ባሃኦላህ ከጥንት ጀምሮ እንዲመጣ ይጠበቅ የነበረው የሰዎች አሰልጣኝ፤ መምህርና ከእርሱ በፊት ከነበሩት ሁሉ የላቀ የአንድ ግሩም ጸጋ መታያ መሆኑን እንዲሁም ወንዞች በውቅያኖሶች ውስጥ እንደሚዋሐዱ ሁሉ ከአሁን በፊት ለነበሩት ሃይማኖቶችም አዋሐጅ መሆኑን ደጋግሞ በግልጽ አስታውቋል። ነቢያት የተነበዩለትና ባለቅኔዎችም ያዜሙለት፤ ሰላምም በምድር ላይ፤ በጎ ፈቃድም በሰዎች መካከል ለተባለው ጊዜ መክፈቻና ለዓለም ሕብረት መነሻ የሚሆን መሠረት ጥሏል።
እውነትን በቅንነት መፈለግ፤ የሰው ልጅ አንድነት፤ በምሥራቅም ሆነ በምዕራብ የሚገኙ ሃይማኖቶች፤ ዘሮችና ሕዝቦች አንድነት፤ የሃይማኖትና የሳይንስ መስማማት፤ የጥላቻና የከንቱ እምነት መደምሰስ፤ የሴቶችና የወንዶች እኩልነት፤ የፍትህና የጽድቅ መቋቋም፤ አንድ ጠቅላይ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት መቋቋም፤ የቋንቋዎች አንድነት፤ የግዴታ ትምህርትን ማሰራጨት፤ እነዚህና ብዙዎችም እነዚህን የመሳሰሉትም ከ19ነኛው ምዕተ ዓመት የመጨረሻው አጋማሽ በፊት ከባሃኦላህ ብዕር በመፍለቅ ቁጥራቸው ላቅ ባለ መጻሕፍትና መልእክቶች የሰፈሩ ሲሆ ከነዚህ መልእክቶች ብዙዎቹ በዚያን ጊዜ ለነበሩት የዓለም ነገሥታትና ገዥዎች የተጻፉ ናቸው።
በመጠኑና በዓላማው ወደር የሌለው መልእክቱ በሚያስገርም አኳኋን ከዘመኑ ምልክትና ፍላጎት ጋር የተስማማ ነው። አዲሶቹ ችግሮች እንደአሁኑ እጅግ የጎሉና የተወሳሰቡ ሆነው ሰውን ከዚህ በፊት ከቶ አልገጠሙትም። ለእነዚህ ችግሮች ማሸነፊያ እንዲሆኑ የቀረቡት አስተያየቶች እንደዚህ ጊዜ በዝተውና ተፋላሽ ሆነው አያውቁም። የአንድ ታላቅ የዓለም መምህር አስፈላጊነት እንደዚህ ጊዜ ጠንክሮ አያውቅም። ምናልባትም ይህን የመሰለው መምህር የመምጣት ምኞት እንደአሁን ጊዜ የተጋነነና የተረጋገጠ ሆኖ ከቶ አያውቅም።
የትንቢቶች መፈጸም
አብዱል-ባሃ እንዲህ ሲል ጽፏል፦
“በወንጌል እንደተጻፈው ክርስቶስ ከሃያ ምዕተዓመት በፊት በተገለጸ ጊዜ ምንም እንኳን አይሁዶች እያለቀሱ ‘አምላክ ሆይ የመሢህን መምጣት አፋጥንልን’ እያሉ በየዕለቱ ሲጸልዩ የነበሩ መሆናቸው ቢታወቅም የእውነቱ ፀሐይ በመጣ ጊዜ ታላቅ ጠላቶች ሆነው ተነስተውበት በመጨረሻውም ክፉው ብኤልዜቡብ በሚል መታወቂያ ጠርተውት ያን መለኮታዊ መንፈስ፤ ያን የእግዚአብሔር ቃል ሰቀሉት። አይሁዶች እንደሚሉት ክርስቶስን የሰቀሉበት ምክንያት እንደሚከተለው ነው፦ በኦሪት መጻሕፍት ትርጉም መሠረት የክርስቶስን መገለጽ አንዳንድ ምልክቶች እንዲያረጋግጡለት ስለሚያስፈልግ እነዚህ ምልክቶች ሳይፈጸሙ እኔ መሲህ ነኝ የሚል ሁሉ አታላይ ነው። ከምልክቶቹም አንዱ መሲህ ካልታወቀ ቦታ ይመጣል የሚል ሲሆን ይህ ሰው ከናዝሬት መምጣቱን ሁላችንም እናውቃለን። ከናዝሬት ደግሞ መልካም ነገር ሊመጣ ይችላልን? ሦስተኛው ምልክት ደግሞ በኃይልና በሥልጣን፤ ማለት ሠይፍን በእጁ ጨብጦ ይገዛል የሚል ሲሆን ይህ መሢህ በትር እንኳን አልነበረውም። ከሌሎች ምልክቶችና መለያዎቹ አንዱ ደግሞ በዳዊት ዙፋን ላይ ተቀምጦ የዳዊትን መንግሥት ያቋቁማል የሚል ነው። ይህ ሰው እንኳንስ በዳዊት ዙፋን ላይ ሊቀመጥና የሚያርፍበት ምንጣፍ እንኳን አልነበረውም። ሌላው ምልክት ደግሞ የእግዚአብሔር መሢህ መጥቶ የኦሪትን ሕግ ያጸናል የሚለው ነበር። ዳሩ ግን ነቢይም ቢሆንና ብርቱ ተአምራትም ቢሠራ የቀዳሚትን ቀን ከሻረ ለሞት የተገባ ነው ተብሎ ነበር። ይህ ሰው ግን በድፍረት በኦሪት ያለውን ቃል የቀዳሚትን ቀን ሻረ። ሌላው ምልክት ደግሞ በዚህ ሰው ዘመነ መንግሥት ርትዕ ከልክ ያለፈ ከመብዛቱ የተነሣ በጎ አድራጎት ከሰዎች ተርፎ ወደ እንስሳትም ስለሚያልፍ እባብና አይጥ አንድ ጉድጓድ ይጋራሉ። ንስርና ድርጭት ባንድ ጎጆ ይተኛሉ። አንበሳና ድኩላ ባንድ ሜዳ ይሰማራሉ። ተኩላና የፍየል ግልገል ከአንድ ምንጭ ይጠጣሉ የሚለው ሲሆን በሱ ዘመን ፍርድ በመጉደሉና ጭካኔ ከመብዛቱ የተነሣ እሱን እራሱንም ሰቀሉት! ሌላው ምልክት ደግሞ አይሁዶች ይበለጽጋሉ፤ የዓለምን ሕዝቦች ሁሉ ድል ይነሣሉ የሚለው ሲሆን በእሱ ዘመን ግን እጅግ በተዋረደ ሁኔታና በሮም ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ባርነት ሥር ይኖሩ ነበር። ስለዚህ በኦሪት እንደተሰጠው ተስፋ ይህ መሢህ ነው ለማለት ይቻላልን?
“ምንም እንኳን በኦሪት የተሰጠው ተስፋ ለዚህ ለእግዚአብሔር መንፈስ ቢሆንም በዚህ ዓይነት መንገድ የእውነትን ፀሐይ ካዱት። የእነዚህ ምልክቶች ሚስጢር ስላልገባቸው አይሁዶች የእግዚአብሔርን ቃል ሰቀሉት። የኦሪት ቃል የተነገረው በምሳሌ ስለሆነ አይሁዶች በገመቱት መንገድ ሳይሆን በክርስቶስ መገለጽ ምልክቶች ሁሉ ተፈጽመዋል ሲሉ በሃኢዎች ያምናሉ። ለምሳሌ ከምልክቶቹ አንዱ ንጉሥነት ስለሆነ የክርስቶስን ንጉሥነት ለጥቂት ጊዜ ደምቆ እንደትቢያ በኖ እንደሚጠፋው እንደናፖሊዎን ያለ ንጉሥነት ሳይሆን ዘለዓለማዊና ሰማያዊ መንግሥት በመሆኑ ይህ ምልክት ተፈጽሟል ሲሉ በሃኢዎች ያምናሉ። የክርስቶስ መንግሥት ከተጀመረ ሁለት ሺ ዓመት ሆኗል። እንዲያውም ዓለም ሳይፈጠር የነበረና እስከ ዛሬ ድረስም በመንግሥቱ ላይ ያለ እስከ ዘለዓለምም ከዙፋኑ የሚቀመጥ ቅዱስ ስሙም ለዘለዓለም የሚኖር ነው። በዚሁ መንገድ ሌሎቹ ምልክቶችም ሁሉ ተፈጽመዋል። ነገር ግን አይሁዶች ምሥጢሩ አልገባቸውም። ምንም እንኳ ክርስቶስ መለኮታዊ ግርማን ተጎናጽፎ ወደዚህ ዓለም ከመጣ ሁለት ሺህ ዓመታት ያህል ቢያልፍም አይሁዶች የመሢህን መምጣት እስካሁን በመጠባበቅ ላይ በመሆናቸው ራሳቸውን እውነተኛ፤ ክርስቶስን ሃሰተኛ አድርገው ይገምታሉ።” (አብዱል-ባሃ ለዚህ ምዕራፍ ያዘጋጀው ጽሑፍ።)
አይሁዶች ክርስቶስን ጠይቀውት ቢሆን ኖሮ ስለራሱ የተጻፈውን ትንቢት ሚስጢር ባስረዳቸው ነበር። ስለዚህ ይህን ምሳሌ አድርገን በመጨረሻው ቀን ስለሚመጣው መምህር እስከፍጻሜው ዘመን ድረስ ሚስጢሩ የተዘጋና የታሸገ መሆኑን ተገንዝበን ‘የተዘጋውንና የታሸገውን’ ከፍቶ በታላቁ ሙዳይ ውስጥ ምስጢር ለማየት የሚችለው እውነተኛው መምህር ብቻ ስለሆነ ባሃኦላህ ራሱ ስለነዚህ ትንቢቶች ሁሉ አተረጓጎም የጻፈውን እንመልከት።
ባሃኦላህ የጥንት ትንቢቶችን ትርጉም በመስጠት ብዙ ጽፏል። ነገር ግን በዚሁ በጻፈው ብቻ ነቢይ መሆኑ እንዲረጋገጥለት አልፈቀደም። የማየት ኃይል ያላቸው ሁሉ ፀሐይ ለራሷ ምስክር መሆኗን ይረዳሉ። ፀሐይ በወጣች ጊዜ ብርሃን ትሰጣለች የሚል ጥንታዊ ማረጋገጫ አያስፈልግም። የእግዚአብሔር መልእክተኛም መገለጽ እንደዚሁ ነው። ጥንታዊ ትንቢቶች ሁሉ ጠፍተው ቢሆን ኖሮ መንፈሳዊ ስሜታቸው ንቁ ለሆኑት ሁሉ ለእርሱነቱ ራሱ ሰፊ ማስረጃ ሊሆናቸው ይችል ነበር።
የነቢይነት ማስረጃዎ ማንም ንግግሩንና መለዮዎቹን ሁሉ ሳይመረምር በጭፍን እንዲቀበለው ባሃኦላህ አላዘዘም። እንዲያውም ሰዎች ትዕዛዙን ሳይመረምሩና እውነተኛነቱን ሳይረዱ በጭፍን እንዳይቀበሉ በጥብቅ ከማስገንዘቡም በላይ እያንዳንዱ ሰው እውነቱን አጣርቶ ለማወቅ እንዲችል፤ ጆሮዎቹን እንዲከፍትና ያለፍርሃት በነፃነት ማመዛዘኛውን እንዲገለገልበት ሲል ይህን ትእዛዝ በትምህርቱ መቅድም ላይ አስፍሮት ይገኛል። መርምሮ መረዳትን የእያንዳንዱ ሰው ግዴታ ከማድረጉም በላይ የነቢይነቱ ዋና ማስረጃ የሆነውን እሱ ራሱ የሰውን ልጅ ባሕርይና ኑሮ በመለወጥ ኃይል ያለውን ቃሉንና ሥራውን አልሸሸገም።
ባሃኦላህ ለነቢይነቱ ማስረጃ እንዲሆኑ ሲል የሰጣቸው ምልክቶች ከሱ በፊት የነበሩት ታላላቅ ቀደምት ነቢያት ከሰጡዋቸው ማስረጃዎች ጋር አንድ ናቸው።
ለምሳሌ ሙሴ እንዲህ ሲል ጽፏል፦
