አረቢያ አብዛኛው ክፍሉ በረሃና ሞቃት እንዲሁም ውሃ እንደልብ የማይገኝበት ነበር፡፡ በነብዩ መሐመድ ጊዜ በአረቢያ ውስጥ ይኖሩ የነበሩት ነገዶች በስልጣኔ ወደኋላ የቀሩና ጊዜያቸውን በእርስ በርስ ጦርነት የሚያባክኑ ነበሩ፡፡ ካለመሰልጠናቸውና ከድንቁርናቸው ብዛት የተነሳ ሚስቶቻቸው፤ ሴት ልጆቻቸውን ሲወልዱ ህጻናቱን ከነነፍሳቸው ይቀብሯቸው ነበር፡፡ የሚፈልጉት ጥሩ ተዋጊ ሊሆኑ የሚችሉትን ወንዶች ብቻ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ በአረቢያ ይኖሩ የነበሩ ሴቶች ከባሮች የተሻለ ነፃነት አልነበራቸውም ነበር፡፡
ምንም እንኳን የነዚህ ሰዎች ጭካኔ ቃላት ከሚገልጹት በላይ ቢሆንም የእግዚአብሔር ልጆች ስለሆኑ መማርና ማወቅ ነበረባቸው፡፡ ስለሆነም የእግዚአብሔር መልዕክተኛ የሆኑት ነብዩ መሐመድ በነዚህ ሰዎች አገርና በእነሱ ነገድ ውስጥ ተወለዱ፡፡
ነብዩ መሐመድ ለዓለማዊ ምቾት ያልተገዙ በመጠነኛ ኑሮ ራሱን የወሰነ ሰው ነበር፡፡ ሥራቸውም አንዳንድ ዕቃዎችን በግመል እየጫኑ ከአረቢያ ወደ ሌላ አገር እየወሰዱ መሸጥ ነበር፡፡ አብዛኛዎቹ የእግዚአብሔር መልዕክተኞች አንደ ነብዩ መሐመድ በቀላል ኑሮ መኖርን የሚሹ ነበሩ፡፡ እንደ ቡድሃ ከነገስታት ወገን የተወለዱት እንኳን ምቾትን በመጠነኛ ኑሮ ለውጠው ኖረዋል፡፡ እግዚአብሔር መልዕክተኞቹ አምላክ ተፅዕኖ እንጂ በምድራዊ ሀብት እንዲመሩ አይፈልግም፡፡ የእግዚአብሔር ሃይል ከታደለው ደካማው ሰው እንኳን ብርቱና ድል አድራጊ ይሆናል፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን ነብዩ መሐመድ በአንድ ተራራ ጫፍ ላይ ቁጭ ብለው ሲፀልዩ የእግዚአብሔር መንፈስ አደረባቸው፡፡ ነብዩ መሐመድ ተማሪ ቤት ገብተው ስለማያውቁ ስማቸውን እንኳን መጻፍ አይችሉም ነበር፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሔር መንፈስ ከሰረፀባቸው ከዚያች ሰዓት አንስቶ የቅዱስ ቁርዓን ታሪክ ተገለጸላቸው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነብዩ መሐመድ የንግድ ስራቸውን አቆሙ፡፡ የእግዚአብሔር መልዕክተኛ ስለሆኑ መልዕክቱን ይዘው ወደ ሕዝቡ ዘንድ ሄዱ፡፡ በመጀመሪያ ማንም ሊያዳምጣቸው አልፈለገም፡፡ በጣዖት ማምለክ ትተው በአንድ እውነተኛ አምላክ እንዲያምኑ ቢነግሯቸውም፣ የአረቢያ ሰዎች በነብዩ መሐመድ ላይ ተነሱባቸው፡፡ እብድ ነው እያሉ ተሳለቁባቸው፡፡ ችሎታ የሌለው ባለቅኔ ነው እያሉ ተዛበቱባቸው፡፡ ነብዩ መሐመድ ግን እንዲህ አሏቸው ‹ እኔ የእግዚአብሔር መልዕክተኛ ነኝ፤ የመጣሁትም እናንተን ለማዳንና ወደ እውነት ጎዳና ለመምራት ነው፡፡›
ለኩሩዎቹ የአረቢያ ሕዝቦች ይህ አነጋገር ሊቀበሉት ከሚችሉት በላይ ነበር፡፡ ነብዩ መሐመድን ብዙ ጊዜ ታግሰዋቸው ነበር፡፡ ከዚያም ተከታዮቻቸውንና ራሱ ነብዩ መሐመድን ወገሯቸው፡፡ ሆኖም ከ13 ዓመት መከራ በኋላ ነብዩ መሐመድ እነዚህ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱና የርሱንም ትዕዛዛት አንዲከተሉ ከመናገር አላቋረጡም፡፡ በጣዖቶቻችን ማምለክ የማንችለው ለምንደን ነው ብለው ራሳቸውን ጠየቁ፡፡ ከዚህ ሁሉ ሌላ የአረቢያ ሰዎች የማያቋርጥ የርስ በርስ ጦርነት ነበረባቸው፡፡ ነብዩ መሐመድን ከዚህ በላይ ሊታገሷቸው አልቻሉም፡፡ ስለዚህ እሱንና ተከታዮቻቸውን ለማውደም ፈለጉ፡፡ ነገር ግን የነብዩ መሐመድ መልዕክት ከፍጻሜ አልደረሰም ነበር፡፡ በጊዜው ለነበሩት ሕዝቦች የሚያስተምሯቸው ሌሎች ሕግጋት ነበሩ፡፡ የተወለዱበትን ሥፍራ መካን ትተው መዲና ተብላ ወደምትጠራው ከተማ ገቡ፡፡
የነብዩ መሐመድ ጠላቶች እሳቸውንና ተከታዮቻቸውን ለመፍጀት አያሌ ጦር ሠራዊት አዘጋጁ፡፡ ነብዩ መሐመድ የእግዚአብሔርን ትምህርት ማስተማርና በእግዚአብሔር ላመኑትም መከታ መሆን ስለነበረባቸው ተከታዮቻቸው ከጠላቶቻቸው ጦር ሠራዊት ጋር እንዲዋጉ ፈቀዱላቸው፡፡ በዚህ አኳኋን ልክ በክሪሽና ዘመን አንደሆነው የብርሃንና የጨለማ ሠራዊቶች ጦርነት ገጠሙ፡፡
ነብዩ መሐመድ መለኮታዊ እረኛ ነበሩ፡፡ ስለዚህም መንጋውን ከነጣቂ ተኩላዎች ማዳን ነበረባቸው፡፡ መጀመሪያ ላይ ነብዩ መሐመድና ተከታዮቹ ችግር አጋጥሟቸው ነበር፡፡ አብዛኛዎቹ የነብዩ መሐመድ ተከታዮች በጠላቶቻቸው ተገደሉ፡፡ ሆኖም የእግዚአብሔር ኃይል ምንጊዜም አሸናፊ መሆኑን ነብዩ መሐመድ ለተከታዮቹ ይነግሯቸው ነበር፡፡ ተከታዮቹ በጠላቶቻቸው በተከበቡ ጊዜ በእግዚአብሔር ያላመኑ ኃያላን መንግስታት ተንኮታኩተው እንደሚወድቁና የእግዚአብሄር ልጆች ድል እንደሚነሱ ነብዩ መሐመድ ትንቢት ተናገሩ፡፡
ሁላችንም እንደምናውቀው ይህ ትንቢት ተፈጽሟል፡፡ ታላላቆቹ የፋርስና የሮማ ግዛቶች በጥቂት አረቦች እጅ ለመውደቅ የበቁት የአረቦቹ ህይወት በነብዩ መሐመድ ትምህርት ወደ እግዚአብሔር ስለተመለሰ መሆኑን እናውቃለን፡፡ የእስልምና ትምህርት ከህንድ እስከ ስፓኝ አገሮች በመዛመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አዲስ ህይወት አግኝተዋል፡፡ በእስልምና የሥልጣኔ ዘመን ብዙ አገሮች በወንድማማችነት ተባብረዋል፡፡ የዕለት ጸሎታቸውን የሚያቀርቡት ለቸሩና ለመሐሪው አንድ አምላክ ብቻ ነበር፡፡ ለሃያሉ እግዚአብሔር መገዛትንና በሱ መታመንን የሚያስተምራቸው ቅዱስ ቁርዓንን ቅዱስ መጽሀፋቸው አደረጉት፡፡ ዛሬም ቢሆን በዓለም ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ምዕመናን ቁርዓንን በሰፊው ያነባሉ፡፡ እንዳለፉት የእግዚአብሔር መልዕክተኞች ሁሉ ነብዩ መሐመድም ከእሳቸው በኋላ ሌላ ታላቅ መልዕክተኛ አንደሚመጣ ለተከታዮቻቸው አረጋግጠውላቸዋል፡፡ በርሱ አማካኝነት ከሰማየ ሰማያት የመጣው የእግዚአብሔር ሃይማኖት ከብዙ ሺ ዓመታት በኋላ ተመልሶ ወደ እግዚአብሔር እንደሚሄድ ተናግረው ነበር፡፡ ይህንንም ማለታቸው ከሺ ዓመት በኋላ ሕዝቡ የእርሳቸው ትምህርት ስለሚረሱት ነው፡፡ በተጨማሪም ሲናገሩ፣ የእግዚአብሔር ሃይማኖት ፋናው ከምድር ሲጠፋ፣ ያን ጊዜ የመለኮት ድምጽ ሁለት ጊዜ ያስተጋባል፡፡ በዚያች ሰዓት የዓለም ህዝቦች የርሱን የእግዚአብሔርን ገጽ ያያሉ ብለዋል፡፡
የመለኮት ድምጽ የተባለውም የእግዚአብሔር ጥሪ ነው፡፡ ነብዩ መሐመድ እንደተነበዩት የእግዚአብሔር ጥሪ በዘመናችን ሁለት ጊዜ ተሰምቷል፡፡ የእስልምና ሃይማኖት ከተመሰረተ ከአንድ ሺ አመት በኋላ በእግዚአብሔር መልዕክተኛና ተከትሎት ለሚመጣው መልዕክተኛ መንገድ ጠራጊ በነበረው ባብና በሁሉም ሃይማኖቶች ቃል በተገባለት ባሃኡላህ የሰው ልጆች የእግዚአብሔርን ገጽ እንዲመለከቱ ጥሪ ቀርቦላቸዋል፡፡
Interesting blog? Like it on Facebook, +1 on Google, Tweet it or share this article on other bookmarking websites.