የባሃኢ ማህበረሰብ ጉዳይ የሚተዳደረው በተቋማት ስርዓት ሲሆን እያንዳንዱ ተቋም የራሱ የሆነ የተግባር መስክ አለው። የባሃኢ አስተዳደርን ባሃኡላህ ለግለሰቦች አደራ አልሰጠም። የሕይወትን ውሃ ወደ ሕልውና መስክ የሚያመጣበትን የተቋማትን መረብ አቅዷል። የአስተዳደራዊ መዋቅሩ ሃይማኖቱ የታለመለትን ግብ እንዲመታ መንገድ ወይም መሣሪያ በመሆን ወሳኝ ሚና ይጫወታል። መመካከርን እና እኩልነትን መሰረት ያደረገ የአስተዳደር መዋቅር፣ የህዝቦችን ሰላማዊ ወይም ገንቢ ግንኙነት ጠብቆ ወደ አንድነት ይመራቸዋል። የባሃኢ አስተዳደር ተቋም ዋና ዓላማ በልዩ ልዩ ነገዶች፣ ዘሮች፣ መደቦች፣ ሀይማኖቶች፣ እና አመለካክቶች መካከል ዘላቂ አንድነትን ለመፍጠር ነው።
የአካባቢ መንፈሳዊ ጉባዔ
በአካባቢ ደረጃ፣ የባሃኢ ማህበረሰብ ጉዳዮች የሚተዳደሩት ዘጠኝ አባላትን ባቀፈው የአካባቢ መንፈሳዊ ጉባኤ ነው።
ከአካባቢ መንፈሳዊ ጉባኤ ኃላፊነቶች ውስጥ፡ የህፃናትን እና ወጣቶችን መንፈሳዊ ትምህርት ማሳደግ፣ የባሃኢ ማህበረሰብ ህይወትን መንፈሳዊ እና ማህበራዊ መዋቅርን ማጠናከር፣ የአካባቢው ግለሰብ ነዋሪዎችን ማማከር የገኙበታል።
ይህም ተቋም በዓመት አንድ ጊዜ ሚያዝያ 21 ቀን በሪዝቫን የመጀመሪያ ቀን ለአካለ መጠን በደረሱ ምዕመናን (ከ18 ዓመት እና ከዚያ በላይ) በሚስጥር ድምጽ ይመረጣል። (ሪድቫን ባሃኡላህ ማንቱን ያወጀበት በዓል ነው።) በአካባቢው የሚኖሩ ሁሉም ባሃኢዎች በጸሎት መንፈስ ተሰብስበው ለመንፈሳዊ ጉባኤ ለመመረጥ በጣም ብቁ ናቸው የሚሏቸውን 9 የአዋቂ ግለሰቦች (21 ዓመት እና ከዚያ በላይ) አባላትን ስም ይጽፋሉ። ሚስጥራዊነቱን በጠበቀ መልኩ እያንዳንዱ አማኝ ድምጹን ይሰጣል። ምንም አይነት የእጩነት ስርዓት የለውም። አጠቃላይ ሂደቱ ምንም አይነት የምረጡኝ ዘመቻ የሌለበት ነው። መራጮች የግለሰቦችን ተገቢነት በተመለከተ እርስ በርሳቸው አይነጋገሩም። ድምጽ የሚሰጥ እያንዳንዱ ባሃኢ በአካባቢው ያሉትን የወንዶች እና የሴቶች መንፈሳዊ ባህሪያት ግምት ውስጥ በማስገባት፡ አምላክ እንዲረዳው ጸሎት በማድረግ ይመርጣል።
በአካባቢያዊ መንፈሳዊ ጉባኤ ውስጥ ለማገልገል መመረጥ ማንኛውም አማኝ በማንኛውም ጊዜ ሊጠሩበት የሚችሉበት ኃላፊነት ነው። ነገር ግን በግለሰብ ዘመቻ ወይም ቅስቀሳ ሊደረግበት አይችልም።
የአካባቢ መንፈሳዊ ጉባኤን ጨምሮ ማንኛውብ የባሃኢ አስተዳደር ስርዓት በምክክር ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ስለመንፈሳዊ ጉባኤ ሥራና ኃላፊነት አስመልክቶ አብዱል-ባሃ እንዲህ ሲል ጽፏል፦
“ለሚመካከሩ ሁሉ መሠረታዊና አስፈላጊ ነገሮች የሃሳብ ቀናነት፣ የመንፈስ ንጽሕና፣ ከሁሉም የግል ፍላጎቶች ርቆ የእግዚአብሕርን ብቻ መከተል፣ በመለኮታዊ መዓዛው መማረክ፣ በምዕመናኑም መካከል ትሕትናና ዝቅተኝነትን ማሳየትና እግዚአብሔርን በማገልገል ላይ በሚደርሰው ረጅም ሥቃይና ችግር መታገስ ናቸው። የእግዚአብሔር ፈቃዱ ሆኖ እነዚህን ጸጋዎች ከታደሉ ከማይታየው የባሃ መንግሥት አሸናፊነት ለእነርሱ ይወርድላቸዋል። በዚህ ዘመን የጉባኤዎች መመካከር አንገብጋቢና እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። ለእነርሱም መታዘዝ አስፈላጊና ግዴታም ነው። አባሎቹ አንዳች ቅሬታና አለመግባባት በማይፈጠርበት መንገድ መመካከርና መወያየት አለባቸው። ይህም የሚሆነው እያንዳንዱ አባል ሃሳቡን በሙሉ ነፃነት አቅርቦ ምክንያቶቹን በግልጽ ሲደረድር ነው። ማንም ሰው ሃሳቡን ቢቃወም ጉዳዩን አጣርተው እስካልተወያዩበት ድረስ እውነተኛው መንገድ ስለማይገለጥ መቀየም የለበትም። የእውነት ብልጭታ የሚታየው ልዩ ልዩ ሃሳቦች ከተጋጩ በኋላ ነው። ከውይይቱ በኋላ አንድ ሃሳብ በሁሉም ከተደገፈ መልካም ነው፤ ግን የእግዚአብሔር ፈቃድ ባይሆንና ልዩነት ቢፈጠር የድምፅ ብልጫ ያገኘው ሃሳብ መጽደቅ አለበት። ...
“የመጀመሪያው ሁኔታ በጉባኤው አባሎች መካከል ፍጹም ፍቅርና ስምምነት መፍጠር ነው። የአንድ ባሕር ውሃ፣ የአንድ ወንዝ ሞገዶች፣ የአንድ ሰማይ ከዋክብት፣ የአንድ ፀሀይ ብርሃን፣ የአንድ አጸድ ዛፎች፣ የአንድ ተክል ሥፍራ አበቦች በመሆናቸው የልዩነትን መንፈስ ማስወገድና የእግዚአብሔርን አንድነት ማሳየት አለባቸው። ፍጹም አንድነትና ስምምነት ከሌለ ያ ስብሰባ መበተን፣ ጉባኤውም እንደሌለ መቆጠር አለበት። “ሁለተኛው ሁኔታ ወደ ስብሰባው በሚመጡበት ጊዜ ፊታቸውን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መመለስና ከእግዚአብሔርም ዕርዳታን መጠየቅ አለባቸው። ... ውይይቱ ነፍስ የምትዳብርበት፣ ሕፃናት የሚማሩበት፤ የድሆች ችግር የሚቃለልበት፤ በዓለም ያሉ በማንኛቸውም ክፍል የሚገኙ ድኩማን የሚረዱበት፤ ለሰው ሁሉ ችሮታ የሚደረግበት፤ የእግዚአብሔር መዓዛ የሚሰራጭበትና ቅዱስ ቃሉ የሚስፋፋበትን የመሳሰሉ መንፈሳዊ ጉዳዮችን የሚመለከት መሆን አለበት። እነዚህን ሁኔታዎች ለማሟላት ከቻሉ የመንፈስ ቅዱስ ፀጋ ይወርድላቸውና ጉባኤው የመለኮታዊ ቡራኬ ማዕድ ይሆናል።የሰማይ መላእክት ለእርዳታ ይደርሱላቸዋል። በየዕለቱም በአዲስ መንፈስ ይሞላሉ።”
ብሔራዊ መንፈሳዊ ጉባዔ
በአገር አቀፍ ደረጃ የባሃኢ ማህበረሰብ ጉዳይ የሚተዳደረው ዘጠኝ አባላትን ባቀፈው በብሔራዊ መንፈሳዊ ጉባኤ ነው። ብሔራዊ መንፈሳዊ ጉባኤ የሚመረጠው በአመት አንድ ጊዜ ከየአካባቢው በሚመጡ ተወካዮች አማካኝነት ነው።
