙም ለዘለዓለም የሚኖር ነው። በዚሁ መንገድ ሌሎቹ ምልክቶችም ሁሉ ተፈጽመዋል። ነገር ግን አይሁዶች ምሥጢሩ አልገባቸውም። ምንም እንኳ ክርስቶስ መለኮታዊ ግርማን ተጎናጽፎ ወደዚህ ዓለም ከመጣ ሁለት ሺህ ዓመታት ያህል ቢያልፍም አይሁዶች የመሢህን መምጣት እስካሁን በመጠባበቅ ላይ በመሆናቸው ራሳቸውን እውነተኛ፤ ክርስቶስን ሃሰተኛ አድርገው ይገምታሉ።” አብዱል-ባሃ
አይሁዶች ክርስቶስን ጠይቀውት ቢሆን ኖሮ ስለራሱ የተጻፈውን ትንቢት ሚስጢር ባስረዳቸው ነበር። ታሪክ እንደሚያስረዳን የአምላክ ከስተቶች በተገለጹበት ወቅት በዙሪያቸው በነበሩ ሕዝቦች ከህደት፣ እምቢታና ከባድ ተቃውሞ ደርሶባቸዋል። ነገር ግን የሰውን ዘር እንደአዲስ የሚፈጥሩ ቃላቶቻቸው ለምእተ አመታት ዘልቀው ይሄዳሉ። ባሃኡላህ በዚህ ጉዳይ እንድናሰላስል እንዲህ በማለት ይመክራናል፡- "አንድ ጊዜ አሰላስል፥ ለእነዚያ ያንን በሚያህል ቅንነትና ናፍቆት ሲመራመሩ ለነበሩት የዚህ ዓይነቱ ክህደት ምን እንደነበረ ለመረዳት በጥልቀት አብሰልስል። ያደረሱት ጥቃት አንደበት ወይም ብዕር ሊገልጸው ከሚችለው በላይ የከፋ ነበር።"
ሁሉም የአምላክ ክስተቶች በተገለጹበት ጊዜ ከፍተኛ ተቃውሞ፣ እንግልት እና መከራ ገጥሟቸዋል። ባሃኡላህ ራሱ ለ40 ዓመታት የእስር፣ የመከራና የስደት ሕይወትን አሳልፏል።
የባሃኡላህ ውልደትና የወጣትነቱ ዘመን
ሚርዛ ሁሴን ዓሊ በመባል ስም ይታወቅ የነበረው ባሃኡላህ እ.ኤ.አ በ1817 በፋርስ (ኢራን) ዋና ከተማ በቴህራን ተወለደ። አባቱ ሚርዛ ቡዝሩግ የፋርሱ ንጉስ ከፍተኛ ባለስልጣንና ታዋቂ መኮንን ነበሩ። ባሃኡላህ ገና በህፃንነቱ የታላቅነት ምልክቶች ይታዩበት የነበረ ሲሆን፣ እጅግ የሚያስደንቅ ዓይነት እውቀትና ጥበብም ነበረው። እርሱም መደበኛ ትምህርት ቤት ገብቶ አያውቅም። ነገር ግን እቤት ውስጥ እንደ ማንበብ፣ መጻፍና ፈረስ ግልቢያ የመሳሰሉ መሰረታዊ ትምህርቶች በጥቂቱ ተሰጥቶታል። ነገር ግን ገና ከልጅነቱ ታላቅ ጥበብና ዕውቀት ይታይበት ነበር። ገና ወጣት ሳለ አባቱ ስላረፈ የታናሽ ወንድሞቹና እህቶቹ ጥበቃና ሰፊው የቤተሰብ ንብረት አስተዳደር በርሱ ትከሻ ላይ ወደቀ። አብዱል-ባሃ እንዲህ አለ፦
“ከልጅነቱ ጀምሮ እጅግ በጣም ደግና ለጋስ ነበር። አብዛኛውን ጊዜውን በየመስኩና በአትክልት ሥፍራ ማሳለፍ ይወድ ነበር። የሚሰማውን ሁሉ ወደርሱ በጣም የመሳብ ኃይል ነበረው። ሁልጊዜ ብዙ ሰዎች ወደርሱ ይሰበሰቡ ነበር። ሚኒስትሮችና የአደባባይ ሰዎች ይከቡት፣ ሕፃናትም በጣም ይወዱት ነበር"።
