የባሃኢ እምነት የጀመረው እ.ኤ.አ በ1844 በፐርዥያ፡ ሺራዝ በምትባል ከተማ ውስጥ ባብ በሚባል የአምላክ መልዕክተኛ ነው። ባብ የሰው ልጆችን ለአዲስ መለኮታዊ የግልፀት ዘመን እና ለሌላ ለአዲስ የአምላክ መልእክተኛ እንዲያዘጋጅ በእግዚአብሔር እንደተላከ አስታወቀ።
ባብ ፍትህ እና ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር ዓለምን ሁሉ አንድ የሚያደርግበትን አዲስ ትምህርት ከአምላክ እንዲቀበሉ ሰዎችን ያዘጋጃቸው ነበር፡፡ በተጨማሪም ባብ ለዚህ ዘመን መለኮታዊ ትምህርት ገላጭ ለሆነው ለባሃኡላህ መንገድ ጠረገ፡፡ የባሃኡላህ የአንድነት እና የመንፈሳዊ እድሳት አስተምህሮዎች የባሃኢ እምነት መሰረት ናቸው፡፡
ምንም እንኳን ብዙዎች የእነዚህን ሁለት መለኮታዊ መልእክተኞች ታሪክ ገና ያልሰሙ ቢሆንም ፣ መንፈሳዊ እና ማህበራዊ ትምህርቶቻቸው ድምፅ በዓለም ዙሪያ ያስተጋባሉ። አስተምሮታቸውም በፍጥነት በመዛመቱ እና ታዋቂነት በማግኘቱ በፐርዢያ ባለስልጣናት እና የሀይማኖት መሪዮች ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጠመው። በዚህም ከ20,000 በላይ የሚሆኑት ተከታዮቹ ለተከታታይ በተደረጉ የጅምላ ግድያዮች ህይወታቸውን እንዲያጡ ተደረገ። ባብ እራሱ እ.ኤ.አ በ1850 ታቢሪዝ በሚባል ከተማ በህዝብ ፊት እንዲገደል ተደረገ።
ባብ እንዲሁም ሌሎች ነቢያቶች እንደሚመጣ የተነበዩለት የዚህ ዘመን የእግዚአበሔር መልዕክተኛ እርሱ መሆኑን ባሃኡላህ እ.ኤ.አ በ1863 አወጀ። የባሃኡላህ ተልእኮ የሰውን ልጅ በመንፈሳዊ ሁኔታ እንደገና ማንቃት እና ሁሉንም የዓለም ህዝቦች ምንም አይነት ድንበሮች ሳይገድቧቸው፣ ዘር እና ሀይማኖት ሳይለያቸው አንድ ማድረግ ነው። ባሃኡላህ አንድ አምላክ እንዳለ ያስተምራል፤ ይህ አምላክም በታሪክ ውስጥ እንደየዘመኑ ፍላጎት ተከታታይነት ያላቸው መለኮታዊ መምህራንን ልኳል። ከእነዚህም ውስጥ አብርሃም፣ ክሪሽና፣ ዞራስተር፣ ሙሴ፣ ቡድሃ፣ ኢየሱስ እና መሐመድ ይገኙበታል። ሃይማኖቶች የተለያየ ጊዜን ፍላጎቶች በሚያሟሉበት መልኩ የተለያዩ ቢመስሉም፣ ሁሉም ከአንድ ምንጭ፣ ከአምላክ የመጡ መሆናቸውን ያስረዳል። የሰው ልጆች አንድነት፣ የአምላክ አንድነትና የሀይማኖቶች አንድነት የባሃኡላህ መሰረታዊ አስተምህሮት ነው። ይህንንም የከበረ አላማ ልናሳካ የምንችልባቸውን የተለያዩ ፅሁፎችና መመሪያዎችን ገልፆልናል። የባሃኢ እምነት የቅዱሳን ጽሑፎች አስኳል ተብለው የሚታሰቡ ተከታታይ መጻሕፍትን፣ ጽላቶችን እና መልዕክቶችን ገልጿል። እነኚሀም ጽሁፎች 100 የሚያህሉ ጥራዞችን የሚያካተቱ ሲሆኑ የእግዚአብሔርን ተፈጥሮ፣ የሰው ልጆችን ሕልውና፣ የህይወትን ዓላማ፣ ሃይማኖታዊ ሕጎችን እና ሰላማዊ የሆነ፣ አንድነት ያለውና የበለጸገ ዓለም አቀፋዊ ማህበረሰብ ለመፍጠር ያለውን ራዕይ ይዘረዝረበታል።
ለዚህም ክቡር ዓላማ ባሃኡላህ ለ40 ዓመታት የእስር፣ የመከራና የስደት ሕይወትን አሳልፏል። የባሃኡላህ መታሰር የጀመረው በፋርስ በ1852 ሲሆን የባብ ደጋፊ ሆኖ ተይዞ፣ ተሰቃይቶ እና ከመሬት በታች በሚገኝ እስር ቤት ውስጥ ተጥሎ በነበረበት ጊዜ ነበር።
ስለባሃኡላህ ተጨማሪ ማወቅ ከፈለጉ ተጨማሪ ያነብቡ
Interesting blog? Like it on Facebook, +1 on Google, Tweet it or share this article on other bookmarking websites.