የባሃኢ ሃይማኖት አስተዳደር የቅስና ሥርአት ወይም የግለሰብ ሀይማኖት መሪዎች የሉትም። የሀይማኖት መሪነትን ተግባር በማከናወን የተለየ ሥልጣን በመያዝ ከምዕመናን ወገኖቻቸው የተለዩ ክፍሎች የሉም። የባሃኢ እምነት የሚተዳደረው እርስ በእርስ ተያያዥነት ባላቸው ተቋማት ነው።
በቀድሞ ዘመናት ግለሰቦች የሀይማኖት መሪነትን ተግባር መያዛቸው አስፈላጊ ነበር። አሁን ግን የሰው ዘር እውነትን በነፃነት ለመመርመር የሚያስችለው አቅም ላይ ይገኛል። አምልክ የሰው ልጆችን ክቡር አድርጎ ፈጥሯል። እያንዳንዱ ሰውም በራሱ ውስጥ የአምላክን ባሕርያት እና ስሞች ተጎናጽፏል። በዚህም መሠረት እያንዳንዱ ግለሰብ ለራሱ መንፈሳዊ እድገት ሀላፊነት በመውሰድ በውስጡ የተቀመጡትን የአምላክ ባህሪያትን የማውጣት እና ራሱንም ሆነ አካባቢውንም የመለወጥ ሀላፊነት አለበት። ቅዱሳን መጻሕፍትን ለራሱ ሊያጠናና የሕይወትን ውሃ ለራሱ በቀጥታ ከምንጩ ሊቀዳ ይችላል።
ለሕጻን አስተማሪ አስፈላጊ ነው። ሆኖም የአስተማሪው ዓላማ ሕጻኑን ያለአስተማሪ እራሱን እንዲችል፣ በእራሱ ዓይን እንዲያይ፣ በራሱ ጆሮ እንዲሰማና በራሱ አእምሮ እንዲረዳ ማድረግ ነው። እንደዚሁም የሰው ዘር በሕጻንነቱ ዘመን የሀይማኖት መሪዎች አስፈላጊው ነበሩ። ነገር ግን እውነተኛ ተግባሩ ሰዎች ራሳቸውን እንዲችሉ፣ መለኮታዊ ነገሮችን በራሳቸው ዓይን ለማየት፣ በራሳቸው ጆሮ ለመስማትና በራሳቸው አእምሮ ለመረዳት እንዲችሉ ማድረግ ነው። የባሃኢ ትምህርቶችም ዓላማ የሰው ልጆች ከእግዚአብሔር በስተቀር ከማንኛውም ነፃ ሆነው በቀጥታ ወደእርሱ፣ ማለትም ወደ ክስተቱ ፊታቸውን እንዲመልሱ ማድረግ ነው።
Interesting blog? Like it on Facebook, +1 on Google, Tweet it or share this article on other bookmarking websites.