ገና የአሥራ ሦስትና የአሥራ አራት ዓመት ወጣት ሳለ በዕውቀቱ ምክንያት ዝናው የገነነ ነበር። በማንኛውም ጉዳይ ላይ የመነጋገርና ለቀረበለት ለማንኛውም ጥያቄ መልስ የመስጠት ችሎታ ነበረው። በትልልቅ ስብሰባዎች ላይ ከኡላማዎች (የእስላምና ሃይማኖት ሊቃውንት) ጋር እየተነጋገረ ብዙ የተወሳሰቡ ሃይማኖት ነክ የሆኑ ጥያቄዎችን ያብራራላቸው ስለነበረ ሁሉም በታላቅ አድናቆት ያዳምጡት ነበር።
“ባሃኡላህ ሃያ ሁለት ዓመት ሲሆነው አባቱ ስላረፉ፣ ምንም እንኳን በዚያን ጊዜ በኢራን እንደተለመደው መንግሥት የአባቱን ቦታ ቢሰጠውም ባሃኡላህ ሹመቱን አልተቀበለም። ይህን በሰማ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደዚህ አለ። ‘ተውት! ይህ ማዕረግ ለእርሱ ያነሰ ነው። ከዚህ የበለጠ ታላቅ ዓላማ አለው። ምንም እንኳን አሁን ልረዳው ባልችል ከዚህ እጅግ በጣም ከፍ ላለ ሥራ የታጨ ለመሆኑ እርግጠኛ ነኝ። ሃሣቡ ከኛ የተለየ ነውና ተውት!’”
ለባሃኡላህ ግልጸት ሰዎችን ሲያዘጋጅ የነበረው እና እራሱም የእግዚብሔር ግልፀት የሆነው ባብ
እ.ኤ.አ. በ1844 በፋርስ፣ ሺራዝ በምትባል ከተማ ውስጥ ባብ የሚባል የእግዚአብሔር መልዕክተኛ የአዲስ መለኮታዊ የግልፀት ዘመን መልእክቱን ሲያውጅ ባሃኡላህ የሃያ ሰባት ዓመት ጎልማሳ ነበር። ያ ታሪካዊ ክንውን ሦስት ወራት እንኳን ሳይሆነው ባሃኡላህ ከባብ አንዳንድ ጽሁፎች የያዘ የብራና ጥቅል ደረሰው። ስለ ባብ ግልፀት እውነትኛነት ወዲያው መሰከረ፥ ትምህርቶቹንም ለማራመድ ተነሳ። ያለፍርሃት በድፍረት ይህን ባብ የገለፀውን ትምህርት ተቀብለው ከነበሩት ምዕመናን ጋር እንደ አንዱ ሆኖ አዲሱን ሃይማኖት በቆራጥነት ማስፋፋት ጀመረ።
ባብ ከሱ ቀጥሎ ለሚመጣው የእግዜብሔር ክስተት(ለባሃኡላህ) የሰዎችን ልብ ያዘጋጅ ነበር። ባሃኡላህን "እርሱ አምላክ የሚከስተው" በማለት ይገልፀው ነበር። ባብ ተከታዮቹን ለታላቁ የባሃኡላህ ግልፀት እንዲህ በማለት ያዘጋጃቸው ነበር "ገነት ማለት እርሱ አምላክ የሚከስተውን ማወቅና ራስን ለእርሱ ማስገዛት መሆኑን በእርግጥ እወቁ"። በተጨማሪም "ምናልባትም እርሱ አምላክ የሚከስተው ዘንድ መቅረብን ትቀዳጅ ዘንድ፣ አምላክን ከማውሳት በስተቀር ምንም እንዳትሰማ ጆሮህን አፅዳ፣ ከአምላክም በስተቀር ምንም እንዳያዩ ዓይኖችህን እንፃ፣ እንዲሁም ሕሊናህ ከአምላክ ሌላ እንዳያስተውል፣ ልሳንህም አምላክን እንጂ ሌላ እንዳያውጅ፣ በእጅህ ከአምላክ ቃላት በስተቀር ሌላ ምንም እንዳይፅፍ፣ እውቀትህም ከአምላክ በስተቀር ምንም እንዳይገነዘብ፣ ልብህም ከአምላክ በስተቀር ምንም ሌላ ምኞት አያስተናግድ... " በማለት ተናግሯል።
