ሐይማኖት የሰው ልጅ በስጋውና በነፍሱ እንዲሻሻል የሚረዳ መለኮታዊ ዕውቀት የሚገበይበት መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ነው፡፡ የዚህም ትምህርት መስራች እግዚዓብሔር ነው፡፡ የሰው ልጆች ብልፅግናንና ደስታን ከፈለጉ በዚህ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ውስጥ ማለፍ አለባቸው፡፡ መጀመሪያ አንድ ሰው ፊደል ወደሚቆጥርበት ትምህርት ቤት መሄድ አለበት፡፡ ከዚያም አንዱን ደረጃ ከአስተማሪው ደግነትና ጥንቃቄ ካለፈ ወደሚቀጥለው ደረጃ ይዛወራል፡፡ በዚህም ሌላ ደግና ርሁሩህ መምህር ስለሚያጋጥመው የመጀመሪያው ደረጃ መሰረት በማድረግና አዲስ እውቀት በመጨመር ትምህርቱን ይቀጥላል፡፡ አእምሮውና ሰውነቱ በአስተማሪው መሪነት በዚሁ ተምህርት ቤት ውስጥ ይዳብራል፡፡
እነዚህ በተለያዩ የትምህርት ደረጃዎች የሚያስተምሩት አስተማሪዎች አንዱ ከሌላው ይበልጣል ማለት እንችላለን? በመጀመሪያ ደረጃ የሚያስተምረንን አስተማሪ ስለወደድነው ብቻ በሁለተኛ ደረጃ የሚያስተምረንን አስተማሪ መጥላት እንችላለን ወይ? በአንደኛ ደረጃ የተማርነው ትምህርት በሁለተኛ ደረጃ ከተማርነው ይሻላል ለማለት እንችላለን ወይ? አንችልም! እነዚህ የተለያዩ ደረጃዎች የሚገኙ በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ ነው፡፡ የሚከተሉት የማስተማር ዘዴ አይለያዩም፤ ግን እድሚያችንና ችሎታችን እንደየደረጃው ይለያያል፡፡ እድሚያችን ስድስት ዓመት በነበረ ጊዜ ችሎታቸንም በዚያው መጠን ያነሰ ነበር፡፡ ስለሆነም ብልሁ የትምህርት ቤቱ መስራች አስተማሪውን ከእድሜያችንና ከችሎታችን ጋር የተመጣጠነ ትምህርት እንዲሰጠን መከረው፡፡ በየደረጃው የተማርነው ትምህርት በዚያ እድሜያችን ማግኘት የምንችለው ያክል ነበር፡፡ በሃይማኖትም ረገድ ይሄው ነው፡፡ እግዚአብሔር አንድ ነው፡፡ የእርሱም ሃይማኖት ትምህርት ቤት አንድ ነው፡፡ በተለያየ እድሜ የተለያየ ችሎታ ያለን ግን እኛ ነን፡፡
መለኮታዊ መምህሮቻችን ማለትም የእግዚአብሔር መልእክተኞች ብልሆች ናቸው፡፡ የሁሉም ዓላማ አንድ ነው፡፡ ይሄውም እኛ በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ እንድንራመድ መርዳት ነው፡፡ የሰው ልጅ ግን ከዘመኑ ጋር እያደገ በመሄዱ የችሎታውም መጠን ተለዋውጧል፡፡ የዚህን ጥበባዊ እርምጃ እግዚአብሔር በሰጠን መልእክተኞች አማካኝነት መመልከት አለብን፡፡
ያስተማረንን መምህር በመውደዳችን ምክንያት በአንድ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ራሳችንን መወሰን የለብንም፡፡ ራሳችንን በአንድ ደረጃ ከወሰነው ለአስተማሪያችን እውነተኛ ፍቅር ሰጠነው ለማለት አንደፍርም፡፡ የእኛ በአንድ ደረጃ መወሰን እርሱን ያሳዝነዋልና፡፡ እርሱ ወደፊት ገፍተን በሚቀጥሉት ደረጃዎች ውስጥ አዲስ ዕውቀት እንድንገበይ ይፈልጋል፡፡ ይህም ማለት የአንዱ መምህር ዕውቀት ከሌላው ያንሳል ማለት አይደለም፡፡ ሁሉም ያላቸው ዕውቀት ልክ አይበላለጥም፡፡ ሁሉም ብልህና ተፈላጊ ናቸው፡፡ ብልሆች ስለሆኑ በአንድ ጊዜ መቀበል የምንችለውን እውቀት መጥነው ይሰጡናል፡፡ የተቻለንን ከሰራንና ትምህርታቸውን በሚገባ ከተከተለን ከፍ ወደ አለ የእውቀት ደረጃ የሚመራን መምህር እንደሚኖረን ይነግሩናል፡፡ የሚቀጥለውም መምህራችንም በተራው ከእሱ በፊት የነበረውን መምህር ጥረትና ችሎታ ያመሰግናል፡፡ በዚህ መሰረት የእግዚአብሔር መልእክተኞች ከነርሱ በፊት የነበሩትን የእግዚአብሔር መልእክተኞች እያመሰገኑ ከነርሱ በኋላ የሚመጣው መልዕክተኛ ደግሞ በእውