“እናንተ በምድር ላይ ነዋሪዎች ሆይ! ይህን ታላቅ ግልጸት ልዩ የሚያደርገው ዓይነተኛ ገጽታ በአንድ በኩል የሁከት፥ የክፋት፥ የተንኮል ምክንያቶችን ከእግዚአብሔር መጽሐፍ መፋቃችን ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የስምምነት፥ የመግባባት፥ የፍጹምና ዘላቂ አንድነትን መሠረታዊ ቅድመ ሁኔታዎች መደንገጋችን ነው። ትእዛዞችን በግብር ላይ ያዋሉ ደስተኞች ናቸው።” (ባሃኦላህ ታብሌት ኦፍ ዘ ዎርልድ በሚል መልእክቱ)
በአሥራ ዘጠነኛው ምዕተ ዓመት የሃይማኖቶች መከፋፈል
ከአሥራ ዘጠነኛው ምዕተ ዓመት ይበልጥ ዓለም ከሃይማኖት አንድነት የራቀበት ጊዜ ያለ አይመስልም። ለብዙ ምዕተ ዓመታት ዞሮአስትራውያን፥ኦሪታውያን፥ ቡዲስቶች ክርስቲያኖች፥ እስላሞች እንዲሁም ሌሎች የሃይማኖት ድርጅቶች ጎን ለጎን ኖሩ። ይሁን እንጂ ተስማምቶ አንድ በመሆን ፈንታ በማያቋርጥ ጠላትነትና ግጭት ኖሩ። በዚህ ብቻ ሳይወሰኑ እያንዳንዱ ሃይማኖት አንዱ ሌላውን አጥብቆ በሚቃወም ቁጥራቸው ብዙ በሆነ አነስተኛ ክፍሎች ተከፋፈሉ። ነገር ግን ክርስቶስ እንዲህ ሲል አስተምሯል፦ “እርስ በርሳችሁ ተፋቀሩ፥ ደቀ መዛሙርቶቼ መሆናችሁ በዚህ ይታወቅ ዘንድ”። ሙሐመድም እንዲህ ብሎአል፦ “ይህ ሃይማኖታችሁ ያው አንድ ሃይማኖት ነው፥ ... እግዚአብሔር ኖህን ያዘዘው ለናንተ ለተላከ መልእክት ነው። እኛ ለእናንተ ለገለጽነው እንዲህም ስንል አብርሃምን፥ ሙሴንና ክርስቶስን ያዘዝነው፥ ‘ይህንን እመምነት ተከተሉ፣ በሃይማኖቱም ስም ከመከፋፈል ተጠበቁ፤’ ስንል ነው።”
የእያንዳንዱ ታላላቅ ሃይማኖት መሥራች ተከታዮቹ እንዲስማሙ አስተምሯል። ሆኖም በሁሉም ዘንድ የመሥራቾቹ ዓላማ በአክራሪነት፥ በአለመቻቻል፥ በቀኖናዊነት፥ በግብዝነት፥ በኢ-ሥነምግባራዊነት፥ በማደናገር፥ በመከፋፈልና በፉክክር ፈለጉ ጠፍቷል። ስምምነት የሌላቸው የሃይማኖት ክፍሎች ብዛት ከማንኛውም ጊዜ ይበልጥ በዓለም ላይ ገኖ የታየው በባሃኢ እምነት መገለጽ መባቻ ነበር። በዚያን ጊዜ የሰው ልጆች በተለያዩ ሃይማኖታዊ እምነቶች፥ በተለያዩ የስግደትና የአምልኮ ሥርዓቶች፥ በተቻለ መጠን በሁሉ የሞራል ሕግጋት ሙከራና ልምምድ የሚያደርጉ ይመስል ነበር።
በዚያን ጊዜ የተፈጥሮን ሕግና የእምነትን መሠረታዊ አቋም ለማወቅ ያለፍርሃት የሚደክሙ ሰዎች ቁጥር እየበዛ ይሄድ ነበር። አዳዲስ የሳይንስ ጥበብ እያደገ፥ ያልተለመዱ የኑሮ ችግሮችም አዳዲስ መፍትሔ እየተገኘላቸው ይሄድ ጀመር። በእንፋሎት ኃይል የሚንሳፈፉ መርከቦችን፥ ባቡርን፥ የፓስታ አገልግሎትን፥ ማተሚያ ቤቶችን የመሳሰሉ በመፈልሰፋቸው ጠቃሚ ሃሳቦችንና የኑሮ ዘዴዎችን ለማሰራጨት ተችሏል።