“ይህች ምልክት ትሁንልህ። ያ ነቢይ በእግዚአብሔር ስም በተናገረ ጊዜ ያው የተናገረው ባይደረግ ባይመጣም። ይህ ነው እግዚአብሔር ያልተናገረው ነገር። ያ ነቢይ በድፍረቱ የተናገረው እንጂ። እርሱን አትፍራው። ” (ኦሪት ዘዳ. 18፡ 22)
ክርስቶስም ማስረጃዎቹን በግልጽ አስረድቶ እነዚህ ማስረጃዎች የሱ የራሱ መታወቂያዎች መሆናቸውንም ሲያመለክት እንዲህ ሲል ጽፏል።
“ተጠንቀቁ ከሃሰተኞች ነቢያት የበግ ለምድ ለብሰው የሚመጡባችሁ በውስጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኩላዎች ናቸው። ከፍሬያቸው ታውቁዋቸዋላችሁ ከሾህ ወይን ይለቀማልን? ከአሜኬላስ በለስ እንዲሁም መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ታፈራለች ክፉም ዛፍ ክፉ ፍሬ ታፈራለች። መልካም ዛፍ ክፉ ፍሬ ማፍራት አይቻላትም። ... መልካም ፍሬ የማታፈራ ዛፍ ሁሉ ትቆረጣለች ወደሳትም ትጣላለች። ” (ማቴዎስ 7፡15-20)
ልደቱና የወጣትነቱ ዘመን
ባሃኦላህ ወይም ክብረ-አምላክ በሚል ስያሜ የታወቀው ቫዚር ወይም ሚንስትር ደ ኤታ የነበረው የኑር ሚርዛ አባስ የበኩር ልጅ ነበር። ቤተ ሰቡ ሀብታምና የታወቀ ከመሆኑም በላይ ብዙዎቹ ዘመዶቹ በኢራን መንግሥት ውስጥ ብዙ ከፍተኛ የሲቪልና የወታደር ማዕረግ ተሰጥቷቸው መንግሥቱን አገልግለዋል። ባሃኦላህ እ.ኤ.አ. ኅዳር 12 ቀን 1817 ጎህ ሲቀድ በኢራን ዋና ከተማ በቴህራን ተወለደ። እርሱም ትምህርት ቤት ወይም ኮሌጅ ገብቶ አልተማረም። ነገር ግን እቤት ውስጥ ትንሽ ትምህርት ተሰጥቶታል። እንደዚሁም ሆኖ ገና ከልጅነቱ ታላቅ ጥበብና ዕውቀት ይታይበት ነበር። ገና ወጣት ሳለ አባቱ ስላረፈ የታናሽ ወንድሞቹና እህቶቹ ጥበቃና ሰፊው የቤተ ሰብ ንብረት አስተዳደር በርሱ ትከሻ ላይ ወደቀ። አብዱል-ባሃ እንዲህ አለ፦
“ከልጅነቱ ጀምሮ እጅግ በጣም ደግና ለጋስ ነበር። አብዛኛውን ጊዜውን በየመስኩና በአትክልት ሥፍራ ማሳለፍ ይወድ ነበር። ለሁሉም የሚሰማ ሰውን ወደርሱ በጣም የመሳብ ኃይል ነበረው። ሁልጊዜ ብዙ ሰዎች ወደርሱ ይሰበሰቡ ነበር። ሚኒስትሮችና የአደባባይ ሰዎች ሲከቡት ሕፃናትም በጣም ይወዱት ነበር
ገና የአሥራ ሦስትና የአሥራ አራት ዓመት ወጣት ሳለ በዕውቀቱ በጣም የታወቀ ነበር። በማንኛውም ጉዳይ ላይ ለመነጋገርና ለቀረበለት ለማንኛውም ጥያቄ መልስ ለመስጠት ችሎታ ነበረው። በትልልቅ ስብሰባዎች ላይ ከኡላማዎች (የእስላም ሃይማኖት ሊቃውንት) ጋር እየተነጋገረ ብዙ የተወሳሰቡ ሃይማኖት ነክ የሆኑትን ጥያቄዎች ያብራራላቸው ስለነበረ ሁሉም በታላቅ አድናቆት ያዳምጡት ነበር።
“ባሃኦላህ ሃያ ሁለት ዓመት ሲሆነው አባቱ ስላረፈ ምንም እንኳንም በዚያን ጊዜ በኢራን እንደተለመደው መንግሥቱ የአባቱን ቦታ ቢሰጠውም ባሃኦላህ ሹመቱን አልተቀበለም። ይህን በሰማ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደዚህ አለ። ‘ተውት! ይህ ማዕረግ ለእርሱ ያነሰ ነው። ከዚህ የበለጠ ታላቅ ዓላማ አለው። ምንም እንኳን ልረዳው ባልችል ከዚህ እጅግ በጣም ከፍ ላለ ሥራ የታጨ ለመሆኑ እርግጠኛ ነኝ። ሃሣቡ ከኛ የተለየ ነውና ተውት!’”
ባቢ በመሆኑ እንደታሠረ
እ.ኤ.አ. በ1844 ዓ.ም. ባብ መልእክቱን ሲያውጅ የሃያ ሰባት ዓመት ጎልማሳ የነበረው ባሃኦላህ ያለፍርሃት በድፍረት ሃይማኖቱን ሲያስፉፉ ከነበሩት ምዕመናን እንደ አንዱ ሆኖ አዲሱን ሃይማኖት በቆራጥነት ደገፈ።
በዚሁም እምነት ምክንያት ከዚህ በፊት ሁለት ጊዜ በእሥራት ከመቀጣቱም በላይ አንድ ጊዜ የውስጥ እግሩን በመገረፍ ስቃይ ደርሶበታል።
ወደ ባግዳድ መጋዝ
ባሃኦላህና ጓደኞቹ ከዚህ እሥር ቤት በአሰቃቂ ሁኔታ ለአራት ወራት ቢቆዩም ከፍ ያለ የመንፈስ ብርታትና ደስታ ነበራቸው። በየቀኑ አንድ ወይም ይበልጥ ከመሃከላቸው ተወስዶ ይሰቃያል ወይም ይገደላል። የቀሩት ደግሞ ቀጥሎ የእነሱ ተራ መሆኑ ይታወሳቸዋል። ከመካከላቸው አንዱ ሊገደል ሲጠራ ያ ስሙ የተጠራው በደስታ ብዛት ይጨፍራል፥ የባሃኦላህን እጆች ይስማል፤ ሌሎቹንም ምዕመናን ያቅፋል። ከዚያም ለመገደያ ወደተዘጋጀው ሥፍራ በደስታ ይሮጣል።
ሁለት ዓመት በምድረ በዳ
ባግዳድ ገብተው አንድ ዓመት ብቻ ከቆዩ በኋላ ብቻውን አንድ ቅያሪ ልብስ ብቻ ይዞ ወደ ሱሌማንየህ ምድረ በዳ ተሰደደ። ስለዚህ ጊዜ ‘ኢቃን’ በሚባለው መጽሐፍ የሚከተለውን ጽፏል፦
“እዚህ አገር ገብተን ጥቂት እንደቆየን ሊደረጉ ስለታቀዱት ነገሮች አንዳንድ ምልክቶች እንዳገኘን እነዚህ ነገሮች ከመሆናቸው በፊት ገለል ለማለት ወሰንን። ወደ ምድረ በዳ ተሰደን እዚያ ከሰው ተለይተን ብቻችንን ለሁለት ዓመት ፍጹም የብቸኝነት ኖሮ ኖርን። ከዓይናችን የሥቃይ እንባ ይዘንብ ነበር፥ በቆሰለው ልባችንም ውስጥ አሰቃቂ የጭንቅ ውቅያኖስ ተንቀሳቀሰ። ብዙ ጊዜ የዕለት እራት አጥተን ተራብን፥ ለብዙ ቀናትም ሰውነታችን ዕረፍት አላገኘም። ነገር ግን ምንም እንኳን የሰቀቀን ወጨፎ ቢገርፈንና ያለማቋረጥ ጭንቅ ቢደርስብንም ነፍሳችን በፍጹም ደስታ ተሞላች። ሰውነታችን በሙሉ በቃላት ሊገለጽ የማይቻል ደስታ ታየበት። ለዚህም መላ ሰውነቴ በእጁ ውስጥ የሆነው አምላክ ምስክሬ ነው! በብቸኝነታችን የማንም ሰው ጉዳት ወይም ጥቅም እንዲሁም ጤንነት ወይም ሕመም አይታወቀንም ነበር። ስለዚህች ዓለምና በውስጧም ስላሉት ነገሮች ሁሉ ረስተን ብቻችንን ከመንፈሳችን ጋር እንወያይ ነበር። ሆኖም መለኮታዊ ዓላማ የማንም አዕምሮ ሊረዳው ከሚችለው በላይ መሆኑና የትዕዛዙም ኃያልነት ከደፋር ሰብአዊ ሴራ የበለጠ መሆኑ አልገባንም ነበር። ከርሱ ወጥመድ ማንም ሊያመልጥ አይችልም፥ ለፈቃዱም ያልታዘዘች ነፍስ መድህን ልታገኝ አትችልም። ስደታችን መመለስን፥ መለያየታችን ተመልሶ መገናኘትን ያላሰበና ያልተመኘ ለመሆኑ ቀጥተኛው አምላክ ምስክር ነው! የስደታችን ዋናው ዓላማ በምዕመናኑ መካከል የመለያየት ምክንያት፥ ለወዳጆቻችን የጸብ ምንጭ፥ የማንም ሰው የጉዳት መሣሪያና የኃዘን ምክንያት እንዳንሆን ነበር። ከዚህ የተለየ ሌላ ዓላማ፥ ከዚህ የተለየ ምኞት አልነበረንም። ነገር ግን ከረቂቅ ምንጭ ታዘን የመመለሻችን ሰዓት እስከደረሰ ድረስ እያንዳንዱ ሰው በራሱ መንገድ ብቻ እየተመራ አጉል ምኞቱን ይከተል ነበር። እኛም በፈቃዱ ተመርተን ትዕዛዙን ፈጸምን።
“ተመልሰን ያየነውን ነገር ለመጻፍ የሚችል ብዕር አይገኝም! በምድረ በዳ በቆየንበት በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ጠላቶቻችን ያለማቋረጥና ያለአንዳች ፋታ ሊያጠፉን ሞከሩ። ለዚህም ሁሉም ምስክር ነው።” (ኢቃን ገጽ 251
የሙላዎች መቃወም
ከስደቱ ከተመለሰ በኋላ ዝናው በጣም ስለገነነ ሰዎች እርሱን ለማየትና ትምህርቱንም ለማዳመጥ ከያለበት ወደ ባግዳድ ይጎርፉ ነበር። አይሁዶች፥ ክርስቲያኖች፥ ዞሮአስተሪያኖችና እንዲሁም እስላሞች ስለአዲሱ መልእክት ለማወቅ ፍላጎት አደረባቸው። ሙላዎች (የእስላም ሃይማኖት ሊቆች) ግን የጥላቻ መንፈስ ስለአደረባቸው እርሱን ለማጥፋት ያለማቋረጥ ሴራ ያደርጉ ነበር። ከዕለታት አንድ ቀን ከመካከላቸው አንዱ እርሱ ዘንድ ሄዶ እንዲያነጋግረውና አንዳንድ ጥያቄዎች እንዲያቀርብለት ላኩት። መልእክተኛው ባሃኦላህ ለጥያቄዎቹ የሰጠው መልስ ትክክለኛና ምንም እንኳን በትምህርት ያልተገኙ ቢሆንም እውቀቱ በጣም አስገራሚ በመሆኑ በእውቀትና በማስተዋል ባሃኦላህን የሚስተካከለው እንደሌለ መመስከር ግድ ሆነበት። ነገር ግን ስለትንቢቱ እውነተኝነት የላኩት ሙላዎች አጥጋቢ ማስረጃ እንዲያገኙ ባሃኦላህ አንዳንድ ተአምራቶችን እንዲያሳይ ጠየቀ። ባሃኦላህም ሙላዎቹ የፈለግቱን ተአምር ተስማምተውበት፣ ተአምሩም ከተደረገ በኋላ መቃወማቸውን ትተው ስለመልእክቱ እውነተኝነት የሚያረጋግጥ በጽሑፍ የሆነ ውል ካቀረቡለ የጠየቁትን ተአምር የሚያሳይ መሆኑንና ተአምሩም ካልተፈጸመ ግን በሐሰተኛነት እንዲፈረድበት የፈቀደ መሆኑን ገለጸለት። ሙላዎቹ እውነት ፈላጊዎች ቢሆኑ ኖሮ ዕድላቸው አሁን ነበር። ነገር ግን ሐሳባቸው ከዚህ የተለየ ነበር። በእውነትም ሆነ በሐሰት መንገድ ለእነርሱ የሚያደላ ውሳኔ ለማግኘት ፈለጉ። እውነትን በመፍራት ከእርሱ ጋር ለመቋቋም አልፈቀዱም። ሆኖም እንደዚህ ያለው ድፍረት ይህ የተጨቆነ የሃይማኖት ክፍል የሚደመስስ አዳዲስ ብልሃት እንዲፈጥሩ አነቃቃቸው። በባግዳድ ውስጥ ይኖር የነበረው የኢራኑ ዋና ቆንሲል እነርሱን በመርዳት ባሃኦላህ የእስላምን ሃይማኖት ከመቼውም ይበልጥ በመጉዳት ላይ መሆኑንና በኢራን ውስጥ ጉዳትን ለማስከተል የሚችል ስለሆነ አሁንም ራቅ ወዳለ ቦታ እንዲጋዝ አስፈላጊ ነው የሚል መልእክት እየደጋገመ ለሻሁ ላከ።
