እነዚያ በእምነት መንገድ የሚራመዱት፣ እነዚያ የእርግጠኝነትን የወይን ጠጅ የሚጠሙት፣ ራሳቸውን ምድራዊ ከሆነው ነገር ሁሉ፣ ማለትም ጆሮዎቻቸውን ከማይረባ ወሬ፣ አእምሮዎቻቸውን ከከንቱ አስተሳሰብ፣ ልቦቻቸውን ከዓለማዊ ፍቅር፣ ዓይኖቻቸውን ከሚጠፋው ነገር ሁሉ ማንጻት አለባቸው። እነርሱ እምነታቸውን በአምላክ ላይ በማድረግ፣ እርሱንም አጥብቆ በመያዝ መንገዱን መከተል አለባቸው። ከዚያም ለመለኮታዊው የዕውቀትና የመረዳት ፀሐይ አንጸባራቂ ጸጋዎች ብቁ ይደረጋሉ፣ ወሰን የሌለውንና የማይታየውንም ጸጋ ተቀባዮች ይሆናሉ፤ ምክንያቱም፣ አምላክንና ነቢያቱን በትክክል ለመረዳትና ለማወቅ፣ የሟች ሰዎችን ቃላትና ተግባራት እንደመለኪያ አድርጎ መቁጠርን እስካላቋረጠ ድረስ፣ ማንም የንዑዱ ዕውቀት ወደሆነው ለመድረስ ተስፋ ለማድረግ፣ ከመለኮታዊውም ዕውቀትና ጥበብ ወንዝ ረክቶ ለመጠጣት፣ ወደ ሞት-አልባነትም መኖሪያ ለመግባት፣ ከመለኮታዊው ቅርበትና ችሮታ ጽዋም ለመካፈል ከቶ አይችልምና።
ያለፈውን ጊዜ አስታውስ። በሁሉ ጊዜያት፣ የእግዚአብሔርን ክስተቶች፣ የእርሱ ኅሩያንን የተቀደሱ ስብእናዎች ተላብሰው መምጣት፣ ስንቶቹ፣ ትልቁም ትንሹም፣ በናፍቆት ተጠባበቁ። መምጣቱን የጠበቁት እንዴት ብዙ ጊዜ ነበር፣ የመልኮታዊ ምሕረት ነፋስ እንዲነፍስና ያ ምፅዓቱ በተስፋ የሚጠበቀው ውበት ከድብቅነት ወጥቶ ለዓለም ሁሉ እንዲገለጽ የጸለዩት እንዴት ብዙ ጊዜ ነበር። የጸጋ በሮች በተከፈቱ፣ የመለኮታዊ በረከት ደመናዎች በሰው ዘር ላይ በዘነቡና የሥውሩ ብርሃን ከመለኮታዊው ኃይል አድማስ በላይ በአበራ ቁጥር ግን፣ ሁሉም ካዱት፤ ከእርሱም ፊት፣ ከእግዚአብሔር ከራሱ ፊት፣ ፊቶቻቸውን አዞሩ። የዚህን እውነትነት ለማረጋገጥ፣ በእያንዳንዱ ቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ የተጻፈውን ተመልከቱ።
አንድ ጊዜ አሰላስል፤ ለእነዚያ ያንን በሚያህል ቅንነትና ናፍቆት ሲመራመሩ ለነበሩት፣ የዚህ ዓይነቱ ክህደት ምክንያቱ ምን እንደነበረ ለመረዳት በጥልቀት አብሰልስል። ያደረሱት ጥቃት አንደበት ወይም ብዕር ሊገልጸው ከሚችለው በላይ የከፋ ነበር። በተከሰተበት ወቅት በዙርያው በነበሩ ሕዝቦች ክህደት፣ እምቢታና ከባድ ተቃውሞ ያልተሠቃየ አንድም የቅድስና ክስተት የለም። ይህ የሚከተለው ጥቅስ የተገለጸው ለዚሁ ነበር፦ “አዬ የሰዎች ምስኪንነት! በመጣበት ጊዜ በፌዝ ያልተሳቀበት መልእክተኛ የለም” 1 እንደገናም እንዲህ ይላል፦ “የእያንዳንዱ አገር ሕዝብ መልእክተኛቸውን በኃይል ለመያዝ በስውር አስረዋል፤ እውነቱንም ዋጋ ለማሳጣት በከንቱ ቃላት ተከራክረዋል።”