በተለያዪ አካባቢው ያሉ የአካባቢ መንፈሳዊ ጉባኤዎች የነዚህን ተወካዮች ምርጫ በየአመቱ ያመቻቻሉ። እነዚሀ ተወካዮች በዓመት አንድ ጊዜ ብሔራዊ ስብሰባ ያደርጋሉ። በየአካባቢያቸው ስለሚሰሩት የማህበረሰብ ግንባታ ሂደት ላይ የመካከራሉ፣ ልምዶችንና ግንዛቤዎችን ይለዋወጣሉ፣ እንዲሁም የብሔራዊ መንፈሳዊ ጉባኤ አባላትን ይመርጣሉ። በተጨማሪም የአለፈውን ዓመት የብሔራዊውን የሥራ ፍሬ ዘገባ በዚህ ስብሰባ ይቀርባል።ለአዲሱ ብሔራዊ መንፈሳዊ ጉባኤም ሃሳብ ይቀርባል።
ከላይ የተገለጹት የባሃኢ ምርጫ መሰረታዊ ህጎች ለብሄራዊ መንፈሳዊ ጉባኤ ምርጫም ተፈጻሚ ይሆናሉ። ሚስጥራዊነቱን በጠበቀ መልኩ እያንዳንዱ ተወካይ ድምጹን ይሰጣል። ምንም አይነት የእጩነት ስርዓት የለውም። አጠቃላይ ሂደቱ ምንም አይነት የምረጡኝ ዘመቻ የሌለበት ነው። መራጮች የግለሰቦችን ተገቢነት በተመለከተ እርስ በርሳቸው አይነጋገሩም። ድምጽ የሚሰጥ እያንዳንዱ ባሃኢ በ አገሪቷ ያሉትን የወንዶች እና የሴቶች መንፈሳዊ ባህሪያት ግምት ውስጥ በማስገባት፡ አምላክ እንዲረዳው ጸሎት በማድረግ ይመርጣል።
ከብሔራዊ መንፈሳዊ ጉባኤ ሀላፊነቶች መካከል፡ በአንድ ሀገር ውስጥ ያሉ የባሃኢ ማህበረሰብን እድገት እና ንቁነት ማጎልበት ፣ ከመንግስት ጋር ያለውን ግንኙነት መከታተል ፣ ከግለሰቦች እና ከአካባቢያዊ መንፈሳዊ ጉባኤዎች የሚነሱ ጥያቄዎችን መፍታት ፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ የባሃኢ ማህበረሰብን በህብረተሰብ ህይወት ውስጥ ያለውን ተሳትፎ ማጠናከር የገኙበታል።
ዓለም አቀፍ ቤተ ፍትሕ
ዓለም አቀፍ ቤተ ፍትሕ በየአምስት አመቱ በሁሉም ሀገራት ባሉ የባሃኢ ብሔራዊ መንፈሳዊ ጉባኤ አባላት የሚመረጥ ዘጠኝ አባላት ያሉት ተቋም ነው። ይህ ተቋም ዓለም አቀፍ የባሃኢ እምነት የአስተዳደር ተቋም ነው። በዓለም ዙሪያ በሙሉ የሃይማኖቱን ጉዳይ ይመለከታል፣ መመሪያም ይሰጣል። በሰው ልጅ ደኅንነት ላይ አዎንታዊ ተጽእኖ እንዲያሳድር፣ ትምህርትን፣ ሰላምን እና ዓለም አቀፋዊ ብልጽግናን እንዲያጎለብት እና የሰውን ክብር ለማስጠበቅ ለዓለም ባሃኢዎች ብቻ ሳይሆን ለመላው የሰው ዘር ደህንነት እንዲሆን ባሃኡላህ ለዚህ ተቋም ስልጣን ሰቶታል።
አለም አቀፍ ቤተ ፍትሕ የሚሰጠው መመሪያ ባሃኡላህ ለአለም አቀፍ ስልጣኔ ያለውን ራዕይ ወደ እውነታ የሚተረጉም ነው። በማህበረሰብ ውስጥም የአስተሳሰብ እና የተግባር አንድነትን ያረጋግጣል። የከንቱ ጥላቻ መወገድ፣ የልዩ ልዩ ዘሮች፣ ነገዶችና የሃይማኖት ክፍሎች መቀራረብ እና አንድ መሆን፣ ለሰው ክብርም የሚገባው ፍትሕ፣ ሰላም እና አንድነት በጠንካራ መሰረት ላይ እንዲመሰረት ዓለም አቀፍ ቤተ ፍትሕ የማያቋርጥ መመሪያ የሰጣል።
Interesting blog? Like it on Facebook, +1 on Google, Tweet it or share this article on other bookmarking websites.