የባብ አስተምህሮት በፍጥነት በመዛመቱ እና ታዋቂነት በማግኘቱ በፋርስ ባላስልጣናት እና የሀይማኖት መሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጠመው። በዚሁም ምክንያት ባሃኡላህ የባብ ተከታይ እንደመሆኑ መጠን ሁለት ጊዜ በእሥራት ከመቀጣቱም በላይ አንድ ጊዜ የውስጥ እግሩን በመገረፍ ስቃይ ደርሶበታል። በተጨማሪም ከ 20,000 በላይ የሚሆኑት የባብ ተከታዮቹ በተከታታይ በተደረጉ የጅምላ ግድያዎች ህይወታቸውን እንዲያጡ ተደረገ። ባብ እራሱ እ.ኤ.አ በ1850 ታቢሪዝ በሚባል ከተማ በህዝብ ፊት መስዋዕት ሆነ።
የባሃኡላህ ግልፀት
እ.ኤ.አ በ1852 ባሃኡላህና ሌሎች የባብ ተከታዮች “ሲያህ ቻል” ትርጉሙም “ጥቁር ጉርጓድ” በሚባል ቴህራን ከተማ ውስጥ በሚገኝ እስር ቤት ውስጥ በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲቆዩ ተደረግ። የባሃኡላህ እግሮች በእግረ ሙቅ ተጠፈሩ፡ ሃምሳ ኪሎግራም የሚመዝን ከባድ ሠንሠለት በአንገቱ ዙሩያ ተንጠለጠለበት። ከዚህም በተጨማሪ የእስር ቤቱ ጥበትና የመቆሸሹ ሁኔታ በጣም የከፋ ነበር። ነገር ግን እንዲህ ባለ አሰቃቂ ሁኔታ በእስር ቢቆዩም ከፍ ያለ የመንፈስ ብርታትና ደስታ ነበራቸው። “እግዜብሔር ለእኔ አርኪዬ ነው፡ እርሱ በእውነቱ ሁሉን የሚያረካው ነው። የሚተማመኑ በእርሱ ይተማመኑ” በማለት ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ ደስታ በተሞላው ሕብረ ዝማሬ ከእስር ቤቱ ሆነው ይዘምሩ ነበር።
በየቀኑ አንድ ወይም ከዚያ በላይ ሰዎች ከመሃከላቸው ተወስደው ይሰቃያሉ ወይም ይገደላሉ። የተቀሩት ደግሞ ቀጥሎ የእነሱ ተራ መሆኑ ይታወሳቸዋል። ከመካከላቸው አንዱ ሊገደል ስሙ ሲጠራ በደስታ ወቶ የመስዋዕትነትን ጽዋ ይቀበላል።
በዚህ እስር ቤት አምላክ ለባሃኡላህ የእርሱን (የባሃኡላህን) ታላቅ ደራጃ ገለፀለት። ሽታው እጅግ አስከፊ በሆነ እስር ቤት፣ እግሮቹ በእግረ ሙቅ ታስረው፣ አንገቱም በክብደቱ እጅግ ከፍተኛ በሆነ ሠንሠለት ጎብጦ ሳለ የመላውን ፍጥረት አንቀሳቃሽ የሆነውን የአምላክን ግልፀት በነፍሱ ተቀበለ። በመሆኑም ከጥቁሩ ጉድጓድ በስተጀርባ የእውነት ፀሐይ ነጋ። የባብ ትንቢት ተፈፀመ። የባሃኢ ግልፀት ተወለደ። በዚህ ጊዜ ባሃኡላህ ተልኮውን ለማንም አላሳወቀም፥ በአምላክ የታዘዘውን፣ የተወሰነውን ሰዓት ይጠብቅ ነበር።
በዚህ ወቅት ጠላቶቹ ክንጉሱ ዘንድ የሞት ፍርድ ሊያስፈርዱበት በመሯሯጥ ተጠምደው ነበር። ነገር ግን የሱን ወንጀለኛነት ማረጋገጥ ሳይችሉ ቀሩ። በስተመጨረሻም ባለሰልጣናቱ እርሱን ነፃ አድርጎ ከመልቀቅ ሌላ አማራጭ አልነበራቸውም። ይህንን ለማድረግ የተስማሙት ግን ባሃኡላህ ከተለቀቀ በኋላ ሃገሩን (ኢራንን) ለቅቆ እንዲሄድ በማድረግ ነበር። ባሃኡላህም በዛን ወቅት በኦቶማን ግዛት ሥር የነበረችው አሁን የኢራቅ ዋና ከተማ ወደሆነችው ወደ ባግዳድ ተሰደደ።
ባግዳድ
ባሃኡላህ በባግዳድ ቆይታው ብዛት ያላቸው የባብ ተከታዮች ሊጎበኙት ይመጡ ነበር። ባሃኡላህም ሁሉንም ወሰን በሌለው ፍቅር እንዲሁም መንፈሳቸውን በማነቃቃት ይረዳቸው ነበር። ባሃኡላህ በባብ ተከታዮች ዘንድ ያለው ክብር እና ፍቅር እያደር እየጨመረ መጣ። ምንም እንኳን ባሃኡላህ በባብ ቃል የተገባለት መሆኑን ባይገልፅላቸውም ቀናት ባለፉ ቁጥር ታላቅነቱ ይበልጥ ግልፅ እየሆነ በመምጣቱ ጥቂቶች ደረጃውን መረዳት ጀምረው ነበር። እርሱ ፊት የቀረበ እያንዳንዱ ሰው በጥዑምና አፍቃሪ ቃላቶቹ ኃይል ይለወጥ ነበር። መለኮታዊ ፍቅር ከእርሱ በመጉረፉ ምክንያት ያልተነኩ ንፁህ ልቦች አልነበሩም። በጽሑፎቹ እና በፅላቶቹ ለብዙ ጊዜያት ያለእረኛ ሲባዝኑ የነበሩትን የባብ ተከታዮች ሁኔታ ለወጠው።
ባሃኡላህ ባግዳድ በቆየባቸ አመታት እያደገ የሄደው የእርሱ ዝና በአገሪቷ ለነበሩ ከፍተኛ የሐይማኖት መሪዎች አሳሳቢ ጉዳይ ሆነ። አንድ ሼይክ የፋርስ እና የኦቶማን መንግሥታት እንዲሁም ካህናት እንዲነሱበት ለማሳመን ያልፈነቀለው ድንጋይ አልነበረም። በመጨረሻም ተደጋጋሚ ጥረቱ ፍሬ አፍርቶ እ. ኤ. አ. ፀደይ ወቅት በ1863 ባሃኡላህ ከባግዳድ ወደ ቁስጥንጥኒያ (የአሁኗ ኢስታንቡል) እንዲጋዝ ትእዛዝ መጣ። የባሃኡላህ ከባግዳድ የመጋዙ ዜና አማኞቹ በሐዘን እንዲዋጡ አደረገ።
