ባብ በደቡብ ኢራን ሺራዝ በምትባለው ከተማ እ. ኤ. አ. ጥቅምት 20 ቀን 1819 ዓ.ም.1 ተወለደ። እርሱም የነቢዩ የሙሐመድ ዘር ነበር። አባቱም በጣም የታወቀ ነጋዴ ነበር። ይሁን እንጂ እንደተወለደ አባቱ ስለሞተ ባብ ሺራዝ ከምትባለው ከተማ ነጋዴ ከነበረው አጎቱ፤ (የእናቱ ወገን) ዘንድ እንዲያድግ ሆነ። እንደአገሩም ባሕል ሕፃናት ማወቅ የሚገባቸውን ያህል ባብ በልጅነቱ የአንደኛን ደረጃ ትምህርት ተሰጥቶት ለማንበብ ቻለ።2 በአሥራ አምስት ዓመቱም መጀመሪያ ከአሳዳጊው ጋር በኋላም ከፋርስባሕረ ሰላጤ ከምትገኘው ቡሺር በምትባል ከተማ ይኖር ከነበረው ከሌላ አጎቱ ጋር ሆኖ የንግድ ሥራ ጀመረ።
በወጣትነቱ ጊዜ በመልኩና በጠባዩ ውበት፤ በጨዋነቱና ተወዳዳሪ በሌለው እምነቱ በጣም የታወቀ ነበር። ሙሐመድ ያዘዘውን ጸሎት አጽዋማት እንዲሁም ሌሎች ትእዛዞች በደንብ ከመከተሉም በላይ ነቢዩ ያስተማረውን መንፈሳዊ እምነት ሁሉ በፍጹም ኑሮው ይገልጸው ነበር። በሃያ ሁለት ዓመቱ ሚስት አገባ። ከዚያም ጋብቻ ተወልዶ የነበረው ልጅ በጨቅላነቱ ባብ መልእክቱን ባወጀበት በመጀመሪያው ዓመት ሞተ።
ባብ በሃያ አምስት ዓመቱ መለኮታዊ ትዕዛዝን በመከተል ‘እግዚአብሔር ለአዋጅ ነጋሪነት እንደመረጠው’ ገለጸ። ‘ትራቭለርስ ናራቲቭ’ ከተባለው መጽሐፍ እንዲህ የሚል ጽሑፍ እናነባለን፦
“ባብ ማለት ከእርሱ በኋላ ከሚመጣ ገና ካልተገለጸ ታላቅ ሰው ለሚጎርፈው ጸጋ መውረጃ ቦይ ማለት ነው። ይህም ከእርሱ በኋላ የሚመጣው ቁጥር ስፍርና ወሰን የሌለው ንጽህናን የተጎናጸፈ ሲሆን፤ ባብም በእርሱ ፍቅር የታሠረና በእርሱም ፈቃድ የሚንቀሳቀስ ነው።” (ኤፒሶድ ኦፍ ዘ ባብ ገጽ 3)
አንድ ታላቅ የእግዚአብሔር መልእክተኛ እንደሚመጣ በዚያን ጊዜ በተለይ ሼኪስ በሚባል የእስላም ሃይማኖት ክፍል የታመነ እንደነበረና ባብም ለመጀመሪያ ጊዜ መልእክቱን የገለጸው ከዚሁ ክፍል ተከታዮች አንዱ ለሆነው ሙላ ሁሴን ቡሽሪይ ለተባለው የታወቀ ደግ ሰው ነበር። ባያን በተባለው ከባብ ጽሑፎች አንዱ በሆነው መጽሐፍ እንደተጻፈው ባብ መልእክተኝነቱን ያበሰረው በእስላም አቆጣጠር ጀማዲዮል አቫል 4 ቀን 12601 ወይንም እ.ኤ.አ. (ግንቦት 22 ቀን 1844 ዓ.ም.) ከምሽቱ በሁለት ሰዓት ከአሥራ አንድ ደቂቃ ላይ ነው ይላል። የባበሃኢ የቀን አቆጣጠር የሚጀምረው እንደ ምዕራባዊያን ከእኩለ ሌሊት ሳይሆን ከጀንበር መጥለቅ በኋላ ስለሆነ ይህ የአዋጅ ቀን የሚከበረው በጀማዲዮል አቫል 5 ቀን ነው። ይኸውም እ.