በእስላም ሙላዎች አነሳሽነት የኢራንና የቱርክ መንግሥታት እንቅስቃሴውን ለመደምሰስ ጥረታቸውን አንድ ላይ ባደረጉበት በዚህ በአደገኛ ጊዜ ባሃኦላህ ለተከታዮቹ ማጽናኛ መመሪያ በመጻፍና በማነቃቃት ሳይሸበር መኖር ልማዱ ነበር። አብዱል-ባሃ “ኅቡአተ ቃላት” የሚባለው መጽሐፍ በዚህ ጊዜ መጻፉን ይናገራል። ባሃኦላህ ብዙ ጊዜ በጤግሮስ ወንዝ ዳር ይንሸራሸር ነበር። ከዚያም በደስታ ተሞልቶ ሲመለስ በኃዘንና በችግር ለተሞሉት ለብዙ ሺ ለሚቆጠሩት ልቦች መድኅን የሚያስገኙትንና መንፈስን የሚማርኩትን ቅኔዎች ይጽፍ ነበር። ለብዙ ዓመታት በእጅ የተጻፉ ጥቂት የኅቡአተ-ቃላት ቅጂዎች ብቻ ሲገኙ እነዚህ ሃይማኖቱን በሚቃረኑት ሰዎች እጅ እንዳይወድቁ ይጠበቁ ነበር። አሁን ግን ይህ አነስተኛ መጽሐፍ ከባሃኦላህ ጽሑፎች ሁሉ በጣም የታወቀና በመላ ዓለም የሚነበብ ነው። ከታወቁት የባሃኦላህ ጽሑፎች አንዱ የሆነው ደግሞ “ዘ ቡክ ኦፍ ኢቃን” (የእርግጠኝነት መጽሐፍ) የተባለው ነው። ይህም መጽሐፍ የተጻፈው የባሃኦላህ በባግዳድ ኑሮ ወደማለቁ በተቃረበበት ወቅት (እ.ኤ.አ. 1862-1863 ዓ.ም.) ነበር።
በባግዳድ፥ ሪዝቫ በተባለው ቦታ መልእክቱን እንዳወጀ
ከብዙ ድርድር በኋላ የቱርክ መንግሥት በኢራን መንግሥት ጠያቂነት ባሃኦላህን ወደ ኮንስታንቲኖፕል የሚጠራ መልእክት አስተላለፈ። ይህ ዜና እንደደረሳቸው ተከታዮቹ በጣም ስጋት አደረባቸው። ለረጅሙ ጉዞ ዝግጅት በመደረግ ላይ ሳለ ምዕመናኖቹ ወደ ተወዳጁ መሪያቸው ቤት ይጎርፉ ስለነበር ቤተሰቡ ለአሥራ ሁለት ቀን ከከተማው ውጭ ወደሚገኘው ወደ ናጂቭ ፓሻ የአትክልት ቦታ ሄደው ሰነበቱ። ከእነዚህ ከአሥራ ሁለቱ ቀኖች በመጀመሪያው (እ. ኤ. አ. በሚያዝያ 21 ቀን እስከ ግንቦት 3 ቀን በ1863 አ.ም. ባብ፥ መልእክቱን ካወጀበት ከአሥራ ዘጠኝ ዓመት በኋላ) ባብ ስለመምጣቱ የተነበየለት - በእግዚአብሔር የተመረጠና ነቢያት ሁሉ የተነበዩለት - እርሱ መሆኑን የሚያበስር አስደሳች ዜና ለአብዛኛዎቹ ተከታዮቹ ገለጸላቸው። ይህን የማይረሳ አዋጅ የታወጀበትን ሥፍራ ባሃኢዎች “የሪዝቫን የአትክልት ቦታ” ብለው ሰየሙት። ባሃኦላህም እዚህ የሰነበተባቸው አሥራ ሁለት ቀናት “የሪዝቫን ክብረ በዓል” ተብለው እየተጠሩ ባሃኢዎች በየዓመቱ ያከብሩዋቸዋል። ባሃኦላህ እዚያ በሰነበተባቸው ቀናት በማዘን ወይም በመበሳጨት ፈንታ በጣም ትልቅ ደስታ፥ ክብርና ኃያልነት ይሰማው ነበር። ተከታዮቹም በጣም በመደሰት የመንፈስ ንቃት ተሰማቸው። ብዙ ሕዝብ ወደእርሱ ተሰብስቦ አክብሮቱን ገለጸለት። የባግዳድ አገረ ገዥና በከተማው የሚኖሩ ታላላቅ ሰዎች መንገደኛውን እስረኛ በአክብሮት ሊሰናበቱ መጡ።
ኮንስታንቲኖፕልና ኤድሪያኖፕል
ወደ ኮንስታንቲኖፕል የተደረገው ጉዞ ከሦስት እስከ አራት ወራት ፈጀ። ባሃኦላህ ቤተሰቦቹና ሃያ ስድስት ደቀ መዝሙሮቹ አብረውት ነበር። ኮንስታንቲኖፕልም ከደረሱ በኋላ በአንዲት ትንሽ ቤት ውስጥ በመታጎር ታሠሩ። ጥቂት እንደቆዩ የተሻለ መኖሪያ አገኙ። ነገር ግን ከአራት ወራት በኋላ እንደገና ወደ ኤድሪያኖፕል ተጋዙ። ወደ ኤድሪያኖፕል ያደረጉት ጉዞ ምንም እንኳን ጥቂት ቀናት ቢፈጅም እስካሁን ድረስ ከአደረጉት ጉዞ ሁሉ በጣም አስቸጋሪ ነበር። ከባድ በረዶ ይጥል ስለነበርና ለዚሁም የሚረዳቸው ልብስና ምግብ ስላልነበራቸው ሥቃያቸው እጅግ የበዛ ነበር። በኤድሪያኖፕል ባሳለፉት በመጀመሪያው ክረምት ባሃኦላህና አሥራ ሁለት የቤተሰቡ አባላት ምንም ምቾት በሌለባት በተባይ በተሞላች አንዲት ትንሽ ባለሦስት ክፍል ቤት ውስጥ ኖሩ። በጸደይ ወራት ግን ትንሽ ሻል ያለ መኖሪያ ተሰጣቸው። ኤድሪያኖፕል ውስጥ ከአራት ዓመት ተኩል በላይ ኖሩ። እዚያም ባሃኦላህ ማስተመሩን ቀጥሎ የምዕመናን ቁጥር እየበዛ ሄደ። መልእክቱን በይፋ ካወጀ በኋላ አብዛኞዎቹ ባቢዎች ተቀብለውት ‘ባቢዎች’ በመባል ፈንታ ‘ባሃኢዎች’ ይባሉ ጀመር። ጥቂቶች ግን በባሃኦላህ ወንድም በሚርዛ ያህያ መሪነት እርሱን አጥብቀው በመቃወምና ከቀድሞ ጠላቶቻቸው ከሺአይዎች ጋር እንደገና በማበር ሴራ እያደረጉ እርሱን ለማጥፋት ይሞክሩ ጀመር። በዚህም ምክንያት ታላቅ ብጥብጥ ስለተነሳ የቱርክ መንግሥት ባሃኢዎችን ባቢዎችንም ከአድሪያኖፕል እንዲወጡ አዞ ባሃኦላህን በፓለስቲን ውስጥ ወደሚገኘው ወደ አቆር ሲያግዝ ሚርዛ ያህያንና ተከታዮቹን ደግሞ ወደ ሳይፕረስ (ቆጵሮስ) ሰደደ።
በዚህ ጊዜ ባሃኦላህ ለቱርክ ሱልጣን፥ ለብዙዎቹ ለታላላቅ የአውሮፓ ነገሥታት፥ ለሮማው ሊቀ ጳጳስ፣ እና ለኢራኑ ሻህ ታዋቂ መልእክተቶቹን አስተላለፈ። ቀጥሎም “ኪታቢ አቅዳስ” (እጅግ ታላቁ መጽሐፍ) ውስጥ ለሌሎች ነገሥታት፥ ለአሜሪካ ገዢዎችና ፕሬዚዳንቶች፥ በአጠቃላይ ለሃይማኖት መሪዎች እና ለሰው ልጅ በሙሉ፥ መልእክቶቹን ላከ። በእነዚህ መልእክቶቹ ስለእውነተኛ ሃይማኖት፥ ስለትክክለኛ መንግሥትና ስለኢንተርናሽናል ሰላም መመስረት በጣም እንዲደክሙ የታወቁትን ደብዳቤዎቹን ጻፈላቸው።
በዚሁ መልእክት ውስጥ ባሃኦላህ በራሱ ላይ ስለደረሰበት ሥቃይና ስለምኞቱ በጣም ልብ የሚነካ ማብራሪያ እንደሚከተለው ጽፎአል፦
“ንጉሥ ሆይ! በእግዚአብሔር መንገድ ስጓዝ ዓይን ያላየውና ጆሮ ያልሰማው ሥቃይ ደርሶብኛል። ወዳጆች ከድተውኛል፤ መንገዶች አስቸጋሪ ሆነውብኛል፤ የደኅንነት ምንጭ ደርቆብኛል፥ የምቾትም ሜዳም ተለብልቦብኛል። ስንት ሥቃይ ደርሶብኛል! ለወደፊትስ ስንት ይደርስብኝ ይሆን! ወደ ኃያሉና ወደ ለጋሱ ሳመራ ከኋላዬ እባብ ይከተለኛል። ከዓይኖቼ በሚዘንበው እንባ መኝታዬ ራሰ። ግን ሃዘኔ ለራሴ አይደለም። በእውነት እላችኋላሁ! ለአምላክ ፍቅር ራሴን ለጦር አሳልፌ ለመስጠት እፈቅዳለሁ። በዛፍ አጠገብ በማልፍበት ጊዜ በልቤ “አንተ ዛፍ! በስሜ በተቆረጥክና በጌታዬ ስም ሰውነቴ አንተ ላይ በተሰቀለ!” ብዬ ሳላዋየው ያለፍኩበት ዛፍ የለም። አዎን! ምክንያቱም የሰው ልጆች በስካራቸው ወደ ጥፋት ጎዳና ሲያመሩ እያየሁና ይህንንም ሳያውቁ በመቅረታቸው ነው። አምላካቸውን ረስተው ምኞታቸውን ብቻ ከፍ ከፍ በማድረግ የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ እንደፌዝ፥ እንደጨዋታና እንደቀልድ የወሰዱት ይመስላል። ይህንንም በማድረጋቸው ደህና የሠሩና በደህንነት ምሽግ ውስጥ የተጠለሉ መስሏቸዋል። ነገሩ እነሱ እንደሚያስቡት አይደለም፤ ዛሬ የካዱትን ነገ ሲፈጸም ያዩታልና።
“ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከተጋዝንበት ከኤድሪያኖፕል ወደ አቆር ወህኒ ቤት መዛወራችን ነው። በዝና እንደሚሰማው ይህ ከተማ ከዓለም ከተሞች ሁሉ የተወረረ በሚመስል፥ ለማየት በጣም የሚቀፍ፥ የአየሩ ሁናቴ ለሰው የማይስማማና ውሃውም በጣም የገማ ነው። ለጉጉቶች የተሠራ ከተማ ይመስል ከእነርሱ ጩኸት በስተቀር ሌላ ድምጽ አይሰማበትም። በዚህ ውስጥ ይህን አገልጋይ ለማሠር አስበዋል። የደግነትንም በሮች በፊታችን ላይ ዘግተው በዚህች ዓለም ላይ በቀሩን ቀናት ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ሊነፍጉን ፈለጉ። በድካም ብዛት አቅመ ቢስ ብሆንና ረሃብ ቢያጠቃኝ፥ መኝታዬ አለት ድንጋይ ቢሆንና ደባሎቼም የበረሃ አውሬዎች ቢሆኑ እንኳን ወደኋላ አላፈገፍግም። ነገር ግን እኔም በእምቅድመ ዓለሙ ንጉሥ በዓለሞች ፈጣሪና ኃያል በሆነው አምላክ ስም እንደታጋሾቹና እንደማያወላውሉ መንፈሰ ጠንካራ እሆናለሁ። በማንኛቸውም ሁኔታ ለአምላክ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። እርሱ ኃያሉና ቸሩ፥ ሰዎች ፊታቸውን በፍቅር ወደርሱ እንዲመልሱ እንዲያደርጋቸው ለጸጋው ተስፋ እናደርጋለን። (እርሱ ነውና ከሁሉ የላቀ!) ... በዕውነቱ እርሱ የለመነውን የሚሰማና ስሙንም ለሚጠራው ቅርብ ነው። እኛም ይህን የሥቃይ ጨለማ ለቅዱሳት ገላ ጋሻ አድርጎ ከሹሉ ሰይፍና ከሰላው ጎራዴ እንዲጠብቃቸው እንለምነዋለን። ብርሃኑ የበራውና ምስጋናውም ሳያቋርጥ ሲያበራ የኖረው በመከራ ብዛት ነው። ይህም ከጥንት ጀምሮ ባለፉት ዘመናት የርሱ ዘዴ ነው።”
በአቆር እስር ቤት
አቆር በዚያን ጊዜ ከቱርክ ግዛት ውስጥ ከያለበት ከባድ ወንጀል የሠሩ ሰዎች የሚላኩበት የእሥረኞች ከተማ ነበረች። ባሃኦላህ ከሰማንያ እስከ ሰማንያ አራት ከሚሆኑ ሴቶችና ሕፃናት ካሉበት ተከታዮቹ ጋር በጣም አስቸጋሪ ከሆነው ከባሕር ጉዞ በኋላ እዚያ እንደደረሰ በወታደሮቹ ሠፈር ውስጥ ታሠረ። ቦታውም በጣም ቆሻሻና ተስፋ የሚያስቆርጥ ከመሆኑም በላይ መኝታ ወይም ለምቾት የሚሆን አንዳች ነገር አልነበረም። የሚታደለውም ምግብ አነስተኛና በጣም የተበላሸ ስለነበረ ከጊዜ በኋላ እሥረኞቹ የራሳቸውን ምግብ እንዲገዙ ፈቃድ ለመኑ። ለመጀመሪያው ጥቂት ቀናት ሕፃናት ያለማቋረጥ ያለቅሱ ስለነበረ ለመተኛት አይቻልም ነበር። ወባ፤ ተቅማጥና እንዲሁም ሌላ ዓይነት በሽታዎች ስለተነሱ ከመካከላቸው ሁለት ሰዎች ብቻ ሲቀሩ (እነሱም በኋላ ታመሙ) የቀሩት በሙሉ ታመሙ። ሶስቱ በበሽታ ሲሞቱ በተረፉትም ላይ የደረሰውን ሥቃይ ለመግለጽ ቃላት አይገኝለትም። ይህ ጽኑ እሥራት ለሁለት ዓመት ቆየ። በዚህ ጊዜ እየተጠበቁ በየቀኑ ምግብ ለመግዛት ከሚሄዱት ከአራት በሃኢዎች በስተቀር ሌሎቹ ከእሥር ቤት ደጃፍ እንዲወጡ አይፈቀድላቸውም ነበር።
በወታደሮቹ ሠፈር በታሠሩበት ጊዜ ጠያቂዎች በጥብቅ ይከለከሉ ነበር። ብዙዎች የኢራን በሃኢዎች ተወዳጅ መሪያቸውን ለማየት ከአገራቸው ድረስ በእግራቸው ሲመጡ በከተማው ክልል ውስጥ እንኳን እንዳይገቡ ተከለከሉ። እነርሱም ባሃኦላህ የታሰረበትን ክፍሎች መስኮቶች ሊያዩ ወደሚችሉበት እሥር ቤቱን ከብበው ከሥስተኛው ሰው ሰራሽ ወንዝ ባሻገር ወደሚገኘው ገላጣ ሥፍራ እየሄዱ ይመለከቱት ነበር። እርሱም ባንድ መስኮት በኩል ብቅ ብሎ ሲታያቸው በሩቅ አተኩረው ካዩት በኋላ እያለቀሱና በአዲስ የመስዋዕትና የማገልገል ስሜት ተሞልተው ወደ የአገራቸው ይመለሱ ነበር።
የእሥር መላላት
በመጨረሻው እሥሩ ተቃለለላቸው። የቱርክ ወታደሮች ንቅናቄ ስለተደረገ እነርሱ የታሰሩበት ሠፈር ለወታደሮች ተፈለገ። ባሃኦላህና ቤተሰቦቹ ለብቻቸው ወደ አንድ ቤት ሲዛወሩ የቀሩት ከተማው ውስጥ በሚገኘው ወደ አንድ የመንገደኞች መጠለያ ተወሰዱ። ባሃኦላህ በዚያች ቤት ውስጥ ለሰባት ዓመታት በእስረኝነት ቆየ። በዚች ቤት በመጀመሪያ የቆይታ ጊዜያቸው በመጣበብ፥ በቂ ምግብ በማጣትና ለኑሮ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ባለማግኘት በጣም ተቸገሩ። ባሃኦላህና ተከታዮቹ የወታደሮቹን ሠፈር እንዲለቁ ከተደረጉበት ጊዜ ጀምሮ ጠያቂዎች እንዲጎበኙአቸው ተፈቀደ። በመንግሥቱም የተፈረደው ጽኑ ቁጥጥር ምንም እንኳን አልፎ አልፎ ቢጠብቅም ቀስ በቀስ እየተሻሻለላቸው ሄደ።
የወህኒ ቤት በሮች ተከፈቱ
እሥራቱ እንኳን በጠናበት ወቅት በሃኢዎች ተስፋ አልቆረጡም። ጽኑ እምነታቸውም አልተናወጠም። አቆር (አካ) በሚገኘው የወታደሮች መኖሪያ ውስጥ በነበረ ጊዜ ባሃኦላህ ለአንዳንድ ምዕመናን እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “አትፍሩ፥ እነዚህ በሮች ይከፈታሉ። ድንኳኔም በቀርሜሎስ ተራራ ላይ ይተከላል። ፍጹም ደስታም ይሆናል።” ይህ አዋጅ ለተከታዮቹ በጣም ትልቅ መጽናኛ ነበር። ጊዜውም ሲደርስ ትንቢቱ ቃል በቃል ተፈጸመ። የወህኒ ቤቶች በሮች አከፋፈት ታሪክ በልጅ ልጁ በሾጊ ኤፌንዲ እንደተተረጎመው በአብዱል-ባሃ ቃላት ቢነገር ይበልጣል፦
“ባሃኦላህ የገጠርን ውበትና ልምላሜ ይወድ ነበር። አንድ ቀን እንዲህ ሲል ተናገረ፦ ‘ዓይኖቼ ልምላሜን ካዩ ዘጠኝ ዓመት ሆናቸው። ገጠር የነፍስ ዓለም ሲሆን ከተማ የአካል ዓለም ነው።’ እነዚህን ቃላት እንደሰማሁ የገጠርን ኑሮ በጣም መፈለጉ ገባኝ። ይህንንም ፍላጎቱን ከግቡ ለማድረስ የማደርገው ጥረት ሁሉ ፍጻሜ እንደሚያገኝ እርግጠኛ ሆንኩ። በዚያን ጊዜ የኛ ተቃዋሚ የሆነ ሞሐመድ ፓሻ ሳፍዋት የሚባል ሰው አካ ውስጥ ይኖር ነበር። እርሱም ከከተማው በስተ ሰሜን አራት ማይልስ ራቅ ብሎ በጣም በተዋበ ባትክልት ቦታዎች የተከበበና ወራጅ ምንጭ ያለበት ማዝራዬ የሚባል ሰፊና ትልቅ መኖሪያ ቤት ነበረው። ይህንን ፓሻ ቤቱ ድረስ ሄጄ ‘ፓሻ አንተ የምትኖረው አካ ከተማ ውስጥ በመሆኑ ቤትህ ወና ሆኗል’ ስል ጠየቅሁት። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰልኝ ‘እኔ በሽተኛ በመሆኔ ከከተማ ልወጣ አልችልም። ወደዚያ ብሄድ ብቸኛ ከመሆኔም በላይ ከወዳጆቼ እለያለሁ።’ እኔም ‘አንተ እዚያ ካልኖርክበት ባዶውን ከሚሆን አክራየን’ አልኩት። በዚህ ኃሳብ በጣም ተገረመ። ይሁን እንጂ ወዲያው ተስማማበት። ቤቱንም በአነስተኛ ዋጋ በመከራየት በአመት አምስት ፓውንድ ለመክፈል ለአምስት ዓመት ውል ተዋዋልን። ቤቱን የሚያድሱና የአትክልት ቦታውንም የሚያጸዱ ሠራተኞች ወደዚያ ላክሁ። መታጠቢያ ቤትም እንዲሠራለት አዘዝሁ። ከዚህም በላይ “የተባረከው ውበት” 1 ወደ ቢታው የሚሄድበት ሠረገላ እንዲዘጋጅ አደረግሁ። አንድ ቀን እኔው እራሴ ቦታውን ሄጄ ለማየት ቁርጥ ሐሳብ አደረግሁ። ምንም እንኳን በተከታታይ ማዘዣ ከከተማ ግንብ እንዳናልፍ በጥብቅ ብንከለከልም በከተማው በር ወጣሁ። ወታደሮች ዘብ ላይ ነበሩ፤ ነገር ግን ምንም ስለአልተቃወሙኝ በቀጥታ ወጥቼ ወደ ተባለው ቤት ሄድኩ። በነጋታውም ምንም እንኳን ዘበኞች በሁለቱም በኩል በከተማው በር ላይ ቢቆሙም ከጥቂት ምእመናንና ባለሥልጣኖች ጋር ያለአንዳች ጉዳትና ተቃውሞ ወጥቼ ሄድኩ። በሌላ ቀን ደግሞ በባህጂ በሚገኙት አርዘሊባኖስ ዛፎች ሥር ግብዣ አዘጋጅቼ የከተማውን ታላላቅ ሰዎችና ባለሥልጣኖች ጋበዝኩ። ሲመሽ ሁላችንም አብረን ወደ ከተማ ተመለስን።
