የእግዚአብሔር መሠረታዊ ባሕርይ የማይታወቅ ቢሆንም የፀጋው ምልክት በያለበት በግልጽ ይታያል። “የመጀመሪያው ምክንያት” ሊታወቅ ባይችልም የመኖሩ ኃይል ለመላው አካላችን ይሰማናል። የሰዓሊውን ስዕል ማየት ለተቺው የሰዓሊውን ዕውቀት እንደሚያስረዳው ሁሉ፥ የሁለንተን ዓለም ዕውቀት ወይም የሰው ባሕርይ እንዲሁም የሚታዩና የማይታዩ ነገሮችን ማወቅ የእግዚአብሔርን ጥበብ ማወቅ ነው። ይህም መለኮታዊ እውነትን ለሚመረምር እውነተኛውን የእግዚአብሔርን ክብር ለማወቅ ይረዳል።
“ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፥ ጠፈሮችም የእርሱን የእጅ ሥራ ይገልጻሉ፥ ቀን ለቀን ይናገራል። ሌሊትም ለሌሊት ዕውቀት ያሳያል።” (መዝ.19 1-2)
መለኮታዊ ክስተቶች
የፀሐይ ብርሃን የሚያርፍባቸው ነገሮች ሁሉ ብርሃንን አነሰም በዛ እንደሚያንጸባርቁ ሁሉ ማናቸውም ነገር የእግዚአብሔርን ጸጋ አነሰም በዛ በግልጽ ያሳያል። የከሰል ክምር አነስ፥ ድንጋይ ከፍ፥ የኖራ ድንጋይ ከዚያ በለጥ ያለ ብርሃን ያንጸባርቃሉ። ሆኖም ከነዚህ በማንኛቸውም ነፀብራቅ ደማቁን የፀሐይን መልክና ቀለም ልናይ አንችልም። ንፁሕ መስተዋት ግን ፀሐይን እራሷን እንደምናያት ያህል መልኳንና ቀለሟን ሊያሳየን ይችላል። ሌሎችም ነገሮች ስለእግዚአብሔር የሚነግሩን በዚህ ዓይነት ነው። ድንጋይ ስለመለኮታዊ ባሕርይ ሊነግረን ይችላል። አበባ በለጥ አደርጎ ይገልጽልናል። አስደናቂ ባሕርያት፥ ስሜትና፥ እንቅስቃሴ ያላቸው እንስሳት ደግሞ ከዚያም በበለጠ ይነግሩናል። በታናናሾቹ መሰል ወንድሞቻችን የፈጣሪን አስገራሚነት የሚናገሩ አስደናቂ የሰውነትክፍሎች እናገኛለን። በባለቅኔው፥ በቅዱሳን፥ በጠበብቱ ታላላቅ የእግዚአብሔር መገለጫዎች እናያለን። ሆኖም ታላላቁ ነብያትና የሃይማኖት መሥራቾች የእግዚአብሔር ፍቅርና ጥበብ ለመላው ሰው ልጅ የሚገለጥባቸው ንፁሕ መስተዋቶች ናቸው። የሌሎቹ ሰዎች መስተዋቶች በከንቱ ጥላቻና በራስ ወዳድነት ጉድፍ ቦዘዋል። ነቢያቱ ግን ንጹሕና እንከን የሌላቸው ለእግዚአብሔር ፈቃድ በሙሉ ያደሩ ናቸው። ስለዚህ የሰው ዘር ታላላቅ መምህራን ይሆናሉ።
እግዚአብሔር ሰውን በሌላ ሰው ላይ አድሮ ስለሚረዳ መለኮታዊው ትምህርትና የመንፈስ ቅዱስ ኃይል በእነርሱ ላይ እየሰፈነ የሰው ልጅ ሥልጣኔ ምክንያት ይሆናሉ፥ቀድሞም ሆነዋል። በሕይወት መሰላል ከፍተኛ ሥፍራ ላይ የሚገኝ ማንኛውም ሰው ከበታች ለሚገኘው ሌላ ሰው ረዳት ነው። እጅግ በጣም ከፍተኛ ቦታ ላይ የሚገኙት ደግሞ ለጠቅላላው የሰው ልጅ ረዳቶች ናቸው። ይህም ሁኔታ ሰዎች በተለጣጭ ክሮች እርስ በርስ እንደተሳሰሩ ዓይነት ነው። ከጠቅላላው ኅብረተሰብ መካከል አንዱ ከፍ ሲል ክሩ ይሳባል። የቀሩት ጓደኞቹ መልሰው ወደታች ሊስቡት ይሞክራሉ። ግን በተመሳሳይ ኃይል እርሱ ደግሞ ወደ ላይ ይስባቸዋል። ከፍ እያለ በሄደ ቁጥር የዓለም ሸክም የበለጠ እየከበደውና ወደታች እየሳበው ይሄዳል። ይህም በሆነ ቁጥር ከእርሱ ከፍ ብለው በሚገኙት ሰዎች በኩል የበለጠ የመለኮት ድጋፍ ያሻዋል። እነዚህን የመሳሰሉት ሰዎች ሁሉ ከፍተኛውን ሥፍራ የያዙት እነዚያ በየዘመናቸው አለአንዳች ምድራዊ ድጋፍና ጓደኛ የመላውን ዓለም ክብደት በእግዚአብሔር ኃይል የተሸከሙት ንጹሐን ነቢያት፥ መድኃኒቶችና፥ የመለኮት “ክስተቶች” ናቸው። “የኃጢአታችን ሸክም በእርሱ ላይ ነበር” የሚለው ትምህርት ሁሉንም ነቢያት ይመለከታል። እያንዳንዱ ለተከታዮቹ “ዕውነትም፥ ሕይወትም፥ መንገድም ነው።” እያንዳንዱ ለሚቀበለው ልብ ሁሉ የእግዚአብሔር በረከት መውረጃ አሸንዳ ነው። እያንዳንዳቸው እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ዕድገት ባዘጋጀው መንገድ ተካፋይ ነበሩ።
Interesting blog? Like it on Facebook, +1 on Google, Tweet it or share this article on other bookmarking websites.