ኤ.አ. ግንቦት 23 ቀን ነው። አብዱል-ባሃ የተወለደው በዚያው እለት ሌሊት ነበር። ይሁን እንጂ ትክክለኛው ሰዓት አልታወቀም። ሙላ ሁሴን ለጥቂት ቀኖች ያህል በናፍቆት ሲመራመርና ሲያጠና ከቆየ በኋላ፤ ሺአይዎች ሲጠባበቁ የኖሩት መልእክተኛ እንደመጣ በሙሉ ልቡ አመነ ደስታውንም ብዙዎቹ ጓደኞቹ ወዱያውኑ ለመካፈል ቻሉ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሼኪዎች በብዛት የባብ ተከታዮች በመሆን ባቢዎች በመባል ታወቁ። ወድያውም የዚሁ የወጣቱ ነቢይ ዝና እንደ እሳተ ነበልባል በፍጥነት በሀገሩ ተሰራጨ።
የባቢ ትምህርት መስፋፋት
የመጀመሪያዎቹ የባብ 18 ደቀመዛሙርት (ከእርሱ ጋር 19) ሆነው “የሕያው ፊደላት” ተብለው ተጠሩ። ደቀ መዝሙሮቹንም ወደ ኢራንና (ፋርስ)፣ ቱርኪስታን ክፍላተ ሀገር ላሉት ሕዝቦች ሁሉ የእርሱን መገለጽ እንዲያስተምሩ ከላካቸው በኋላ እርሱም መንፈሳዊ ጉብኝት ለማድረግ ወደ መካ ተጉዞ እ.ኤ.አ. ታሕሣሥ ወር 1844 ዓ.ም. ደረሰ። ... እዚያም በብዛት ተሰብስበው ለነበሩት መልእክቱን በይፋ ገለጸ። ወደ ቡሺይር ከተመለሰም በኋላ “ባብ” ነኝ ብሎ በማስታወቁ ትልቅ መደናገጥና መሸበር ሆነ። ሕሊናን የሚመስጥ ንግግሩ፥ ፈጣንና በመንፈስ የተገለጹ ጽሑፎቹ፥ የላቀ ጥበቡና ዕውቀቱ፥ ለለውጥ የነበረው ጽኑ ፍላጎቱ በተከታዮቹ ዘንድ ታላቅ አድናቆትን ሲፈጥር፥ በኦርቶዶክስ እስላሞች ዘንድ ግን ተመሳሳይ ድንጋጤንና ጥላቻን አስነሳ። ከሺአይዎች ወገን በምቀኝነት የባብን እውነተኛ ቃል ኃጢአት አድርገው ሁሴን ካን ለተባለው ጨካኝና አረመኔ ለነበረው የፋርስ አገረ ገዥ ነግረው ካስጠኑት በኋላ ባብን ስለከሰሱት ይህ አገረ ገዥ አዲሱ ሃይማኖት ሳይስፋፋ እንዲጠፋ ለማድረግ ሲል ባብን እንዲታሠር አድርጎ በየፍርድ ቤቱ እየተጎተተ ግርፋትና ውርደት እየደረሰበት ችግርን በመቀበል በሰማዕትነት ሕይወቱ እስካለፈችበት ቀን እ.ኤ.አ. እስከ 1850 ዓ.ም. ድረስ ቆየ።
የባብ ማንነት
