የባሃኢ እምነት በኢትዮጵያ ውስጥ እንዴት ተጀመረ?
የባሃኢ ሃይማኖትን ወደ ኢትዮጵያ የገባው ሳብሪ ኤሊያስ በሚባሉ ግብፃዊ አማኝ አማካኝነት ነው። እኝህ ሰው በወጣትነታቸው ማለትም በ27 ዓመታቸው እ.ኤ.አ 1933 ያለምንም ቅድመ ዝግጅት ፣በውስን አቅማቸውና የኢትዮጰያን ቋንቋዎችን ባለማወቃቸው ሳይገቱ የባሃኢ ሃይማኖትን ለማስተማር ወደ ኢትዮጵያ መጡ። በልብስ ስፌት ስራም መተዳደር ጀመሩ ። ጎን ለጎንም ሃይማኖቱን ማስተማር ጀመሩ። ከብዙ ጥረት፥ ልፋትና ፈተናም በኋላ አንዳንድ ኢትዮጵያን ሰዎች ሃይማኖቱን መቀበል ጀመሩ። ከዚያም የባሃኢ ሃይማኖት የአስተዳደር ተቋም የሆነውን የአካባቢ መንፈሳዊ ጉባዔ ለመጀመሪያ ጊዜ ለማቋቋም አስቻሉ።
ከሳብሪ ኤሊያስ ታላቅ ስኬት መካከል “ባሃኡላህና አዲሱ ዘመን” የተሰኘውን መፅሀፍ በ1934 እ.ኤ.አ ወደ አማርኛ ለማስተርጎምና ማሳተም መቻላቸው ነው። የመፅሀፉም ቅጅ በጊዜው ለነበሩ ቤተ መጽሃፍቶችና ለዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ባሃኢዎች ተሰራጭቷል። በ1936 እ.ኤ.አ የመፅሃፉ ቅጂ በወቅቱ የኢትዮጵያ መሪ ለነበሩት ንጉስ ሃይለስላሴ እየሩሳሌም በነበሩበት ወቅት ወ/ሮ ሎሮል ስቸፐፍሎቸር በተባሉ ካናዳዊ ባሃኢ አማካኝነት ተሰጥቷቸዋል።
በ1935 እ.ኤ.አ በጣሊያን ወረራ አማካኝነት በሃገሪቱ በተከሰተው ብጥብጥና አለመረጋጋት ሳቢያ ሳብሪ ኤሊያስ ወደ ትውልድ ሀገራቸው ግብፅ ለመመለስ ተገደዱ። ወደ ሀገራቸው ግብፅ ከተመለሱ በኋላ ወ/ሮ ፋሂማ ያኩት ጋር በጋብቻ ተቆራኙ። እንዲሁም የሁለት ወንድ ልጆች አባት ሆኑ። ነገር ግን በ1944 እ.ኤ.አ የጣሊያን ወረራ ማቆም ማግስት ሳብሪ ኤሊያስ ከባለቤታቸው ወ/ሮ ፋሂማ ያኩት እና ከሁለት ወንድ ልጆቻቸው ሁሴንና ሳፋ ጋር ወደ ኢትዮጵያ ለመኖር መጡ። በዚህ ጊዜ ሃገሪቱ በጣሊያን ወረራ ምክንያት ብዙ ችግር ውስጥ ገብታ ስለነበረች ሁሉንም ነገር ቀድሞ እንደነበሩት ሊያገኙት አልቻሉም።
እሳቸው በነበሩበት ወቅት እምነቱን የተቀበሉትን ሰዎች ሊያገኟቸው አልቻሉም። እምነቱን እንደገና በዚህች የተቀደሰች ሃገር ለማስፋፋት ጥረት ጀመሩ። ወዲያውኑም የጃንሆይ (ንጉስ ሃይለስላሴ) ፍርድ ሸንጎ የህግ ሰው የነበሩት ቀኝ አዝማች ጊላ ሚካኤል ባህታ የተባሉ ሰው እምነቱን ተቀበሉ። እኚህም ሰው የእምነቱ ጠንካራ አማኝና አገልጋይ ሆኑ። በጥቂት ወራት ውስጥ የአማኞች ቁጥር እየጨመረ ሄደ።
የባሃኢ ማህበረሰቦች መስፋፋትና መጠናከር
በ1953 እ.ኤ.አ በአለም ዙሪያ የሚገኙ የባሃኢ ማህበረሰቦች በሾጊ ኤፈንዲ አማካኝነት የ10ዓመት እቅድ (ከ1953 – 1963) የተሰኘውን ይህን እምነቱን ለማስፋፋትና ለማጠናከር የተቀረፀውን የመጀመሪያውን አለማቀፋዊ እቅድ በይፋ ጀመሩ። በእነዚህ አስርት ዓመታት ውስጥ ባሃኢዎች በፕላኔቷ እያንዳንዷ ጫፍ ውስጥ እምነቱን ለማስፋፋትና ለማጠናከር ተሰራጩ። በ1953 እ.ኤ.አ ገደማ በርካታ ባሃኢዎች ከግብፅ፥ አሜሪካና ኢራን ወደ ኢትዮጵያ በአገር አቅኚነት መምጣት ጀመሩ።
በ1963 እ.ኤ.አ የሲቪል አቪየሽን፥ የዩንቨርስቲና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች እምነቱን በብዛት መቀበል ጀመሩ ። ለእነዚህ አዳዲስ አማኞቹም የጥልቀት ትምህርት በእነዚህ አገር አቅኚዎችና ነባር አማኞች አማካኝነት መሰጠት ተጀመረ። ከዚህ በኋላ ጠንካራ የባሃኢ ማህበረሰብ መፈጠር ጀመረ።