“የሳይንስና የሃይማኖት ያለመስማማት” የተባለው ከፍተኛ የሃሳብ ግጭትን ፈጠረ። በክርስቲያን ዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ ምርምር ከሳይንስ ጥናት ጋር በመተባበር ለብዙ ምዕተ ዓመታት የእምነቱ መሠረት የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን መንቀፍ፥ አንዳንዴም ጨርሶ መቃወምን አስከተለ። ብዛት ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች በየቤተክርስቲያኖቹ ስለሚሰጡ ትምህርቶች ይጠራጠሩ ጀመር። ቁጥራቸው በዛ ያለ የሃይማኖቱ ቀሳውስት እንኳን በስውር ሆነ በግልጽ ስለየሃይማኖታቸው ሕግጋት ጥርጣሬና ቅሬታቸውን ይገልጹ ጀመር።
ከጥንት ሃይማኖትና የእምነት ባህል አለመሟላት ጋር ይህ ምስቅልቅልና ተለዋዋጭ የሆነ ሃሳብ በመጣመር በክርስቲያን አገሮች ብቻ ሳይሆን በሁሉም አገርና ሃይማኖቶች መሐከል ከሞላ ጎደል በልዩ ልዩ መልክ የተሟላ እውቀትንና መረጃን የመሻት እንቅስቃሴ ፈጠረ።
የባሃኦላህ መልዕክት
ይህ ግጭትና የምስቅልቅል ሁኔታ ከፍተኛ ደረጃ በደረሰበት ጊዜ ነው ባሃኦላህ ታላቁ የመልእክት ጥሪውን ለሰው ልጆች ያሰማው፦
“አገሮች ሁሉ በእምነት አንድ እንዲሆኑና በሰዎች ዘንድ ወንድማማችነት እንዲፈጠር የፍቅር ሰንሰለትና አንድነት በሰው ልጆች መካከል እንዲጠነክር የሃይማኖት መከፋፈል እንዲወገድና የዘር ልዩነት ፈጽሞ እንዲጠፋ... ። እነዚህ ብጥብጥ፥ አለመግባባትና ደም መፋሰስ ይወገዱ ፥ ሰዎችም አንድ ወገንና አንድ ቤተሰብ ይሁኑ...” (ለፕሮፌሰር ብራውን ከተነገሩት ቃላት)
መልእክቱ ከብዙ ሺህ ዘመን ጀምሮ ነቢያት የሰበኩት፥ ደራሲያን ያዜሙትና ቅዱሳት የጸለዩለት ታላቅ መልእክት ነው። የሃይማኖት መለያየት ግን አልቀረም፥ ፀብ፥ ደም ማፋሰስና ጥላቻ አልተወገደም። እንደዚህ ከሆነ ይህ መልእክት እንደምን በሥራ ላይ ለመዋል ይችል ይሆን? አሁን ተአምራቱ የሚፈጸም ለመሆኑ ምን መረጃ አለ? ተጨማሪ የሆነ አዲስ ነገር አለን? የሰው ተፈጥሮስ ጥንት እንደነበረና፥ ዓለም እስካለ ድረስ በተመሳሳይ ሁኔታ የሚቀጥል አይደለምን? ሁለት ሰዎች ወይንም ሁለት መንግሥታት አንድን ነገር የተመኙ እንደሆነ ሲደረግ እንደቆየው ሁሉ ያንን የተመኙትን ነገር ለማግኘት አይዋጉበትምን? ሙሴ፥ ቡድሃ፥ ክርስቶስና ሙሐመድ የዓለምን አንድነት ለመመሥረት ካልተቻላቸው ባሃኦላህ ይችል ይሆን? ያለፉት ሃይማኖቶች እንደጎደፉና እንደተከፋፈሉ ሁሉ የባሃኢ ሃይማኖትስ ይህ ዕድል አይገጥመው ይሆን? የባሃኢ ትምህርቶች ለእነዚህና እነዚህን ለመሳሰሉ ጥያቄዎች ምን መልስ እንደሚሰጡ እስቲ እንመርምር።
Interesting blog? Like it on Facebook, +1 on Google, Tweet it or share this article on other bookmarking websites.