ባብ ባብነቱን (በርነቱን) በገለጸበት ጊዜ ተቀስቅሶ የነበረው የጥላቻ መንፈስ እንደገና በጭማሪ ሙሐመድ የተነበየለት ሚህዲ (ማህዲ) መሆኑን በገለጸ ጊዜ ይህ የጥላቻ መንፈስ እየዳበረ ሄደ። ይህንንም ሚህዲ ሺአይዎች ከአንድ ሺ ዓመት በፊት ከሰዎች ፊት በተሰወረው በአሥራ ሁለተኛው ኢማም1 ይመስሉታል። እርሱም በሕይወቱ ያለና በነበረበትም ሁኔታ ተመልሶ የሚመጣ ነው ብለው ያምናሉ። ስለመሲህ መምጣት የተነገሩትን ትንቢቶች በክርስቶስ ጊዜ አይሁዶች ቃል በቃል
እንደተረጎሙት ሁሉ፥ እነዚህም ስለመንግሥቱ፥ ስለጸጋው፥ ስለሚያስገኘው ድልና እንደዚሁም ስለአመጣጡ የተሰጡትን “ምልክቶች” በምድራዊ መንገድ ተረጎሙት። በምድራዊ ገዥነት፥ ቁጥራቸው እጅግ በጣም በበዛ የጦር ሠራዊቶች ታጅቦ በመገለጽ ትምህርቱን የሚያውጅ፤ በሞቱትም ሰዎች አስከሬን ነፍስ የሚዘራና ይህንንም የመሳሰሉ ተአምራት የሚያደርግ ይሆናል ብለው ይጠባበቁት ነበር። በዚህ ሁኔታ ምልክቶቹ ስላልተፈጸሙ ባብን ሺአይዎች ከመቃወማቸውም በላይ አይሁዶች በክርስቶስ እንዳፌዙበት፥ እነዚህም ባብን ንቀው በማቃለል ተሳለቁበት። ባቢዎች ግን ትንቢቶቹን በመንፈሳዊ መንገድ ተረጎሙአቸው። እንደ ገሊላው “የስቃይ ሰው” መንግሥቱ ስውር፥ ጸጋው መንፈሳዊ እንጂ ሥጋዊ እንዳይደለ፥ ድል አድራጊነቱም በሰው ልጆች ልብ ከተማ ላይ መሆኑን አመኑ። አዋጁ ትክክለኛ ለመሆኑ በአኗኗሩ፥ በትምህርቱ፥ በማያውላውል እምነቱ፥ በማይሸነፍ ዓላማውና ሰዎችን ከስህተትና ከድንቁርና መቃብር በማስነሳት በአዲስ መንፈሳዊ ሕይወት እንዲኖሩ ለማድረግ በሚያስችል ኃይሉ ብዙ ማስረጃዎችን አግኝተዋል።
ባብ ሚህዲ መሆኑን ብቻ በመግለጽ አዋጁን አልገታም። ነገር ግን “ኑኩቲይኡላ” ወይም “ቀዳማዊው ነቁጥ” (ፕራይማል ፖይንት) በሚል የተቀደሰ ማዕረግ እንዲጠራ ፈቀደ። ይህም ማዕረግ ለነቢዩ ለሞሐመድ በተከታዮቹ የተሰጠው መጠሪያው ነበር። ኢማሞች እንኳን ሥልጣናቸውንና መንፈሳዊ ኃይላቸውን የሚያገኙት ከዚህ ስለሆነ ከቀዳማዊው ነቁጥ ያነሱ ናቸው። ይህንን ማዕረግ ሲይዝ ባብ ከታላላቅ ነቢያቶች አንዱ ከሆነው ከሞሐመድ ጋር ራሱን ማወዳደር ስለሆነ ከእርሱ በፊት የነበሩት ሙሴ እና ክርስቶስ ሃሰተኞች እንደተባሉት ሁሉ ሺአይዎችም ባብን ሃሰተኛ አሉት። ይልቁንም ይሠራበት የነበረውን የጨረቃ ዘመን አቆጣጠር ሠርዞ የፀሐይን የዘመን አቆጣጠር እንደገና መሠረት በማድረግ ትምህርቱን ካወጀበት ዕለት የሚጀምር አዲስ ዘመን አቆጣጠር መሠረተ።
የመከራና ስቃይ መብዛት
