የእግዚአብሔርን ክስተት ማወቅ ማለት፥ እርሱንም መውደድ ነው። አንዱ ያለሌላው ሊሆን አይችልም። እንደ ባሃኦላህ አነጋገር ሰው የተፈጠረበት ምክንያት እግዚአብሔርን ያውቅና ይወደውም ዘንድ ነው
ከመልእክቶቹ በአንዱ እንዲህ ይላል፦
“ለሁሉም ፍጥረት የመፈጠር ምክንያት ፍቅር ነው፥ በታወቀው ባህላዊ አነጋገር ‘ድብቅ ዕንቁ ነበርሁ ለመታወቅም ወደድሁ፤ ስለዚህ እታወቅ ዘንድ ፍጥረትን ፈጠርኩ’ ይላል።”
በኅቡአተ ቃላት እንዲህ ይላል፦
“የሕያው ልጅ ሆይ!
“አፍቅረኝ አፈቅርህ ዘንድ፥ ባታፈቅረኝ ግን የእኔም ፍቅር በምንም ዓይነት ሊደርስህ አይችልም። ይህንን እወቅ አገልጋይ ሆይ!”
“የአንጸባቂ ራዕይ ልጅ ሆይ!
“በውስጥህ የእኔን የራሴን መንፈስ እስትንፋስ ተንፍሼአለሁ፥ አፍቃሪዬ ትሆን ዘንድ፥ ለምን እኔን ትተህ ሌላ ወዳጅ ፈለግህ?”
የእግዚአብሔር አፍቃሪ መሆን! ይህ ብቻ ነው የባሃኢ ዋና የሕይወቱ መሠረተ ዓላማ። ፍጹም የደስታ ምንጭ የሆነው እግዚአብሔርን እንደዋና ቅርብ ጓደኛና ዘመድ፥ አቻ እንደሌለው ወዳጅ መውሰድ! እግዚአብሔርን መውደድ ማለት ማንንም፥ ሁሉንም መውደድ ማለት ነው። ሁሉም የእግዚአብሔር ናቸውና። እውነተኛ ባሃኢ ፍጹም አፍቃሪ ይሆናል። በንጹህ ልብ ሁሉንም ከልብ ይወዳል። ማንንም አይጠላም። የታላቁ ወዳጁን መልክ በእያንዳንዱ ፊት ማየት ስለሚችልና ምልክቱንም በያለበት ስለሚያገኘው ማንንም አይንቅም። ፍቅሩ የሃይማኖት፥ የሀገር፥ የነገድ፥ የጎሳ ወሰን አያውቅም።
ባሃኦላህ እንዲህ ይላል፦
“በቀድሞ ዘመን እንዲህ ተብሏል፥ ‘የአንድን ትውልድ አገር ማፍቀር ሃይማኖት ነው።’ የታላቁ ሥልጣን አንደበት ግን በዚህ ክስተቱ ዘመን እንዲህ ይላል፦ ‘መመካት የእርሱ ሐገሩን የሚወድ አይደለም፥ መመካት ግን ለእርሱ የሰውን ዘር ለሚወድ እንጂ’” (ታብሌት ኦፍ ዘወርልድ)“እርሱ ወንድሙን ከእራሱ የማያስቀድም የተባረከ ነው። እንዲህም ያደረገ ከባሃ ሕዝብ እንደ አንዱ ነው።” (ወርድስ ኦፍ ፓራዳይስ)
አብዱል-ባሃ ‘በብዙ ሰውነቶች እንደተዋሃደች እንደ አንዲት ነፍስ መሆን እንዳለብንና በበለጠም እርስ ብርስ ስንፋቀር ወደ እግዚአብሔር እንደምንቀርብ’’ ይነግረናል።
“እንዲሁም የእግዚአብሔር ክስተቶች መለኮታዊ ሃይማኖቶች ምንም በስም ቢለያዩ በመሠረቱ አንድ ናቸው። ብርሃን ከማንኛቸውም በኩል ይምጣ፥ ሰው ብርሃንን አፍቃሪ መሆን አለበት። ከየትኛውም አፈር ላይ ትብቀል ሰው የጽጌረዳ ወዳጅ መሆን አለበት። ምንጩ ከየትም ይሁን ሰው የእውነት ፈላጊ መሆን አለበት። ፋኖሱን መውደድ ብርሃኑን መውደድ አይደለም። መሬትንም ማፍቀር አይገባም፥ የሚያበቅላትን ጽጌረዳ እንጂ። ዛፉን ብቻ መውደድ ትርፍ የለውም። ከፍሬው መቋደስ ግን ጠቃሚ ነው ። ጣፋጭ ፍሬዎች በማንኛውም ዛፍ ይብቀሉ ከየትኛውም ቦታ ይገኙ መወደድ አለባቸው። የእውነት ቃል በማንም አንደበት ይነገር መከበር አለበት። ፍጹም እውነቶች በማንኛውም መጽሐፍ ይመዝገቡ መቀበል አለብን። ምክንያት ለሌለው ጥላቻ ማኅደር መሆን ድንቁርናንና ውርደትን ያስከትላል። በሃይማኖቶች፥ በሀገሮችና በነገዶች መካከል ግጭት የሚነሳው ከአለመግባባት ነው። ሃይማኖቶችን ዓላማቸውንና በመሠረታቸው ያለውን ቁም ነገር ለማግኘት ብንመረምር አንድ ሆነው እናገኛቸዋለን። ምክንያቱም መሠረታዊ እውነታቸው አንድ እንጂ ብዙ ስለአልሆነ ነው። ይህም ከሆነ የዓለም ሃይማኖት ተመራማሪዎች አንድ የአንድነት የመግባቢያ ነጥብ ላይ ይደርሳሉ ማለት ነው።”
እንደገናም እንዲህ ይላል፦
“ይህ ጮራ በአድማስ ተዘርግቶ፥ ይህ ዜማ ሰዎችን ሁሉ አስደስቶ፥ ይህ መለኮታዊ ፈውስ ለማንኛውም በሽታ መድኃኒት ሆኖ፥ ይህ የእውነት መንፈስ ለእያንዳንዱ ነፍስ የሕይወት ምክንያት ይሆን ዘንድ እያንዳንዱ ምዕመን ሌሎችን መውደድ አለበት። ንብረቱንና ሕይወቱንም ከነርሱ መሰወር አይገባውም። እንዲያውም ለሌሎች ደስታና ሐሴት ምክንያት ለመሆን መጣር ይኖርበታል። ሌሎች ደግሞ የግል ዝንባሌ የሌላቸውና ራሳቸውን መስዋዕት አድራጊ መሆን አለባቸው” (ታብሌት ኦፍ አብዱል-ባሃ ቮሊዩም 1 ገጽ 147)
READ MORE: http://www.bahai.org/