“አንድ ቀን ወደ ‘ተባረከው ውበት’ ቅዱስ ፊት ቀርቤ እንዲህ አልኩ። ‘ማዝራዬ የሚገኘው መኖሪያ ቤት ተዘጋጅቶልሃል። ወደዚያም የሚወስድህ ሠረገላ ቀርቧል።’ (በዚያን ጊዜ አካ ወይም ሃይፋ ውስጥ ሠረገላ አልነበረም) እርሱም ‘እስረኛ ነኝና አልሄድም’ ሲል መለሰ። ደግሜም ብጠይቀው ይህንኑ መለሰልኝ። ለሦስተኛ ጊዜ ብጠይቀው ‘አልሄድም’ ብሎ መለሰልኝ። ደጋግሜ ለመጠየቅ አልደፈርኩም። የሆነ ሆኖ በአካ ውስጥ ባሃኦላህን በጣም የሚወድና በእርሱም ተወዳጅ የሆነ በጣም ዝነኛና የታወቀ አንድ የእስላም ሼክ ስለነበረ እርሱን ጠርቼው ሁናቴውን እንዲህ ስል አብራራሁለት። ‘አንተ ደፋር ነህ፥ ዘሬ ማታ ከተቀደሰው ፊት ቀርበህ ተንበርክከህ እጆቹን ያዝና ከከተማው ለመውጣት ቃል እስኪገባልህ ድረስ ለምነው’። ይህም ዓረብ በቀጥታ ወደ ባሃኦላህ ሄደና ጉልበቱ ሥር ተቀመጠ። የተበረከውን ውበት እጆች ይዞ በመሳም እንዲህ ሲል ጠየቀው። ‘ለምን ከተማውን አትለቅም?’ አለው እርሱም ‘እስረኛ ነኝ’ ብሎ መለሰለት። ሽይኩም መልሶ ‘እግዚአብሔር አይበለው! አንተን እሥረኛ ለማድረግ ሥልጣን ያለው ማነው? ራስህን እሥር ቤት ያቆየኸው አንተ ነህ። የታሠርከው በራስህ ፈቃድ ነው። አሁንም ከእሥር ቤት ወጥተህ ወደ ቤተ መንግሥቱ እንድትሄድ እለምንሃለሁ። ቦታው በጣም ውብና ለምለም ነው። ዛፎቹ በጣም ቆንጆ ሲሆኑ ብርቱካኖቹም የእሳት አለሎ ይመስላሉ!’ የተበዘረከው ውበት ‘እስረኛ ነኝ፥ ሊሆን አይችልም’ ባለ ቁጥር ሼይኩ እጆቹን እየያዘ ይስም ነበር። አንድ ሰዓት ሙሉ ሲለምነው ቆየ። በመጨረሻው ባሃኦላህ ‘ኬሊኩብ’ (እሺ) ስላለ የሼይኩ ትዕግሥትና አጥብቆ መለመን ዋጋውን አገኘ። ... ሸይኩ በታላቅ ደስታ ተመልቶ ወደኔ በመምጣት የቅዱስነቱን (የብጽዕነቱን) የመስማማት ምሥራች አበሰረኝ። ምንም እንኳን ከተቀደሰው ውበት ጋር እንዳንተያይና ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዳናደርግ የሚከለክል የአብዱል አዚዝ ጥብቅ ትእዛዝ ቢኖርም በነጋታው ሠረገላውን አምጥቼ ወደ መኖሪያ ቤቱ አብረን ሄድን። ማንም የተቃወመን አልነበረም። እሱን እዚያው ትቼ እኔ ወደ ከተማው ተመለስኩ።
“ለሁለት ዓመት በዚያ ውብና በጣም ባማረ ሥፍራ ኖረ። ከዚያ በኋላ ወደሌላ ቦታ እንዲዛወር ተወስኖ ወደ ባህጂ ሄደ። እንደአጋጣሚ ባህጂ ተላላፊ በሽታ ገብቶ ስለነበርና አንድ ባለንብረት ሳይወድ ቤተሰቡን ይዞ ለመሸሽ ስለፈለገ ቤቱን ሊኖሩበት ለሚፈልጉ ሁሉ በነፃ ለመስጠት ዝግጁ ነበር። እኛም ቤቱን በትንሽ ዋጋ ተከራየነው። በዚያም የግርማና የእውነተኛ መንግሥት በሮች በሰፊው ተከፈቱ። ምንም እንኳን ለደንቡ ባሃኦላህ እስረኛ ቢሆንም (የሱልጣን አብዱል አዚዝ ጥብቅ ትእዛዝ ያልተሰረዘ ስለሆነ) እንደእውነቱ ከሆነ በአኗኗሩ በአኳኋኑ የታላቅነትና የክብር ግርማ የሚያይበትና በሁሉም ዘንድ የተከበረ ስለነበረ የፓለስታይን ገዥዎች በችሎታውና በክብሩ ይቀኑበት ነበር። ምንም እንኳን ጥያቄአቸውን ብዙ ጊዜ ባይቀበለውም አገረ ገዥዎችና ሙታሳሪፎች፥ ጀኔራሎችና የአካባቢ ባለሥልጣኖች እርሱ ፊት ለመቅረብ ዕድል ለማግኘት በትህትና ይጠይቁ ነበር።
“ከእለታት አንድ ቀን የከተማው ገዥ ከከፍተኛ ባለሥልጣን በታዘዘው መሠረት ከአንድ ጄኔራል ጋር ‘የተባረከውን ውበት’ ለመጎብኘት ፍቃድ ለመነ። ልመናው ከተፈቀደ በኋላ በጣም ግዙፍ የነበረው አውሮፓዊ ጄኔራል በግርማ በተሞላው በባሃኦላህ ገጽ በጣም በመደነቅ በደጃፉ ላይ ተንበርክኮ ብዙ ጊዜ ቆየ። የሁለቱም ጎብኚዎች ፍርሃት በጣም የበዛ ከመሆኑ የተነሣ የቀረበላቸውን ናርግዌሌ (ጋያ) እንኳን ለመቀበል የቻሉት ባሃኦላህ እየደጋገመ ከጋበዛቸው በኋላ ነበር። ቢሆንም ጋያውን ጥቂት በመቅመስ ብቻ ተወስነው እዚያ ተሰብስበው የነበሩት እስኪያደንቁ ድረስ ትህትና በተሞላበት አክብሮት እጃቸውን አጣምረው ተቀመጡ።
“ፍቅር የተሞላበት የወዳጆች አክብሮት፥ በባለሥልጣኖችና በታላላቅ ሰዎች ይሰጠው የነበረው የአክብሮት ግምት፥ የጎብኝዎችና የእውነት ፈላጊዎች መጉረፍ፤ በግልጽ ይታይ የነበረው የእምነትና የአገልግሎት መንፈስ፤ ግርማዊና ንጉሣዊ የሆነው ‘የብሩክ ፍጹምነት’ ገጽ፥ የትእዛዞቹ ተፈጻሚነት፥ ከልባቸው የሚያፈቅሩት የምእመናን ብዛት፤ እነዚህ ሁሉ ባሃኦላህ የነገሥታት ንጉሥ እንጂ በርግጥ እሥረኛ እንዳልነበረ ይመሰክራሉ። ኃያላንና ያልተወሰነ ሥልጣን የነበራቸው ሁለት ጨቋኝ ነገሥታት ተቃዋሚዎቹ ነበሩ፤ ሆኖም በገዛ ወህኒ ቤታቸው ውስጥ እንኳን ታስሮ ተገዥዎቹን እንደሚያነጋግር ንጉሥ ኃይለኛ ቃላት የተሞላበት ደብዳቤ ይጽፍላቸው ነበር። በኋላም ምንም እንኳን ጥብቅ ትእዛዞች ቢኖሩም እንደ አንድ ልል ሆኖ በባህጂ ኖረ። ብዙ ጊዜ ‘እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ፤ በጣም የከፋው ወህኒ ቤት ወደ ኤደን ገነት ተለውጧል’ ይል ነበር።
“በእርግጥ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እንደዚህ ያለ ነገር ታይቶ አይታወቅም!”
የባህጂ ኑሮ
ባሃኦላህ በመጀመሪያዎቹ የችግር ዓመታት በችግርና በውርደት እየኖረ እግዚአብሔርን ያወድስ እንደነበረ ሁሉ እንዲሁም ደግሞ በሚቀጥሉት ዓመታት በክብርና በብልጽግና በባህጂ በኖረበት ወቅት እግዚአብሔርን የማመስገን አርአያ አሳይቷል። በብዙ መቶ ሺ የሚቆጠሩ ታማኝ ተከታዮች፥ እንዲጠቀምበት ብዙ መዋጮ አድርገው በእርሱ አስተዳደር ሥር እንዲሆን ጠየቁት። ምንም እንኳን የባህጂ ኑሮው በርግጥ የንጉሣዊ ኑሮ ቢሆንም፤ ይህ ኑሮው በዓለማዊ ክብር ወይም ሀብት መልክ አልነበረም። ባሃኦላህና ቤተ ሰቦቹ መጠነኛ ኑሮ ቢኖሩም በራስ ወዳድነት ለድሎት ወጭ ማውጣት በዚያ ቤተሰብ ያልተለመደ ነበር። ምእመናኑ በቤቱ አቅራቢያ ሪዝቫን የሚባል የተዋበ ያትክልት ቦታ ሠርተውለት ስለነበር ተከታታይ ቀኖችን ወይም ሳምንቶችን አትክልቱ ቦታ ውስጥ ከሚገኘው ትንሽ ጎጆ ውስጥ ያሣልፍ ነበር። አንዳንድ ጊዜም ራቅ ብሎ ወደመስክ ይሄድ ነበር። አካንና ሀይፋን ብዙ ጊዜ ጎብኝቷል። እንደዚሁም በአካ በወታደሮች መኖሪያ ውስጥ ታሥሮ በነበረ ጊዜ ተንብይቶት እንደነበረው ከአንድ ጊዜ ይበልጥ በቀርሜሎስ ተራራ ላይ ድንኳኑን ተክሏል። ባሃኦላህ አብዛኛውን ጊዜውን በጸሎት፥ በሱባኤ፥ ቅዱሳት መጻሕፍትን በመጻፍ፥ መልእክቶችን በመግለጽና ለምዕመናኑ መንፈሳዊ ትምህርትን በመስጠት ያሳልፍ ነበር። ለዚህ ታላቅ ሥራ ሙሉ ነጻነት እንዲያገኝ፥ አብዱል-ባሃ ሙላዎችን፥ ባለቅኔዎችንና የመንግሥቱን ባለሥልጣኖች ተቀብሎ በማነጋገርና እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮችን በማከናውን ይረዳ ነበር። እነዚህ ሁሉ አብዱል-ባሃን በመገናኘት ሲደሰቱ በማብራሪያውና በንግግሩ አጥጋቢ መልስ ስለሚያገኙ ምንም እንኳን ባሃኦላህን ራሱን ባያነጋግሩትም ከልጁ በሚያገኙት አጥጋቢ ማብራሪያ ባሃኦላህን ይወዱት ነበር። እንደዚሁም የአብዱል-ባሃ አኳኋን ያባቱን ደረጃ እንዲረዱት ያደርጋቸው ነበር።
በጣም የታወቀው የምሥራቅ ታሪክ ተመራማሪ የነበረው የከምብሪጅ ዩኒቨርስቲው ፕሮፌሰር ኤድዋርድ ጂ. ብራውን እ. ኤ. አ. 1890 ዓ.ም. ባሃኦላህን በባህጂ ባገኘ ጊዜ ያደረበትን ስሜት እንደሚከተለው ጽፏል፦
“ጫማዬን እስካወልቅ ድረስ አስተናባሪዬ ለጥቂት ጊዜ ቆሞ ጠበቀኝ። በተለመደው የአቀባበል ባህል ካስገባኝ በኋላ መጋረጃውን ዘግቶ ተመለሰ። እኔም ባንድ በኩል በአጭር ሶፋ ተከቦ፥ ከመዝጊያው ፊት ለፊት ካለው ወገን ደግሞ ሁለት ወይም ሦስት ወንበሮች የተደርደሩበት ሠፊ ክፍል ውስጥ ገብቼ ቆምኩ። ምንም እንኳን የት እንደምሄድና ማንን እንደማይ ትንሽ ብጠራጠርም (በቅድሚያ የተሰጠኝ ማብራርያ ስላልነበረ) በአድናቆትና በድንጋጤ በክፍሉ ውስጥ ማንም ሰው መኖሩን ሳልረዳ አንድ ወይም ሁለት ሴኮንዶች ያህል አለፉ። ወደግድግዳው በሚጠጋ ከአጭሩ ሶፋ ላይ ጠርዙን በነጭ መጠምጠሚያ የተከበበና ታጅ የሚሉትን (ነገር ግን በጣም ረዥም የሆነ ከማቅ የተሠራ) ቆብ የደፋ በጣም ግሩምና የተከበረ ሰው ተቀምጦ ነበር። ያንን ያየሁትን ገጽ ምንም እንኳን ልገልጸው ባልችል ፍጹም ከአእምሮዬ አይጠፋም። እነዚያ አተኩረው የሚመለከቱ ዓይኖቹ የሰውን ነፍስ ጠልቀው የሚያዩ ይመስላሉ፤ ኃይልና ሥልጣን በሠፈው ሽፋሉ ላይ ሲታይበት፥ በግንባሩና በፊቱ ላይ ያሉት ጥልቅ መሥመሮች እስከወገቡ ተንጣሎ የተኛው ጥቁር ሐር የመሰለው ፀጉሩና ጺሙ ሊደብቁ የሞከሩትን እድሜ ያሳዩ ነበር። ነገስታት ቢቀኑበት፥ ንጉሠ ነገሥቶች ቢሹት ሊያገኙት የማይችሉትን የታማኝነትና የፍቅር ባለቤት ከሆነው ፊት አጎንብሼ ቀና እንዳልኩ ከማን ፊት እንደቆምኩ መጠየቅ አላሻኝም።