በባብ እወጃ ምክንያት የሁሉም መደብ ሕዝቦች፥ ድሀና ባለጸጋ፥ የተማረና ያልተማረውም የባብን አዋጅና ትምህርት ከፍ ባለ ፍጥነት ከመቀበሉና ከማመኑ የተነሳ፥ እነርሱን ለማጥፊያ በየጊዜው የሚደረገው የጭቆናና የአረመኔ ሥራ እጅግ እየባሰ ሄደ። ቤቶች ተዘረፉ። በቴህራን፥ 23/7/2006 በፋርስ፥ በማዚንድራንና እንዲሁም በሌሎች ቦታዎች ቁጥራቸው ከፍ ያሉ አማኞች ተገደሉ። ብዙዎችም አንገታቸው ተቀላ፥ ተሰቀሉ፥ በመድፍ አፈ ሙዝም እንደትቢያ በነኑ። እንዲቃጠሉና እንዲቀረ ጣጠፉም ተደረገ፥ ይሁን እንጂ በዚሁ አሰቃቂ ሁኔታ የተነሣ ትምህርቱ ከመድከም ይልቅ ዝናው እየገነነ፥ እንቅስቃሴውም እየበረታና አማኖቹም ጭቆናው ሳይገታቸው ቁጥራቸው እያደገና እየዳበረ በመሄዱ ስለሚህዲ መምጣት ይነገር የነበረው ትንቢት ቃል በቃል ፍጻሜ አገኘ
“እርሱም ፍጹም የሙሴ ምሉዕነት፥ የኢየሱስ መድኃኒትነትና፥ የኢዮብም ትእግሥት ይኖረዋል። ቅዱሳኑም በዘመኑ የተዋረዱ ይሆናሉ። በቱርክና በደይላማይት ይደረግ እንደነበረው ሁሉ እራሳቸው ተቆርጦ ለስጦታ ይለዋወጡታል። ይሰየፋሉ፥ ይቃጠላሉ፥ ይፈራሉ፥ ይሰጋሉ፤ ተስፋ ይቆርጣሉ፥ መሬትም በደማቸው ትቀልማለች። ሃዝንና ትካዜ በሴቶቻቸው ላይ የበዛ ይሆናል። በርግጥም እኒህ የኔ ቅዱሳን ናቸው።” (ፕሮፌሰር ኢ. ጂ. ብራውን ከተረጎሙት ኒው ሂስትሪ ኦፍ ዘ ባብ ገጽ 132።)
የባብ ሰማዕትነት
እ.ኤ.አ. ሐምሌ 9 ቀን 1850 ዓ.ም. (እንደ እስላም አቆጣጠር ዓርብ ሻባን 28 ቀን 1266) የሰላሳ አንድ ዓመት ጎልማሳ የነበረው ባብ በጨቋኞችና በግል እምነታቸው በተመኩ ጠላቶቹ እጅ ወደቀ። ሰማዕትነቱን ለመካፈል በጣም ከፈለገው አቃ ሙሐመድ አሊ ከሚባለው ወጣት ምዕመኑ ጋር በታብሪዝ በሚገኘው የወታደሮች መኖሪያ አደባባይ ውስጥ ለአመፀኞች መግደያ ወደ ተዘጋጀው ቦታ ተወሰደ። ከጠዋቱ አራት ሰዓት ገደማ የሙሐመድ አሊ ራስ ከተወዳጁ መምህሩ ደረት ላይ እንዲያርፍ ሆኖ ሁለቱንም በብብታቸው ሥር በታሠረው ገመድ አንጠለጠሏቸው። አንድ የአርመን ወታደሮች ረጅመንት በሰልፍ ከተዘጋጀ በኋላ እንዲተኩሱባቸው ታዘዘ። ወዲያውም ተኩሱ አስተጋባ። ነገር ግን የተኩሱ ጢስ ከጠፋ በኋላ ጥይቶቹ የታሠሩባቸውን ገመዶች ብቻ ሲበጣጥሱ እነርሱ ግን ምንም ሳይጎዱ መሬት ላይ ወደቁ። ባብም አቅራቢያው ወደሚገኘው ክፍል ገብቶ ከወዳጆቹ መካከል ከአንዱ ወጣት ጋር ሲነጋገር ተገኘ። ቀትር ላይ እንደገና ተይዘው እንደመጀመሪያው ከተንጠለጠሉ በኋላ እንዲተኩሱባቸው