በ1960 እ.ኤ.አ የአዲስ አበባ ማህበረሰብ በከፍተኛ ሁኔታ ማደግ በመጀመሩ ከባሃኢዎች መኖሪያ ቤቶች ወጥቶ በባሃኢ ማእከል ውስጥ እንቅስቃሴዎቹን ማካሄዱ የግድ ሆነበት። በ1962 እ.ኤ.አ ለባሃኢ ማእከል መስሪያ የሚሆን የመጀመሪያውን መሬት በግዢ አገኘ። በ10ዓመት ጊዜም የመጀመሪያውን የብሔራዊ የባሃኢ ማእከል ተገንብቶ በ1972 እ.ኤ.አ ተመረቀ። በመቀጠልም የባሃኢ ማህበረሰቦችን ለማስፋፋትና ለማጠናከር በቢሾፍቱ፥ አዳማ፥ አምቦ፥ ሰበታ፥ ሆለታ፥ ወሊሶ፥ ሃዋሳ እና ጅማ ጥረት ተጀመረ።
የባሃኢ አስተዳደራዊ ተቋማት መጠናከር
በባሃኢ ሃይማኖት በተለይ አንድ መወሳት የሚገባው ነገር አለ። ይኸውም የቅስና ስርዓት አለመኖር ነው። የአንድን አካባቢ ባሃኢዎች ጉዳይ ማየትና ማስተዳደር የአካባቢ መንፈሳዊ ጉባኤ ተብሎ የሚጠራው ተቋም ኃላፊነት ነው። ይህም ዘጠኝ አባሎች ያሉበት ተቋም በዓመት አንድ ጊዜ ሚያዚያ 21 ቀን በሪዝቫን የመጀመሪያ ቀን ለአካለ መጠን በደረሱ ምእመናን (ከ21 ዓመት በላይ) ይመረጣል። በብሔራዊ ደረጃም ይኸው ነው። በሃገሪቱ የሚገኙትን ባሃኢዎች የሚያስተዳድረው ብሔራዊ መንፈሳዊ ጉባዔ የተሰኘው ትቋም ሲሆን አባላቱም በሃገሪቱ ከሚገኙ ባሃኢዎች መካከል ዘጠኝ አማኞች በአመት አንዴ በሚስጥር ይመረጣሉ።
ከላይ እንደተገለፀው የመጀመሪያው አካባቢ መንፈሳዊ ጉባኤ በኢትዮጵያ የተመሰረተው በ1934 እ.ኤ.አ ነበር። የባሃኢ ማህበረሰብ በተለያዩ ከተሞችና የገጠር አካባቢዎች መስፋፋት ሲጀምር የአካባቢ መንፈሳዊ ጉባዔዎችም መቋቋም ጀመሩ። በ1956 እ.ኤ.አ የመጀመሪያው በሰሜን ምስራቅ ሃገራት ለሚኖሩ የባሃኢ ማህበረሰብ የሚያገለግል ብሔራዊ መንፈሳዊ ጉባዔ በካይሮ ተቋቋመ። ይህም መንፈሳዊ ጉባዔ በግብፅ፥ በኢትዮጵያ፥ ኤርትራ፥ ሊቢያ፥ ሱዳን፥ ሶማሊያና፥ ጅቡቲ የሚገኙን ባሃኢዎች ያገለግል ነበር። የአማኞቹና የአካባቢ መንፈሳዊ ጉባኤዎቹ ቁጥር በኢትዮጵያ በመጨመሩ የተነሳ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መንፈሳዊ ጉባዔ በ1975 እ.ኤ.አ በአዲስ አበባ ተቋቋመ።
በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ባሃኢዎች ቁጥር በርካታ ሲሆን በብሔራዊና በአካባቢ መንፈሳዊ ጉባዔዎች አማካኝነት ለማህበረሰባቸው የሚጠቅሙ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ ይገኛሉ። የዜግነት ግዴታቸውንም ለመወጣት ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉ አማኞች ሲሆኑ ለአገራቸው መንፋሳዊና ማሕበራዊ ደህንነት መረጋገጥ የማያሰልስ ጥረት የሚያደርጉ ናቸው። በንፁህ የአገልግሎት መንፈስ ለአገራቸው ማሕበረሰብ ዕድገትና ሰላም ይተጋሉ። በዓለም ዙሪያ ከሚተገበረው በባሃኢ ሃይማኖት አማካኝነት ከተቀረፀው ለሁሉም ከሚያገለግለው የስነ-ምግባር ትምህርት ዘዬም አገራቸው እንድትቋደስ ሁሉንም ዜጎች በማሳተፍ ይጥራሉ።
Interesting blog? Like it on Facebook, +1 on Google, Tweet it or share this article on other bookmarking websites.