የባሃኢ ማህበረሰብ ትምህርታዊ ጥረቶች የሚያተኩሩት በሁሉም የእድሜ ክልል የሚገኙ ግለሰቦችን መንፈሳዊ እና አእምሯዊ ችሎታዎቻቸውን በማሳደግ ለሚኖሩበት ማህበረሰብ አዎንታዊ አስተዋፅዖ እንዲያበረክቱ ለማስቻል ነው። ትምህርታዊ ሒደቶቹም፥ የህፃናት መንፈሳዊ ትምህርት፣ የታዳጊ ወጣቶች ፕሮግራም እና የጥናት ክበቦች ናቸው።
የህፃናት ትምህርት
ህፃናት የማሕበረሰቡ እንቁ እንደሆኑ የባሃኢ ሃይማኖት ያምናል። በእነሱ ውስጥ የወደፊቱ መልካም ተስፋ ተደብቆ ይገኛል ። እነሱ አንድ ማህበረሰብ ሊይዘው የሚችለው እጅግ በጣም የተከበረ ሀብት ናቸው። እኛ ዛሬ የምናደርገው ወይም ለማድረግ ያልቻልነው ነገር፣ በሕፃናት ሕይወት ላይ አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ተጽእኖ እንደሚኖረው እንዲሁም እነሱ ነገ እንደ ዓለም ዜጋ የሚፈጽሙትን ተግባር እንደሚወስን ምንም ጥርጥር የለውም። ስለዚህ በሞራል ስነምግባር ትምህርት መታነፃቸው የወቅቱ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው።
የህጻናት መንፈሳዊ ትምህርት ከ5 እስከ 11 አመት ለሆኑ፥ ከሁሉም ሃይማኖታዊ ዳራ ለሚመጡ ልጆች ክፍት ነው። ለእድሜያቸው በሚመጥን መልኩ የተነደፈ ሥርዓተ ትምህርትንም ይጠቀማል። የትምህርቶቹም ዓላማ ልጆች ጠንካራ መንፈሳዊ መሠረት እንዲያዳብሩ፣ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለማህበረሰባቸው እንዲሁም ለአለም አዎንታዊ አስተዋጽዖ ለማድረግ ቁርጠኝነት እንዲኖራቸው ለመርዳት ነው። እንደ ደግነት፣ መከባበር፣ ፍቅር፣ ፍትህ፣ ይቅር ባይነት፣ ወዘተ ያሉትን በጎ ምግባራትን ለማዳበርና ለመተግበር የሚያስችላቸውን አቅም በትምህርቶቹ ውስጥ ያገኛሉ።
የታዳጊ ወጣቶች ፕሮግራም
በታዳጊ ወጣቶች የትምህርት ፕሮግራም ውስጥ የሚሳተፉት እድሜአቸው ከ12 እስከ 15 ዓመት የሆኑ ልጆች ናቸው። ይህ የእድሜ ክልል ከልጅነት ወደ ሙሉ ወጣትነት የመሸጋገሪያ ወሳኝ የእድሜ ክፍል ሲሆን ፈጣን አካላዊ ፥ አእምሮእዊና ስሜታዊ ለውጦች ይካሄዱበታል። መንፈሳዊና አእምሮአዊ አመለካከታቸውም መስፋት ይጀምራል። በራሳቸው ውስጥ አዲስ የሆነ ጥያቄዎችንና እይታን፥ አቅምንና ችሎታን የሚያስተናግዱበትም ጊዜም ነው። ህብረተሰቡ ብዙውን ጊዜ ይህንን የዕድሜ ክልል በአንድ ሰው ሕይወት ውስጥ እንደ ሁከት ጊዜ ሊያየው ይችላል። ነገር ግን የታዳጊ ወጣቶች የትምህርት ፕሮግራም በእነዚህ ወጣቶች ላይ ርህራሄን፣ የፍትህ ስሜትን፣ ስለ አለም ለማወቅ ጉጉት እና ለተሻለ አለም ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋፅዖ ለማድረግ ያላቸውን ፍላጎት ይመለከታል።
የታዳጊ ወጣቶች የትምህርት ፕሮግራም በዚህ የእድሜ ክልል የሚገኙ ታዳጊዎችን የመግለፅ አቅማቸውን የሚያሳድግ፣ ጠንካራ የሞራል ማንነትእንዲመሰርቱ የሚያደርግ እንዲሁም ያላቸውን ጉልበት ማህበረሰባቸውን ላማሳደግ እንዲጠቀሙበት አቅምን የሚፈጥር ትምህርታዊ ፕሮግራም ነው።
የጥናት ክበብ
የጥናት ክበብ አንድ ላይ ለማጥናት፣ ለማሰላሰል እና ለመስራት በየጊዜው የሚሰበሰብ አነስተኛ የሰዎች ስብስብ ነው። አስራ አምስት አመት ወይም ከዚያ በላይ የሆነ ማንኛውም ሰው፣ ጾታም ሆነ ሀይማኖት ሳይገድበው ለመሳተፍ የሚችልበት ሂደት ነው። የጥናት ክበቦች አላማ የተሳታፊዎችን መንፈሳዊ እና አእምሮአዊ ክህሎት በማዳበር ከራሳቸው ሰፈር ጀምሮ ማህበረሰባቸውን ለመለወጥ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማበርከት የሚያስችላቸውን አቅም ማሳደግ ነው። የጥናት ክበብ የሚከናወነው ተከታታይ የሆኑ ኮርሶችን አሳታፊ በሆነ እና ተከታታይነት ባለው መንገድ በማጥናት ነው።የጥናት ክበባት በቤት ውስጥ ወይንም እንደየሁኔታው በሌሎች በሚመች ቦዎች ውስጥ መካሄድ ይችላሉ።
የመጀመሪያው መጽሐፍ (መጽሐፍ 1) "በመንፈስዊ ሕይወት ላይ እሰብታዎች" ይባላል። እንደ ጸሎት፣ ተመስጦ፣ ህይወት እና ሞት እና የነፍስ እድገትን የመሳሰሉ መንፈሳዊ ጉዳዮችን ይመረምራል። በአሁኑ ጊዜ እስከ መፅሃፍ 14 ድረስ የተለያዩ ጭብጦችን የሚዳስሱ ዋና ዋና ተከታታይ ኮርሶች በአግልግሎት ላይ እየዋሉ የገኛሉ። የተከታታይ ኮርሶቹ ዋና ዓላማ ተሳታፊዎች ለማህበራዊና መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲነሳሱ ማስቻል ሲሆን አጥኚዎችም በጥናት ክፍለ-ጊዜያቸው ለአገልግሎት የሚያስፈልጓቸውን ሃሳቦች በጥናት ይወያያሉ በጥልቀትም ያስቡበታል፥ እንዲሁም ለመተግበር ይነሳሳሉ።
በእነዚህ ትምህርታዊ ሂደቶች ላይ ለመሳተፍ፥ መልእክት ይላኩልን
Interesting blog? Like it on Facebook, +1 on Google, Tweet it or share this article on other bookmarking websites.