“ለዘብ ባለና አክብሮት በተሞላበት ድምጽ እንድቀመጥ ከጋበዘኝ በኋላ ንግግሩን ቀጠል በማድረግ፦ ‘ፍላጎትህ በመሟላቱ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይድረሰው!... እሥረኛና ስደተኛ ለማየት መጥተሃል... ፍላጎታችን ለዓለም ደህንነትና ለአገሮች ደስታ ብቻ ነው፤ ግን እሥራትና ከአገር መባረር እንደሚገባው የጠብ ቆስቋሽና አነሳሽ እንደሆነ ሰው አድርገው ገመቱን... አገሮች ሁሉ በእምነት አንድ እንዲሆኑና በሰዎች ዘንድ ወንድማማችነት እንዲፈጠር፥ የፍቅር ሰንሰለትና አንድነት በሰው ልጆች መካከል እንዲጠነክር፥ የሃይማኖት መከፋፈል እንዲወገድና የዘር ልዩነት ፈጽሞ እንዲጠፋ ዓላማችን ነው። ይህ ምን ጉዳት አለው? ... ሆኖም ይህ ሁሉ ይፈጸማል፤ እነዚህ ፍሬቢስ ብጥብጦችና አጥፊ ጦርነቶች አልፈው ‘ታላቁ ሰላም’ ይመሠረታል ... እናንተስ በአውሮፓ ይህ አያስፈልጋችሁምን? ክርስቶስ የተነበየለት ይህ አይደለምን? ... ይሁን እንጂ ነገሥታቶቻችሁና ገዥዎቻችሁ ሀብታቸውን ለሰው ልጅ ደስታን ለሚጨምሩ ነገሮች በማዋል ፋንታ የሰው ልጅ ማጥፊያ በሚሆን ነገር ላይ ሲያባክኑ እናያቸዋለን። … እነዚህ ብጥብጦች፥ አለመግባባቶችና ደም መፋሰስ ይወገድ፥ሰዎችም አንድ ወገንና አንድ ቤተሰብ ይሁኑ። … አንድ ሰው አገሩን በመውደድ ብቻ አይመካ ፥ የሰውን ልጅ በመውደድ እንጂ።
“ከባሃ የሰማኋቸው ቃላት ከብዙ በጥቂቱ እንደማስታውሰው እነዚህ ናቸው። ይህ ትምህርት ሞትንና እስራትን የሚያስከትል ወይም በዓለም ተሰራጭቶ ዓለምን የሚጠቅም ወይም የሚጎዳ እንደሆነ አንባቢ ያመዛዝን።” (የ‘ትራቭለርስ ናሬቲቭ’ መቅድም፤ ኤፒሶድ ኦፍ ዘ ባብ ገጽ 39)
ዕ ር ገ ት
ባሃኦላህ የመጨረሻ ምድራዊ ዘመኑን በሰላም በማሳለፍ ላይ ሳለ እ.ኤ.አ. ግንቦት 29 ቀን 1892 ዓ.ም. ሕመም ባስከተለ ትኩሳት ምክንያት በተወለደ በሰባ አምስት ዓመቱ አረፈ። ከገለጻቸው የመጨረሻ መልእክቶቹ መካከል በእጁ ጽፎ የፈረመበትና በማህተሙ ያሸገው ቃለ ኑዛዜው ይገኝበታል። በሞተ በዘጠነኛው ቀን ቤተሰቡና ጥቂት ምዕመናን ባሉበት ታሽጎ የነበረውን ቃለ ኑዛዜ የበኩር ልጁ ከፍቶ በተነበበ ጊዜ አጭር ሆኖ በውስጡ ግሩምና አስደናቂ ቃላት የሠፈሩበት ቃለ ኑዛዜው ታወቀ።
በኑዛዜው መሠረት አብዱል-ባሃ የአባቱ እንደራሴና የትምህርቱ አስፋፊ እንዲሆን ሥልጣን ስለተሰጠው የባሃኦላህ ቤተሰብ፥ ቤተዘመዶቹና ምእመናኑ በሙሉ እንዲከተሉትና እንዲታዘዙት አደረገ። በዚህም ሁናቴ በሃይማኖቱ መከፋፈልና መለያየት እንዳይኖርና የሃይማኖቱም አንድነት ማረጋገጫ መድህን ሆነ።
የባሃኦላህ ነቢይነት
ባሃኦላህ ነቢይ ለመሆኑ ግልጽና የተስተካከለ አስተያየት እንዲኖረን ያስፈልጋል። ቃላቱ እንደሌሎቹ መለኮታዊ ‘መገለጦች’ በሁለት ሊከፈሉ ይችላሉ። ይኸውም በአንደኛው በእግዚአብሔር ታዞ ለወገኖቹ መልእክት እንደሚያስተላልፍ ሰው ሲናገር በሁለተኛው ደግሞ ቃላቱን በቀጥታ እግዚአብሔር ራሱ የሚናገራቸው ይመስላል።
‘ኢቃን’ በተባለው መጽሐፉ ውስጥ እንዲህ ሲል ጽፏል፦
“ቀደም ብለን ባለፉት ገጾች እንደገለጽነው ከዘለዓለማዊ ቅድስና የቀን ጮራ የሚያበሩት ለእያንዳንዱ የብርሃን ምንጮች ሁለት ደረጃዎችን ሰጥተናቸዋል። ከነዚህም አንዱ የሆነውን መሠረታዊ የአንድነታቸውን ደረጃ ቀደም ብለን አብራርተናል። ‘አንዱን ከሌላው የማንለይ’ (ቆርአን 2፤ 136) ሁለተኛው ደግሞ የመለያ ደረጃ ሲሆን ይህም በፍጥረት ዓለሙ ሁኔታና በውስጧም የሚገኝ ውሱንነት ነው። በዚህም ረገድ እያንዳንዱ ክስተት ከእግዚአብሔር ተለይቶ የሚታወቅበት የግል መለያ፥ ተመጥኖ የታዘዘ መልእክት፥ በቅድሚያ የታዘዘ ራዕይ በተለይ ለእርሱ የተሰጠ ውሱንነት አለው። እያንዳንዱ በልዩ ስም ይታወቃል፤ በተለየ ጠባይ ይለያል፤ የተወሰነ መልእክት ይፈጽማል፤ እንደዚሁም ለተለየ ራዕይ ባለአደራ ነው። እርሱም እንደዚህ ብሏል ‘እነዚህን መልእክተኞች ከፊላቸውን በከፊሉ ላይ አስበለጥን፥ ከእነርሱ ውስጥ አላህ ያነጋገረው አለ፥ ከፊሎቻቸውንም በደረጃቸው ከፍ አደረገ፥ የማርያምን ልጅ ኢሳንም ግልጽ ተዓምራቶችን ሰጠነው፥ በቅዱስ መንፈስም አበረታነው’ (ቱርአን ም. 2፤ አልቀበራህ 253)
“በዚህ መሠረት ከአንድነታቸውና ከፍጹምነታቸው ደረጃ ሲታይ በመለኮታዊ ምሥጢር ላይ የተመሠረቱና በመለኮታዊ ግልጽነት ዙፋን ላይ የተቀመጡ፦ የአምላክነት፥ የመለኮታዊነት፥ የከፍተኛው አንድነትና የጥልቅ ባሕርይ ለእነዚህ የሕይወት መሠረት ለሆኑት ተሰጥቶ የነበረና የሚሰጥም ነው። የእግዚአብሔር ክስተት ይገለጣል። በእነርሱም ገጽ የእግዚአብሔር ውበት ይታያል። ስለዚህ በእነዚህ ክስተቶች የተነገረውን ሁሉ ከእግዚአብሔር ከራሱ እንደተነገረ ለመቁጠር ይቻላል።
“በሁለተኛው ደረጃቸው ማለት ከመበላለጥ፥ ከልዩነት፥ ከዚህም ምድራዊ ኑሮ ውስንነታቸው ከባህርያቸውና ከኑሮ ደረጃቸው መጠን ሲታዩ ፍጹም አገልጋይነት፥ እጅግ በጣም መቸገርና የፍጹም ዝቅተኝነት ጠባይ ይታይባቸዋል። እርሱ ‘እኔ የእዚአብሔር አገልጋይ ነኝ እንደናንተም ሰው ነኝ’ ይላል፦
“ሁሉን አቀፍ ከሆኑት ከእግዚአብሔር ክስተቶች አንዱ ‘እኔ እግዚአብሔር ነኝ!’ ቢል እርሱ በርግጥ፥ እውነት ተናገረ፥ ጥርጣሬም የለውም። ምክንያቱም በእነርሱ መገለጽ፥ በባህርያቸውና በስማቸው የእግዛኢብሔር መገለጽ፥ ስሙና ባህርይው ለዓለም የሚገለጽ መሆኑ ተደጋግሞ ታይቷል። እርሱ እንደዚህ ሲል ገልጿል፦ ‘እነዚህ ፍላጻታች የእግዚአብሔር እንጂ ያንተ አልነበሩም።’ (ቆርአን 8. 17) ደግሞም እንደዚህ ብሏል፦ ‘በእውነት ላንተ ታማኝነታቸውን የገለጡ ሁሉ በእርግጥ ለእግዚአብሔር ታማኝነታቸውን ገለጡ።’ (ቆርአን 48፤ 10) እንደዚሁም ማንኛቸውም ‘እኔ የእግዚአብሔር መልእክተኛ ነኝ’ ብሎ ቢናገር እርሱም የማያጠራጥር እውነት ተናገረ። እርሱ እንደተናገረው ‘ሞሐመድ ከእናንተ መካከል የማንም አባት አይደለም፥ የእግዚአብሔር መልእክተኛ እንጂ።’ በዚህ ሁኔታ ሲታዩ ሁሉም የዚያ የፍጹም ንጉሥ የማይለወጥ ባህርይ መልእክተኞች ብቻ ናቸው። እንደዚሁም ደግሞ ሁሉም ‘እኔ የነቢያቶች መጨረሻ ነኝ፤’ ብለው ሲያውጁ በርግጥ ጥርጥር የሌለበት እውነት ተናገሩ። ምክንያቱም ሁላቸውም አንድ ሰው፥ አንድ ነፍስ፥ አንድ መንፈስ፥ አንድ ፍጥረት፥ አንድ ክስተት ናቸው። ሁሉም የመንፈሶች ውስጣዊ መንፈስና የባሕርይዎች ዘለዓለማዊ ባሕርይ የሆነው የርሱ ‘አልፋና ኦሜጋ’ የመጀመሪያውና የመጨረሻው የሚታየውና ስውር የሆነው ክስተት ናቸው። እንደዚሁም ደግሞ ‘የእግዚአብሔር አገልጋዮች ነን’ (ቆርአን 33፤40) ቢሉ ይህም ግልጽ የሆነና የማያጠራጥር እውነት ነው። ምክንያቱም የማንም ሰው ግልጋሎት ሊወዳደረው በማይችል በፍጹም አገልጋይነት ደረጃ የተገለጹ ስለሆነ ነው። በዚህ መሠረት እነዚህ የፍጥረት ባህርያት በጥንታዊውና በዘለዓለማዊው ቅድስና ውቅያኖስ ውስጥ ጠልቀው ሲመስጡ ወይም በመለኮታዊ ሚስጢር ከፍተኛ አምባ ላይ ሲንሳፈፉ የእግዚአብሔር የራሱ ጥሪ የሆነው መለኮታዊ ድምጽ መሆናቸውን በቃላቸው ያውጃሉ። የማስተዋል ዓይን ቢከፈት በዚህ ሁኔታቸው ሁሉን ቻይና የማይበላሽ በሆነው በርሱ ፊት ጭራሽ እንዳሌሉና ራሳቸውን ኢምንት አድርገው መገመታቸውን ለመረዳት ይቻል ነበር። እንደማስበው ራሳቸውን ፈጽሞ ከምንም አልቆጠሩትም፤ በዚያም አደባባይ የስማቸውን መነሳት እንደ ኃጢአት ቆጠሩት። ምክንያቱም በዚህ አደባባይ ስለራስ መጥቀስ እንኳን የትምክህትና ተለይቶ በነፃ የመኖር ፍላጎት ምስክር ነው። ወደዚያ ለመድረስ በቻሉት ሰዎች ዘንድ እንደዚህ ያለው ኃሣብ አሳዛኝ ጥፋት ነው። ከእርሱ ውበት በስተቀር ሌላ ገጽታ ሲመለከት፥ የሰው ልብ፥ አንደበትና አዕምሮው ወይም ነፍሱ በጣም ተወዳጅ ከሆነው ጋር ሳይሆን ቢቀር ዓይኖቹ ከርሱ ውበት በስተቀር ሌላ ገጽ ቢመለከቱ፤ ጆሮው ከርሱ ድምጽ በቀር ወደ ሌላ ዜማ ቢያዘነብል፤ ጫማውም የርሱን መንገድ እንጂ ሌላ መንገድ ቢረግጥ ጥፋቱ የቱን ያህል በበለጠ አሳዛኝ በሆነ ነበር።
“በዚህ ዘመን የእግዚአብሔር እስትንፋስ ነፍሷል። መንፈሱም በሁሉም ላይ ተሰራጭቷል። የጸጋው መጉረፍ በጣም ታላቅ ከመሆኑ የተነሣ የሚጽፈው ብዕር መንቀሳቀሱን ያቆማል። ስለርሱም የሚናገር አንደበት ንግግር ይሳነዋል።
“በዚህ ደረጃ ለራሳቸው የመለኮት ድምጽንና የመሰሉን ማዕረግ ሲሰጡ በመልእክተኝነት ደረጃቸው ደግሞ ራሳቸውን የእግዚአብሔር መልእክተኞች አድርገው አውጀዋል። በየጊዜው ለዘመኑ ሁኔታ ተስማሚ የሚሆን ድምጽ አሰምተዋል። እነዚህም ከመለኮታዊ መገለጽ እስከ ፍጥረተ ዓለምና ከመለኮታዊ ግዛት እስከ ምድራዊ ኑሮ ግዛት ድረስ ላሉት አዋጆች ምክንያቶች ሆነዋል። በዚህ መሠረት ስለመለኮታዊነት፥ ስለጌትነት፥ ስለነቢይነት፥ ስለመል እክተኛነት፥ ስለጠባቂነት ስለሐዋርያነት ሆነ ስለአገልጋይነት ግዛት የሚናገሩት ቃላት ሁሉ ያላንዳች ጥርጥር እውነት ነው። ስለዚህ የማይታየውና የቅድስናው የብርሃን ምንጭ ክስተቶች ልዮ ልዩ ቃላቶች ነፍስን እንዳያውኩና አእምሮን እንዳያናውጡ ከዚህ በላይ አስትያየቶቻችንን እንዲደግፉ ያቀረብናቸውን እነዚህን ቃላቶች ተመራምሮ ማወቅ ይጠቅማል።” (ኪታብ-ኢቃን 176-181)
ባሃኦላህ እንደሰው ሆኖ ሲናገር ለራሱ የሚሰጠው ደረጃ በጣም ዝቅተኛ የሆነና በእግዚአብሔር ዘንድ እራሱን ፈጽሞ እንደሌለ አድርጎ ይቆጥረዋል። በሰብአዊ ተፈጥሮ አንድ ክስተት ከሌላው ሰው የሚለይበት በኃይሉ ፍጹምነትና ራሱን ፈጽሞ በመናቅ ነው። ምንም ነገር ቢያጋጥመው፥ ኢየሱስ በጌተሰማኔ የአትክልት ቦታ ውስጥ ‘የሆነ ሆኖ የኔ ፈቃድ ሳይሆን ያንተ ፈቃድ ይፈጸም’ እንዳለው ለማለት በመቻሉ ባሃኦላህ ለሻሁ በጻፈው መልእክት ውስጥ እንዲህ ይላል፦
“ንጉሥ ሆይ! በእውነት እንደማንኛውም ሰው አንቀላፋ ነበር። የኃያሉ እግዚአብሔር መንፈስ ባጠገቤ ነፍሶ ፈቃዱ የሆነውን እውቀት ሁሉ ገለጸልኝ። ይህ ሁሉ ከኃያሉና ሁሉን አዋቂ ከሆነው እንጂ ከራሴ አይደለም። እርሱ በምድርና በሰማይ መሀከል እንዳውጅ አዘዘኝ። በዚህም ምክንያት የሚገባቸው ሁሉ ዓይናቸው እንባ እስኪያጎርፍ ድረስ የሚያስለቅስ መከራ ደረሰብኝ። ሰዎች በትምህርት ያገኙትን የሥነ ፍጥረት ትምህርት አላጠናሁም፤ ትምህርት ቤቶቻችሁም አልገባሁም። ... ይህች የኃያሉ ከሁሉ በላይ የተመሰገነው የጌታህ ፈቃድ ያንቀሳቀሳት ቅጠል ናት። ኃይለኛ ነፋስ ሲነፍስ ሳትንቀሳቀስ ትቀራለችን? አትቀርም፤ በስመ አምላክና በባሕርይዎች ጌታ እላችኋላሁ! ይልቅስ ከእምቅድመ ዓለም ጀምሮ ከነበረው ፊት ፍጡር በእምቢተኛነት ሊኖር ስለማይችል እንዳፈቀደው ያንቀሳቅሳታል። ስለክብሩም ከዓለማት መካከል እንድናገር የማያወላውለው ትእዛዝ ደረሰኝ። ጌታህ መሐሪውና ደጉ አምላክህ እያንቀሳቀሰኝ ነው እንጂ እንደሞተ ሰው ነበርኩ። አንድ ሰው በራሱ ፈቃድ ትንሽም ሆነ ትልቅ እንዲያሳድዱት የሚያደርገውን ትምህርት ሊሰጥ ፈቃደኛ ነውን? አይደለም! ብዕሩ ከኪምቅድመ ዓለም ጀምሮ ያሉትን ሚስጥር ባስተማረው ስም ሁሉን ቻዩና በሥልጣን ሁሉ ጌታ ጸጋ ካላበረታው በስተቀር ማንም አይችልም።” (ዘ ፕሮሚስድ ዴይ ኢዝ ካም ገጽ 40-41)
ኢየሱስ የደቀመዛሙርቱን እግር እንዳጠበ ሁሉ ባሃኦላህም አንዳንዴ ለተከታዮቹ ምግብ ማብሰልና ሌላም ዝቅተኛ ሥራዎችን ይፈጽምላቸው ነበር። የአገልጋዮች አገልጋይ ሲሆን ክብሩ በአገልግሎት ላይ ብቻ የተመሠረተ፥ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም ደረቅ መሬት ላይ በመተኛት የሚደሰት፥ በደረቀ ዳቦና በውሃ ብቻ ለመኖር የሚችልና እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ በረሃብ (በባሃኦላህም ስያሜ) “በመለኮታዊ ምግብ” ለመኖር ይችል ነበር። ፍጹም ትህትናው ይታይ የነበረው ለፍጥረት፥ ለሰው ልጅና በተለይም ለቅዱሳን፥ ለነቢያትና ለሰማዕታት በነበረው ጥልቅ አክብሮት ነው። ለእርሱ ከኢምንት እስከ ግዙፍ ያሉት ነገሮች ሁሉ ስለእግዚአብሔር ይነግሩት ነበር።
ሰብአዊ ህልውናው መለኮታዊ ብዕር እና እንደራሴ እንዲሆን በእግዚአብሔር ተመርጧል። ይህን ተወዳዳሪ የሌለውን ችግርና መከራን የሚያስከትል ሁኔታ በፈቃዱ አልመረጠውም። ኢየሱስ “አባቴ ሆይ፥ ይቻል እንደሆነስ ይህች ጽዋ ከኔ ትለፍ” እንዳለው እንደዚሁም ባሃኦላህ “የእግዚአብሔርን ቃል የሚያብራራ ወይም የሚናገር ሌላ ቢገኝ ኖሮ ራሳችንን በሰዎች ዘንድ የወቀሳ፥ የመሣለቂያና የፌዝ መሣሪያ ባላደረግን ነበር” ብሏል። (ታብሌት ኦፍ ኢሽራቃት) ነገር ገን መለኮታዊ ጥሪ ግልጽና አዛዥ ስለነበር፥ ታዘዘው። የእግዚአብሔር ፈቃድና የእግዚአብሕር ደስታ ደስታው ስለሆነ ‘በብሩህ ፈቃደኛነት’ እንዲህ ሲል አወጀ፦
“እውነት እላችኋለሁ፥ በእግዚአብሔር መንገድ የሚደርስ ማንኛውም መሰናክል ሁሉ የነፍሴ ተወዳጅና የልቤ ፍላጎት ነው። ፍጹም ኃይለኛው መርዝ በርሱ መንገድ ንጹህ ማር ሲሆን ማንኛውም ጭንቅና መከራ በጥም ጊዜ ከንጹሕ ውሃ እንደ መጎንጨት ያህል ነው።” (በሾጊ ኤፌንዲ ከተተረጎመው ኤፒሲል ቱ ዘ ሳን ኦፍ ዘ ውልፍ ገጽ 17)
ቀደም ብለን እንደገለጽነው ባሃኦላህ አንዳንዴ ሲናገር ‘በአምላክነት ደረጃ’ ነው። በዚህም ደረጃ ሲናገር ሰብአዊ ባህርይው በፍጹም ታዛዥነቱ ስለሚሸፈን ከግምት አይገባም። እግዚአብሔርም በርሱ አድሮ ፍጡሮቹን በማነጋገር፥ ፍቅሩን በመግለጽ፥ ባህርይውን በማስተማር፥ ፍቃዱን በማስታወቅ፥ እንዲመሩበት ሕጉን በማወጅ፥ ፍቅራቸውን፥ ታማኝነታቸውንና አገልግሎታቸውን አጥብቆ ይጠይቃል።
በባሃኦላህ ጽሑፎች ውስጥ አነጋገሩ ብዙውን ጊዜ ከአንዱ ቅርጽ ወደ ሌላው ይለዋወጣል። ስለዚህም አንዳንድ ጊዜ የሚነጋገረው በሰባዊ ሁኔታ ሲሆን ወዲያው ጽሑፉን ሳያቋርጥ በአምላካዊ አነጋገር ይቀጥላል። በሰብአዊነቱ ሲነጋገርም እንኳን ባሃኦላህ እንደ እግዚአብሔር መልእክተኛና ለእግዚአብሔር ፍቃድ ባለው ፍጹም ፍቅር አርአያ በመሆን ነው። ህይወቱ በሙሉ የሚንቀሳቀሰው በመንፈስ ቅዱስ ነው። ስለሆነም በሕይወቱም ሆነ በትምህርቱ በሰብአዊነቱና በመለኮታዊነቱ ጎልቶ የሚታይ ልዩነት የለውም። (ለመለየት አይቻልም) እግዚአብሔር እንዲህ ይለዋል፦
“‘ገጼ ከእግዚአብሔር ገጽ ሌላ ውበቴም ከእርሱ ውበት በቀር፥ ሕያውነቴ ከእርሱ ሕያውነት ሌላ፥ እኔነቴ ከእርሱነቱ በስተቀር፥እንቅስቃሴዬ ከርሱ እንቅስቃሴ ሌላ፥ ፈቃደኝነቴ ከርሱ ፈቃድ ሌላ፥ ብዕሬም በጣም ከተከበረውና ከተመሰገነው ከእርሱ ብዕር ሌላ ምንም አይታይባቸውም።
“‘በመንፈሴ ከዕውነት በስተቀር ሌላ የለም፥ በእኔም ከእግዚአብሔር በስተቀር ሌላ አይታይም።” (ሱራቱል ሐይቃል ገጽ 30)
ተልዕኮው
ባሃኦላህ ለዓለም ያመጣው መልእክት አንድነትን ለማስገኘት ነው። ይህም ሲባል በእግዚአብሔር እምነት ከእግዚአብሔር የሚመጣ የሰው ልጅ አንድነት ማለት ነው። እንዲህ ይላል፦
“ከእውቀት ዛፍ የተገኘው፤ ከሁሉ ይልቅ ድንቅ የሆነው ፍሬ የሚከተለው ከፍተኛ ቃል ነው፤ ሁላችሁም የአንድ ዛፍ ፍሬ፥ የአንድ ቅርንጫፍ ቅጠል ናችሁ። ማንም አገሩን በመውደድ አይመካ፥ መሰሉን የሰውን ዘር እንጂ”
የቀድሞ ነቢያት በምድር ላይ ስለሚመሠረተው የሰላም ዘመን፥ በሰዎች ዘንድ ስለሚገኘው በጎ ፍቃድ ከማብሠራቸውም በላይ ይህ ዘመን ቶሎ እንዲደርስ ሕይወታቸውን ሰውተዋል። ሆኖም እያንዳንዳቸው ይህ የተባረከው ዘመን የሚደርሰው በኋለኛው ዘመን ‘ጌታ መጥቶ’ ኃጥአን ሲፈረድባቸውና ጻድቃንም ወሮታቸውን ካገኙ በኋላ ነው ብለው በግልጽ አውጀዋል።
ዞራስተር የዓለም መድህን የሆነው ሸህ ባህራም መጥቶ የክፋት መንፈስ የሆነውን አህሬማንን ድል ነስቶ የጽድቅና የሰላም ዘመን ከመመሥረቱ በፊት ሦስት ሺህ የብጥብጥ ዘመናት እንደሚያልፉ አስቀድሞ ተናግሮአል።
‘የሠራዊት ጌታ’ መጥቶ የእሥራኤልን ልጆች ከመላው ዓለም ሰብስቦና ጨቋኞቹን አጥፍቶ መንግሥቱ በምድር ላይ ከመመሥረቱ በፊት ረጅም የመሰደድ የመሰቃየትና የመጨቆን ዘመን በእሥራኤል ልጆች እንደሚደርስባቸው ሙሴ አስቀድሞ ተናግሮአል።
ክርስቶስ እንዲህ አለ፦ “በምድር ላይ ሰላም ለማምጣት የመጣሁ አይምሰላችሁ። ሰይፍን እንጂ ሰላም ለማምጣት አልመጣሁም” (ማቴ. 10-34) እንደዚሁም የሰው ልጅ ‘በአባቱ ክብር’ እስኪመለስ ድረስ ስለሚሆነው ጦርነትና የጦርነት ወሬዎች፥ የመጨነቅና የመሰቃየት ዘመን ትንቢት ተናግሯል።
‘አይሁድና ክርስቲያኖች ከክፉ ሥራቸው የተነሣ በትንሣኤ ሙታን ፍርዳቸውን እስኪቀበሉ ድረስ፥ አላህ በመካከላቸው ባላጋራነትንና ጥላቻን ፈጥሯል’ ሲል ሞሐመድ ተናግሯል።
በሌላ በኩል ባሃኦላህ በእነዚህ ነቢያት የተተነበየለትና በዘመኑም ሰላም በርግጥ የሚመሠርት መለኮታዊ ክስተት እርሱ መሆኑን ያውጃል። ይህ ከዛሬ በፊት ያልተደረገና ተወዳዳሪ የሌለው ነው። ከጊዜውም ምልክቶችና ከታላላቆቹ ነቢያት ትንቢት ጋር በሚያስደንቅ አኳኋን ይስማማል። ባሃኦላህ በሰው ዘር መካከል ሰላምንና አንድነትን የሚያስገኝ መፍትሔ ግልጽና ወደር በሌለው መንገድ ገልጾአል።
በእርግጥ ከባሃኦላህ መገለጽ ወዲህና እስካሁንም ድረስ ጦርነትና መተላለቅ ከመቼውም በበለጠ አኳኋን ተደርገዋል፤ በመደረግም ላይ ነው። ስለዚህም ይህ ነቢያቶች ሁሉ ‘በታላቁና ባስፈሪው የጌታ ቀን’ መጀመሪያ ላይ ይፈጸማል ብለው የተነበዩለት ስለሆነ ‘የጌታ መምጫ’ መቃረቡ ብቻ ሳይሆን የተፈጸመ እውን መሆኑን ያረጋግጣል።
ክርስቶስ በምሳሌ እንደተናገረው የወይኑ ባለቤት የወይኑን ሥፍራ በጊዜው ፍሬውን ሰብስበው ለሚሰጡት ለሌሎች ከመስጠቱ በፊት ክፉዎቹን የወይን ጠባቂዎች ጨርሶ ማጥፋት አለበት። ከብዙ መቶ ዓመታት ጀምሮ እንደክፉዎች የወይን ጠባቂዎች ዓለምን ያለአግባብ ሲገዙና ፍሬዋንም ለራሳቸው ጥቅም ብቻ ያዋሉትን እነዚያን ጨቋኝ መንግሥታት ስግብግቦችና የማይቻሉትን (የኃሳብ ነፃነት የማይሰጡትን) ቀሳውስትና ሙላዎች ወይም ጨካኝ መሪዎች ጌታ ሲመጣ አሰቃቂ ጥፋት እንደሚጠብቃቸው ይህ አያስረዳምን?
ምናልባት በጣም የከፋ ድርጊትና ወደር የሌለው ጥፋት ለጥቂት ጊዜ በምድር ላይ ይቀጥል ይሆናል። ግን ባሃኦላህ ‘ከጥቂት ጊዜ በኋላ እነዚህ ፍሬቢስ ብጥብጦችና አጥፊ ጦርነቶች አልፈው ታላቁ ሰላም ይተካል’ ሲል ያረጋግጥልናል። ጦርነትና ብጥብጥ ሊታገሱት በማይቻል አስጊ ሁኔታ ላይ ስለደረሱ የሰው ዘር ጨርሶ ከመጥፋቱ በፊት መድኅን መፈለግ አለበት።
“የፍጻሜው ዘመን መጥቷል፤ እንዲሁም የተጠበቀው መድኅን!”
የባሃኦላህ ጽሑፎች
የባሃኦላህ ጽሑፎች ብዙ ነገሮችን ያዘሉ ሲሆኑ በውስጣቸው በግልም ሆነ በማኅበራዊ ስለማንኛውም ሰብአዊ ኑሮ፥ ስለምድራዊና ስለመንፈሳዊ ነገሮች፥ ስለዘመናዊውና ስለቀድሞው ቅዱሳት መጻሕፍት ትርጉምና በቅርብም ሆነ በሩቅ ለወደፊቱ ስለሚሆኑት ነገሮች ትንቢት ይገኝባቸዋል።
የዕውቀቱ ጥልቀትና ትክክለኛነት የሚያስደንቅ ነበር። ምንም እንኳን ስለብዙዎቹ ቅዱሳት መጻሕፍት በተለመደው ሁኔታ ተመራምሮ የገበየው ዕውቀት ባይኖረውም ለሚጽፉለትም ሆነ በቃል ለሚጠይቁት ለልዩ ልዩ ሃይማኖት ተከታዮች በሚታመንና ሥልጣን በተሞላበት መንገድ ከየመጽሐፋቸው ለመጥቀስና ለማብራራት ችሎታ ነበረው። “እፒስል ቱ ዘ ሰን ኦፍ ዘ ውልፍ” በተባለው መጽሐፍ ውስጥ እንደተገለጸው ምንም እንኳን በራሱ ጽሑፎች ውስጥ ስለባብ መገለጽ ፍጹም ትክክል የሆነ ዕውቀት ቢታይበትም (የባብን ጽሑፎች ለማንበብ እንኳን ጊዜና ዕድል እንዳልነበረው ተናግሯል። ቀደም ብለን እንደተረዳነው ባብ የገለጸው ባያን የተባለው ቅዱስ መጽሐፍ ‘እርሱ እግዚአብሔር የሚገልጸው’ ያነቃቃውና ከእርሱ የመነጨ መሆኑን ገልጾአል!) በ1890 ዓ.ም. እያንዳንዳቸው ከሃያ እስከ ሠላሳ ደቂቃ የሚፈጅ አራት ቃለ መጠይቅ ከፕሮፌሰር ብራውን ካደረገው በስተቀር ከሌሎች ምዕራባዊያን አዋቂዎች ጋር ለመገናኘት ዕድል ባያጋጥመውም ስለምዕራባዊያን ዓለም የማኅበራዊ፥ የፖለቲካና የሃይማኖት ችግሮች በደንብ የሚያውቅ መሆኑን ጽሑፎቹ ይገልጻሉ። ጠላቶቹ እንኳን ጥበብና ዕውቀቱ ወደር የሌለው መሆኑን ማመን ግድ ሆኖባቸዋል። በጽሑፎቹ ውስጥ የተገለጸው የዕውቀት ሃብት ከመንፈሳዊ ምንጭ እንጂ በተለምዶ ጥናትና መማር ያልተገኙና ያለመጻሕፍትና ያለመምህር1 ዕርዳታ የተገኙ መሆናቸውን በጣም የታወቀው የረጅም ዘመን እሥራቱ ሁኔታ እንዳንጠራጠር ሊያደርገን ይችላል።
አንዳንዴ በሀገሩ ተወላጆች ዘንድ በሚሠራበትና ከአረብኛ ጋር በተቀየጠ በዘመናዊው በፋርስ (በኢራን) ቋንቋ ሲጽፍ በሌላ ጊዜ ደግሞ ለተማሩት ዞራስትራያኖች በጠራው በጥንት የፋርስ ቋንቋ ይጽፍ ነበር። በዓረብኛም ሲጽፍ ክፋርስኛ (ኢራንኛ) ቋንቋ ባላነሰ ሁኔታ ሲሆን አንዳንዴ ቀለል ባለ ቋንቋ፥ እንዳንዴም ደግሞ ከቁርዓን በተመሳሰለ ጥንታዊ ስነጽሑፍ ይጽፍ ነበር። የሥነ ጽሑፍ ትምህርት ጨርሶ ስላልነበረው የነዚህ የልዩ ልዩ ቋንቋዎች ዕውቀትና ያጻጻፍ ፍጹም ችሎታው በጣም ይደነቅ ነበር።
በአንዳንድ ጽሑፎቹ የቅድስና መንገዶች በቀላል አነጋገር ስለተገለጹ ‘መንገደኛው እንኳን ቢሆን አይሳሳትበትም’ ሲል በኢሳያስ 35፤ 8 ተገልጿል። በአንዳንዶቹ ደግሞ የቅኔ አጣጣል ኃብት፥ ጥልቅ ፍልስፍና፥ ባለቅኔዎች፥ ፈላስፎች ወይም በጣም የተማሩ ሰዎች በደንብ የሚረዱት የእስላምን፥ የዞራስትሪያኖችንና የሌሎችንም ቅዱሳን መጻሕፍት ወይም የፋርሶችንና የአረቦችን ሥነ ጽሑፍና ተረቶችን የሚመለከት ጽሑፍ ይገኝበታል። እንዲሁም ሌሎች በከፈተኛ ደረጃ ስላሉት መንፈሳዊ ሕይወት ሲሆን እነዚህንም ለመረዳት የሚችሉት የመጀመሪያዎቹን ፈረጃ ያለፉት ብቻ ናቸው። ትምህርቱ የዕውቀት ፈላጊዎችን ሁሉ ፍላጎትና ጣዕም ለማርካት በየዓይነቱ ጣፋጭ ምግብ በተደረደረበት ጠረጴዛ ይመሰላል።
ሃይማኖቱ በተማሩትና በሠለጠኑት በመንፈሳዊ ባለቅኔዎችና በታወቁት ጸሐፊዎች ዘንድ ተወዳጅነትን ያገኘው ለዚህ ነው። ጽሑፎቹ በጣዕማቸውና በመንፈሳዊ ትርጉም ጥልቀታቸው ከሌሎች ጸሐፊዎች ሁሉ ስለላቁ የሱፊዎችና የሌሎችም የእስላም ሃይማኖት ክፍል መሪዎች እንደዚሁም ደራሲዎች የነበሩት አንዳንድ የፖለቲካ ሚኒስትሮች እንኳን በትምህርቱ በጣም ይደነቁ ነበር።
1. አብዱል-ባሃ፥ ባሃኦላህ ስለምዕራባውያን ጽሑፎች የተለይ ጥናት ያደረገ መሆኑንና ጽሑፎቹንም በእነርሱ ላይ መሥርቶ እንደሆነ በተጠየቀ ጊዜ፣ ‘የባሃኦላህ ብዙዎቹ መጻሕፍት የተጻፉትና የታተሙ ከእ.ኤ.አ. በ1870ዎቹ በፊት ባሉ ብዙ ዓመታት ነው። ጽሑፎቹ ባሁኑ ዘመን በምዕራባውያን ዘንድ የተለመዱትን ሃሳቦች ያዘሉ ቢሆንም እነዚህ ሃሳቦች በዚያን ጊዜ እንኳን መጻፍ እንዲያውም አልታሰቡም፤’ ሲል መልሷል ።
Interesting blog? Like it on Facebook, +1 on Google, Tweet it or share this article on other bookmarking websites.