በተመሳሳይ ሁኔታ፣ እነዚያ ከኃይል ምንጭ የፈሰሱትና ከክብር ሰማይ የወረዱት ቃላት ሥፍር ቁጥር የሌላቸውና ከሰው ተራ ግንዛቤ በላይ ናቸው። ለእነዚያ በትክክል ለመረዳትና በጥልቀት ለማየት ችሎታ ላላቸው ሰዎች የሁድ ምዕራፍ (ሱራ) በእርግጥ ይበቃል። እነዚያን ቅዱሳት ቃላት ለአንዳፍታ በልብህ አሰላስል፤ ፍፁም በሆነ መላቀቅም ትርጉማቸውን ለመጨበጥ ተጣጣር። ምናልባት፣ የሰብአዊ ልብ ወፍን በረራ ከደንታቢስነትና ከጥርጣሬ መኖርያዎች ርቃ ወደ እምነትና እርግጠኝነት ጎጆ ለመክነፍ፣ ከጥንታዊውም የጥበብ ንጹህ ውሀዎችን በጥልቀት ለመጠጣት፣ ከመለኮታዊ ዕውቀት ዛፍ ፍሬም ለመካፈል ታስችላት ዘንድ፣ የነቢያትን ድንቅ ጠባይ መርምር፤ በአሉታና በሐሰተኝነት ልጆች የተነገሩትንም የስም ማጥፋት ድርጊቶችና ክህደቶች አስታውስ። የልበ-ንጹሐን ድርሻ የሆነው፣ ከዘለዓለማዊነትና ከቅድስና ግዛቶች የወረደው ኅብስት እንዲህ ያለ ነው።
በእግዚአብሔር ነቢያት ላይ የተከመሩትን ውርደቶች መርምረህ ብታውቅና በጨቋኞቻቸው የተሰነዘሩባቸውን ቅዋሜዎች እውነተኛ ምክንያቶች ብትረዳ፣ በእርግጥ የሁኔታቸውን ምንነት ትገነዘባለህ።
ከዚህም በላይ፣ የእነዚያን የመለኮታዊ ባሕርያት ክስተቶችን ተቃዋሚዎች ክህደት ይበልጥ በቅርበት በአስተዋልክ ቁጥር፣ በአምላክ እምነት ላይ ያለህ እምነትህ ይበልጥ የጠነከረ ይሆናል። ስለዚህ፣ ቀድሞ በነበሩት ዘመናትና ምዕተ ዓመታት ሁሉ፣ የሥልጣንና የክብር ክስተቶች፣ ምንም ብዕር ሊገልጻቸው ለማይደፍራቸው አሰቃቂ ጭካኔዎች ለመዳረጋቸው እውነቱን ይገልጹ ዘንድ፣ በዚህ መልእክት ውስጥ የአምላክን ነቢያት በተመለከተ፣ የተለያዩ ታሪኮች በአጭሩ ይጠቀሳሉ። እነዚህም፣ ምናልባት አንዳንዶቹን፣ በቀሳውስትና በዚህ ዘመን ቂሎች ጩኸትና ቅዋሜዎች ከመሸበር ለመዳን፣ እምነታቸውንና እርግጥኝነታቸውንም ለማጠናከር ያስችሏቸው ይሆናል። (ባሃኦላህ;የእርግጠኝነት መጽሐፍ)
Interesting blog? Like it on Facebook, +1 on Google, Tweet it or share this article on other bookmarking websites.