ህፃናት የማሕበረሰቡ እንቁ እንደሆኑ የባሃኢ ሃይማኖት ያምናል። በእነሱ ውስጥ የወደፊቱ መልካም ተስፋ ተደብቆ ይገኛል ። እነሱ አንድ ማህበረሰብ ሊይዘው የሚችለው እጅግ በጣም የተከበረ ሀብት ናቸው። እኛ ዛሬ የምናደርገው ወይም ለማድረግ ያልቻልነው ነገር፣ በሕፃናት ሕይወት ላይ አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ተጽእኖ እንደሚኖረው እንዲሁም እነሱ ነገ እንደ ዓለም ዜጋ የሚፈጽሙትን ተግባር እንደሚወስን ምንም ጥርጥር የለውም። ስለዚህ በሞራል ስነምግባር ትምህርት መታነፃቸው የወቅቱ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው።
የህጻናት መንፈሳዊ ትምህርት ከ5 እስከ 11 አመት ለሆኑ፥ ከሁሉም ሃይማኖታዊ ዳራ ለሚመጡ ልጆች ክፍት ነው። ለእድሜያቸው በሚመጥን መልኩ የተነደፈ ሥርዓተ ትምህርትንም ይጠቀማል። የትምህርቶቹም ዓላማ ልጆች ጠንካራ መንፈሳዊ መሠረት እንዲያዳብሩ፣ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለማህበረሰባቸው እንዲሁም ለአለም አዎንታዊ አስተዋጽዖ ለማድረግ ቁርጠኝነት እንዲኖራቸው ለመርዳት ነው። እንደ ደግነት፣ መከባበር፣ ፍቅር፣ ፍትህ፣ ይቅር ባይነት፣ ወዘተ ያሉትን በጎ ምግባራትን ለማዳበርና ለመተግበር የሚያስችላቸውን አቅም በትምህርቶቹ ውስጥ ያገኛሉ።
አስተማሪዎች
የባሃኢ ሃይማኖት ለሁሉም ህፃናት ያዘጋጀው ትምህርትን የሚያስተምሩ አስተማሪዎች በባሃኢ የስልጠና ተቋማት የሰለጠኑ አስተማሪዎች ናቸው። ማንኛውም ወጣት ሆነ ጎልማሳ የዚህን ስልጠና በመውሰድ በየአካባቢው ህፃናትን በማስተማር አገልግሎት መስጠት ይችላል።
ተማሪዎች
የሕፃናት ትምህርቱን የሚወስዱት ሕፃናትም እድሜያቸው ከ11 ዓመት በታች የሆኑት ቢሆኑም እንደያስፈላጊነቱም በእድሜያቸው የሚከፋፈሉበት ሁኔታም ይኖራል። ትምህርቱም የሚስጠው እንደየአካባቢው ፍላጎት በሳምንት ለተወሰነ ጊዜ ይሆናል።
የትምህርቱ ይዘት
እያንዳንዱ የትምህርት ክፍለጊዜ የተቀረፀው በአንድ መንፈሳዊ ባህሪ ላይ እንዲያተኩር ተደርጎ ነው። ለምሳሌ በአንዱ ክፍለጊዜ የሚማሩት ስለፍቅር ወይም ስለፍትህ ከሆነ በፍቅር ወይም በፍትሕ ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ፀሎቶችን ያደርጋሉ፥ ቅዱሳን ጥቅሶችን በቃል ያጠናሉ፥ መዝሙሮችን ይዘምራሉ፥ ትረካዎችን ያዳምጣሉ፥ ጨዋታዎችን ይጫወታሉ ፥ ስእሎችን ይስላሉ። የሚያስተምረው መንፈሳዊ ባህሪያትን ማለትም እውነተኝነትን፥ ታማኝነትን፥ ፍቅርን፥ አንድነትን ፍትሃዊነትንና የመሳሰሉትን ባህሪያትን ማዳበርን ነው። እነዚህ ባህሪያት ደግሞ በሁሉም ሃይማኖት ትምህርቶች ውስጥ እንድናዳብራቸው የታዘዙ ናቸው። ይህም የባሃኢ የህፃናት ትምህርት ክፍለጊዜን ማንም ሰው ከየትኛውም የሃይማኖትንና የአኗኗር ሁኔታ ውስጥም ቢሆንም ሊያከናውነው የሚችል እንዲሆን አድርጎታል። ትምህርቱ የሚሰጥበትም ስፍራ እንደየአካባቢው ሁኔታ በቤት ውስጥ ፥ በዛፍ ጥላ ስር፥ በትምህርት ቤት ውስጥና በሌሎች ምቹ አካባቢዎች ሊሆን ይችላል።
በህፃናት ትምህርት ፕሮግራም ላይ ለማገልገል ከፈለጉ መልእከት ይላኩላን
Interesting blog? Like it on Facebook, +1 on Google, Tweet it or share this article on other bookmarking websites.