እ. ኤ. አ ኤፕሪል 22 ቀን 1863 አማኞችና ብዛት ያላቸው የባግዳድ ነዋሪዎች ተሰብስበው በነበሩበት የሪዝቫን አትክልት ስፍራ በመባል በሚታወቀው ቦታ እውነተኛ ማንነቱን፥ በሁሉም ዘመናት ቃል የተገባለት እርሱ መሆኑን በግልፅ አወጀ። ተልዕኮውን ማወጁ በተወዳጆቹ ነፍስ ውስጥ አዲስ ሕይወትን ፈጠረ። ባብ ያዘጋጃቸው ለዚህ የቀናት ሁሉ ቀን ለሆነው ነበር። የባሃኡላህ ግልፀት እና ተልዕኮውን አስመልክቶ በየዓመቱ በዓለም ዙሪያ ሪዝቫን በሚል ክብረ በዓል ይከበራል። ይህ ዓመት በዓል የተቀደሰ እና ከባሃኢ በዓላት እጅግ ታላቁ እና ዋነኛው ሲሆን በባሃኡላህም ‹‹ የበዓላትም ንጉስ›› ተብሎ ተሰይሟል።
ከዚያም በባግዳድ የሚኖሩ ሰዎች እና አማኞች መንገደኛውን እስረኛ በአክብሮት ሊሰናበቱ መጡ።
ቁስጥንጥኒያ
ባሃኡላህ ቤተሰቡ እና አብረዋቸው የነበሩት ጥቂት አማኞች በቁስጥንጥያ ለአራት ወራት ብቻ ቆዩ። በርቀት ያለው የፋርስ መንግስት እያደገ የመጣውን የእርሱን (የባሃኡላህን) ተፅዕኖ ፈጣሪነት እንደስጋት መቁጠሩን አላቋረጠም። በኦቶማን ሥርወ መስግስት ውስጥ የሡልጣኑ ችሎት የፋርስ አምባሳደር የሆነው፣ በባሃኡላህ ላይ ሰልታዊ ዘመቻ ማድረጉን እየቀጠለበት መጣ። በመጨረሻም ባሃኡላህ ከፋርስ ድንበር በጣም ወደራቀችው አድሪያኖፕል እንዲጋዝ ትዕዛዝ ወጣ።
አድሪያኖፕል
አሁን ለሶስተኛ ጊዜ የተጋዘበት ከቁስጥንጥኒያ እስከ አድሪያኖፕል የተደረገው የአስራሁለት ቀናት ጉዞ ለባሃኡላህ እና ለቤተሰቦቹና እስካሁን ድረስ ከአደረጉት ጉዞ ሁሉ በጣም አስቸጋሪው ነበር። ወሩ ታሀሳስ እንደመሆኑ መጠን የዓየር ንብረቱ እጅግ አስመራሪ ቀዝቃዛ ክረምት ነበር። የከፋ ቅዝቃዜውን ለመከላከል አብዛኞቹ ስደተኞች አስፈላጊውን ልብስ እንኳ አልነበራቸውም። ባሃኡላህ እ. ኤ. አ ዲሴምበር 12 ቀን 1863 አድርያኖፕል ከተማ ደረሰ። በዚያች ከተማ አራት አመት ከመንፈቅ ተቀመጠ። ባሃኡላህ ለነገስታት እና ለዓለም መሪዎች ብዙዎቹን ፅላቶች የላከው እና የእርሱን ሃይማኖት በቅርብም በሩቅም ያወጀው ከዚህች ከተማ ነበር። ነገር ግን እንደገና ከአድሪያኖፕል እንዲወጡ ታዘዘ። ባሃኡላህም እ. ኤ. አ ኦገስት 12 ቀን 1868 አድሪያኖፕልን ለቀው በመሬትና በባህር ላይ አስቸጋሪ የሆነ ጉዞ ካደረጉ በኋላ ኦገስት 31 ቀን አቆር ( የአሁኗ እስራኤል ውስጥ ያለች ከተማ) ደረሱ።
አቆር (አካ)
ለአቆር ነዋሪዎች የእስረኞች መምጣት እንግዳ ነገር አልነበረም፥ ምክንያቱም ኦቶማኖች ከተማይቱን ወንጀለኞችን ለማጋዝ ይጠቀሙበት ስለነበር ነው። አሁን የመጡት እስረኞች የመንግሥት፣ የእግዜአብሔር እና የሃይማኖት ጠላቶች ናቸው ተብሎ ተነገራቸው። የአቆር አስከፊ ሁኔታም እስከመጨረሻው እንደሚያጠፋቸው ተገምቶ ነበር።
ምንም እንኳ የእስሩ ሁኔታ ቀስ በቀስ እየተሻሻለ ቢመጣም በአቆር የኖሩባቸው የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ለባሃኡላህ አስከፊ የስቃይ ወቅት ነበሩ። ጽኑ እሥራታቸው ለሁለት ዓመት በቆየበት በዚህ ጊዜ፥ እየተጠበቁ በየቀኑ ምግብ ለመግዛት ከሚሄዱት ከአራት ባሃኢዎች በስተቀር ሌሎቹ ከእሥር ቤት ደጃፍ እንዲወጡ አይፈቀድላቸውም ነበር። በመጨረሻ የቱርክ ወታደሮች ንቅናቄ ስለተደረገ እነርሱ የታሰሩበት ሠፈር ለወታደሮች ተፈለገ። ባሃኡላህና ቤተሰቦቹ ለብቻቸው ወደ አንድ ቤት ሲዛወሩ የተቀሩት እስረኞች ከተማው ውስጥ በሚገኘው ወደ አንድ የመንገደኞች መጠለያ ተወሰዱ። ባሃኡላህ በዚያች ቤት ውስጥ ለሰባት ዓመታት በእስረኝነት ቆየ። ባሃኡላህና ተከታዮቹ የወታደሮቹን ሠፈር እንዲለቁ ከተደረጉበት ጊዜ ጀምሮ ጠያቂዎች እንዲጎበኙአቸው ተፈቀደ። በመንግሥቱም የተፈረደው ጽኑ ቁጥጥር ምንም እንኳን አልፎ አልፎ ቢጠብቅም ቀስ በቀስ እየተሻሻለላቸው ሄደ።
ጊዜ እያለፈ ሲሄድ የአቆር ህዝብ ከፋርስ የመጡት ጥቂት ግዞተኞች፣ ወንጀለኞች እንዳልሆኑ መገንዘብ ጀመሩ። በዚህ ጊዜ የአቆር ብቻ ሳይሆን በቅርብ የሚገኙት የሶሪያ እና የሊባኖስ ሕዝቦች ስለ ባሃኡላህ እና ተከታዮቹ የነበራቸው አስተሳሰብ ፈጽሞ ተለውጦ ነበር። ምንም እንኳን የሡልጣኑ ትእዛዝ ገና ያልተሻረ የነበረ እና በቁጥጥር ሥር የዋለ እስረኛ የነበረ ቢሆንም እንደ እውነቱ ከሆነ ግን እንደ ንጉሥ በጥልቅ የተከበረ ነበር። የአካባቢው ባለሥልጣኖች እንኳን ምክሩን በመሻት ወደ እርሱ ይመጡ ነበር።
እሥራቱ በጠናበት ወቅት ባሃኢዎች ተስፋ አልቆረጡም ነበር። ጽኑ እምነታቸውም አልተናወጠም። አቆር በሚገኘው የወታደሮች መኖሪያ ውስጥ በነበረ ጊዜ ባሃኡላህ ለአንዳንድ ምዕመናን እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “አትፍሩ፥ እነዚህ በሮች ይከፈታሉ። ድንኳኔም በቀርሜሎስ ተራራ ላይ ይተከላል። ፍጹም ደስታም ይሆናል።” ይህ አዋጅ ለተከታዮቹ በጣም ትልቅ መጽናኛ ነበር። ጊዜውም ሲደርስ ትንቢቱ ቃል በቃል ተፈጸመ። ምንም እንኳ የባሃኡላህ ተከታታይ ግዞቶች በሙስና ከዘቀጡ የሃይማኖት መሪዎች ጋር በመተባበር በሁለቱ ምድራዊ ባለሥልጣናት ትዕዛዝ የተፈፀሙ ቢመስሉም፣ ነገር ግን በእርግጥ የታዘዘው በእራሱ በፍፁም ኃያሉ አምላክ ነበር። በመጨራሻም የእምነቱ መንፈሳዊ እና አስተዳደራዊ ማዕከል ወደ ተመሰረተበት ሀገር (እስራኤል) እስኪደርስ ድረስ የአምላክ ክስተት የሆነው ባሃኡላህ ከትውልድ ስፍራው (ኢራን) አንስቶ እስከ አቆር ዳርቻ ከቦታ ቦታ ሲዘዋወር የተለቀቁትን ኃይል አቅሞች ለማስላት አይቻልም። በአጠቃልይ 40 የእስርና የግዞት አመታትን አሳልፏል።
በነዚህም ዓመታት የባሃኡላህ ብዕር የሰው ልጅ አስደናቂ የሆነ የዓለም ስልጣኔ ለመገንባት የሚያስችለውን መመሪያ የያዙ እጅግ ብዙ ፅሑፎችን (ጥራዞችን) ለዓልም ገለጿል። ጽሑፎቹም ብዙ ነገሮችን ያዘሉ ሲሆኑ በውስጣቸው በግልም ሆነ በማኅበረሰብ ደረጃ ስለማንኛውም ሰበዓዊ አኗኗር፥ ስለምድራዊና ስለመንፈሳዊ ነገሮች፥ ስለዘመናዊውና ስለቀድሞው ቅዱሳት መጻሕፍት ትርጉምና በቅርብም ሆነ በሩቅ ለወደፊቱ ስለሚሆኑት ነገሮች ትንቢት ይገኝባቸዋል። አብዱል-ባሃ፥ ባሃኡላህ ስለምዕራባውያን ጽሑፎች የተለያየ ጥናት ያደረገ መሆኑንና ጽሑፎቹንም በእነርሱ ላይ መሥርቶ እንደሆነ በተጠየቀ ጊዜ፣ ‘የባሃኦላህ መጻሕፍት የተጻፉት እ.ኤ.አ. በ1870ዎቹ በፊት ባሉ ብዙ ዓመታት ነው። ጽሑፎቹ ባሁኑ ዘመን በምዕራባውያን ዘንድ የተለመዱ ሃሳቦችን ያዘሉ ቢሆንም እነዚህ ሃሳቦች በዚያን ጊዜ እንኳን መጻፍ እንዲያውም አልታሰቡም፤’ ሲል መልሷል ።
የባሃኢ እምነት መስራች ባሃኡላህ እ.ኤ.አ. በ1892 አረፈ። በ1868 በኦቶማን መንግስት ወደ ፍልስጤም ተወስዶ በመጨረሻም ባለሥልጣናቱ የእስር ቤቱን ሁኔታ እስኪያላሉት እና እንዲንቀሳቀስ እስከተፈቀደለት ድረስ ባሃኡላህ እና ቤተሰቡ በታላቁ የአቆር እስር ቤት በርካታ አመታትን በከባድ እስር አሳልፈዋል። ምንም እንኳን መንግስት የቤት ውስጥ እስራትን በመጣል እንቅስቃሴውን የገደበ ቢሆንም እ.ኤ.አ. በ1879 ባሃኡላህ ከአካ በስተሰሜን ወደሚገኘው "ባሀጂ" ወደሚባል የገጠር መኖሪያ ስፍራ ተዛወረ - ትርጉሙም በአረብኛ "ደስታ" ማለት ነው ። ባሃኡላህ የመጨረሻዎቹን አስርት አመታት ያሳለፈው በዚህ የባሀጂ መኖሪያ ስፍራ ነበር። አሁን ይህ ስፍራ የባሃኡላህ ቅዱስ መካነ መቃብር የሚገኝበት እና ለተከታዮቹም በምድር ላይ እጅግ የተቀደሰው ቦታ ነው።
በአለም ዙሪያ ያሉ ባሃኢዎች መንፈሳዊ ጉዞ ወደዚህ የተቀደሰ ስፍራ ያደርጋሉ። በአሁኑ ሰሜናዊ እስራኤል ውስጥ የሚገኘው ዓመቱን ሙሉ የሚያብቡና እጅግ በሚያማምሩ እርከኖችና የአትክልት ቦታዎች የተከበበው ይህ ቅዱስ ቦታ ከመላው ዓለም የሚመጡ እንግዶችንም ጭምር ያለማቋረጥ ይቀበላል።
“በእግዚአብሔር መንገድ ስጓዝ ዓይን ያላየውና ጆሮ ያልሰማው ሥቃይ ደርሶብኛል። ወዳጆች ከድተውኛል፤ መንገዶች አዳጋች ሆነውብኛል፤ የደኅንነት ምንጭ ደርቆብኛል፥ የምቾትም ሜዳም ተለብልቦብኛል። ስንት ሥቃይ ደርሶብኛል! ለወደፊትስ ስንት ይደርስብኝ ይሆን! ወደ ኃያሉና ወደ ለጋሱ ሳመራ ከኋላዬ እባብ ይከተለኛል። ከዓይኖቼ በሚዘንበው እንባ መኝታዬ ራሰ። ግን ሃዘኔ ለራሴ አይደለም። በእውነት እላችኋላሁ! ለአምላክ ፍቅር ራሴን ለጦር አሳልፌ ለመስጠት እፈቅዳለሁ። በዛፍ አጠገብ በማልፍበት ጊዜ በልቤ “አንተ ዛፍ! በስሜ በተቆረጥክና በጌታዬ ስም ሰውነቴ አንተ ላይ በተሰቀለ!” ብዬ ሳላዋየው ያለፍኩት ዛፍ የለም። አዎን! ምክንያቱም የሰው ልጆች በስካራቸው ወደ ጥፋት ጎዳና ሲያመሩ እያየሁና ይህንንም ሳያውቁ በመቅረታቸው ነው። አምላካቸውን ረስተው ምኞታቸውን ብቻ ከፍ ከፍ በማድረግ የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ እንደፌዝ፥ እንደጨዋታና እንደቀልድ የወሰዱት ይመስላል። ይህንንም በማድረጋቸው ደግ የሠሩና በደህንነት ምሽግ ውስጥ የተጠለሉ መስሏቸዋል። ነገሩ እነሱ እንደሚያስቡት አይደለም፤ ዛሬ የካዱትን ነገ ሲፈጸም ያዩታልና…ነገር ግን እኔም በእምቅድመ ዓለሙ ንጉሥ በዓለሞች ፈጣሪና ኃያል በሆነው አምላክ ስም እንደታጋሾቹና እንደማያወላውሉ መንፈሰ ጠንካራ እሆናለሁ። በማንኛቸውም ሁኔታ ለአምላክ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። እርሱ ኃያሉና ቸሩ፥ ሰዎች ፊታቸውን በፍቅር ወደርሱ እንዲመልሱ እንዲያደርጋቸው በጸጋው ተስፋ እናደርጋለን። (እርሱ ነውና ከሁሉ የላቀ!) ... በዕውነቱ እርሱ የለመነውን የሚሰማና ስሙንም ለሚጠራው ቅርብ ነው። እኛም ይህን የሥቃይ ጨለማ ለቅዱሳት ገላ ጋሻ አድርጎ ከሹሉ ሰይፍና ከሰላው ጎራዴ እንዲጠብቃቸው እንለምነዋለን። ብርሃኑ የበራውና ምስጋናውም ሳያቋርጥ ሲያበራ የኖረው በመከራ ብዛት ነው። ይህም ከጥንት ጀምሮ ባለፉት ዘመናት የርሱ መንገድ ነው።” ባሃኡላህ
የባሃኡላህን ፅሑፎች ለማንበብ ከፈለጉ እንዲሁም ባገኙት እውቀት ማህበረሰቦትን ማገልገል ከፈለጉ
Interesting blog? Like it on Facebook, +1 on Google, Tweet it or share this article on other bookmarking websites.