ጸሎት አንዲት ነፍስ፡ ከፈጣሪዋ ጋር የምትገናኝበት፣ ለመንፈሳዊ እድገቷም መሰረት የሆነ የዕለት ተዕለት ምግቧ ነው። በግለሰብም ሆነ በማኅበረሰብ ወይም በተቋማት ደረጃ፣ ጸሎት የማህበረሰቡ የአምልኮ ሕይወት ዋነኛ መገለጫ እንደሆነ የባሃኢ እምነት ያስረዳል።
ከባሃኢ ሃይማኖት ዋና ዋና አስተምህሮቶች አንዱ ከሁሉም ሃይማኖት ተከታዮች ጋር በወዳጅነት እና በአብሮነት መቀላቀል ሲሆን፤ የዚህም ተግባር አንዱ መገለጫ የሁሉንም ሃይማኖት ተከታዮች የሚያሳትፉ የጋራ ፀሎተ አምልኮ ክፍለ-ጊዜዎችን ማካሄድ ነው። በእንደዚህ አይነት የፀሎት ክፍለ-ጊዜም ሁሉም በአንድነት መንፈስ ፀሎት እንዲያደርግ፥ ከየቅዱሳን መፅሀፎቶቹም እንዲያነብ እና እንዲያሰላስል ይበረታታል።
እንደዚህ አይነት የጸሎት ክፍለ-ጊዜዎች በየቤቱ እና እንደየሁኔታው በተለያዩ አመቺ ቦታዎች የሚካሄዱ ሲሆን፡ ሁሉም ተሳታፊዎች የጋራ ሃላፊነት የሚወስዱበት እንቅስቃሴ እንጂ የግለሰብ ወይንም የአንድ ሃይማኖት የበላይነት የሚታይበት አይደለም። የዚህ ክፍለ-ጊዜ ዓላማ በሁሉም ሰዎችና ሃይማኖቶች መካከል አንድነትን ለማጠንከር፥ መቻቻልን ለማጎልበት፥ ሰላማዊ ህይወትን ለመምራትና ጥላቻን ለማስወገድ ነው።
በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች ውስጥ የሚገኙ ባሃኢዎች ከጎረቤቶቻቸው እና ከጓደኞቻቸው ጋር በወዳጅነት መንፈስ አንድ ላይ ሆነው ለመጸለይ በየጊዜው ይሰበሰባሉ። እነዚህ አጋጣሚዎች ተሳታፊዎች የጸሎትን ጣፋጭነት የሚያጣጥሙበት፣ በመካከላቸውም የአብሮነት ስሜትን የሚፈጥሩበት፣ ልቦቻቸውን የሚያስተሳስሩበት፣ አንድነታቸውንም የሚመሰርቱበት ናቸው። ከዚህም በላይ ተሳታፊዎች ስለ መንፈሳዊ ጭብጦች ትርጉም ያለው ውይይት ለማድረግ እንዲሁም በአካባቢያቸው ስላለው ችግር እና መፍትሔም ለመነጋገር እድል ይሰጣቸዋል። እነደዚህ አይነት የጸሎት ጊዜዎች የንቁ ማህበረሰብ ህይወት ዋነኛ መገለጫዎች ናቸው።
በእንደዚህ ዓይነት የጸሎት ቦታዎች ውስጥ መሳተፍ ይፈልጋሉ?
Interesting blog? Like it on Facebook, +1 on Google, Tweet it or share this article on other bookmarking websites.