ቢታዘዙ የመጀምሪያውን ተኩሳቸውን ውጤት እንደተአምር የቆጠሩት እነዚህ የአርመን ወታደሮች ፍቃደኞች አለመሆናቸውን ገለጹ። ስለዚህ ሌላ ረጅመት ወደ ሥፍራው ተጠርቶ ትዕዛዝ ከተሰጠ በኋላ ተኮሱባቸው። በዚህ ጊዜ ተኩሱ የታቀደለትን ዓላማ ከግቡ አደረሰው። ምንም እንኳን የሁለቱ ሰማእታት ፊት ባይነካም የቀረው ገላቸው በሚያሰቅቅ ሁኔታ በጥይቶቹ ተበሳሰከ።
በእንደዚህ ያለው አሳዛኝ ሁኔታ የታብሪዙ የወታደሮች መኖሪያ ሁለተኛው ቀራኒዮ ሆነ። የዕውነት ዛፍ በዓለማዊ ፋስ ሊቆረጥ አለመቻሉን ያልገባቸው የባብ ጠላቶች ይህ የባብ የእምነት ዛፍ ከነሥሩ የተነቀለና ከነጭራሹ መደምሰሱም ቀላል መስሏቸው የጥፋት ስሜት የተቀላቀለበት ደስታ ተሰማቸው! ግን በዚህ ያገኙት ድል ባጭር ተቀጨ! ቢያውቁት ኖሮ ይህ የሠሩት ግፍ ለሃይማኖቱ የበለጠ ኃይል የሰጠው መሆኑ በገባቸው ነበር። የባብ መስዋዕትነት በተስፋና በናፍቆት ሲጠባበቅ የነበረውን ምኞቱን ከመፈጸሙም በላይ የከታዮቹ ለሃይማኖቱ በበለጠ እንዲሠሩ አነቃቃቸው። መንፈሳዊ እምነታቸው በጣም ጠንካራ ከመሆኑ የተነሳ ኃይለኛው የሥቃይ ነፋስ የእምነታቸውን እሳት እንዲንበላበል አደረገው። ሃይማኖቱንም የመደምሰስ ሙከራ በጨመረ ቁጥር የእሳቱ ወላፈን እየጠነከረ ሄደ።
የቄርሜሎስ ተራራ መካነ መቃብር
ባብ በሰማዕትነት ከተሰዋ በኋላ አስከሬኑ ከታማኝ ጓደኛው አስከሬን ጋር ከከተማው ግንብ ውጭ ወደሚገኘው የከተማው የውሃ አጥር ዳር ተጣለ። በሁለተኛው ቀን እኩለ ሌሊት ላይ በጥቂት ባቢዎች ተወሰደ። ለብዙ ዓመታት በኢራን ውስጥ በድብቅ ቦታዎች ከቆየ በኋላ በመጨረሻው በብዙ ችግር ወደ ቅድስት አገር ተወሰደ። ባሃኦላህ የመጨረሻ ጥቂት ዓመታት ኖሮበት፥ በአሁኑ ወቅት መካነ መቃብሩም ከሚገኝበት ሥፍራ ጥቂት ራቅ ብሎ ቄርሜሎስ ተራራ ላይ በጣም አምሮ በተሰራው መካነ መቃብር ውስጥ ይገኛል። የተቀደሰውን የባሃኦላህን መካነ መቃብር ለመጎብኘት ከመላው ዓለም ከሚመጡት በብዙ ሺ ከሞቆጠሩት ምዕመናን መሐከል በታማኙ፥ በተወዳጁና ባዋጅ ነጋሪው በባብ መካነ መቃብር ጸሎት ሳያደርስ የሚመለስ የለም።
READ MORE: http://www.bahai.org/
Interesting blog? Like it on Facebook, +1 on Google, Tweet it or share this article on other bookmarking websites.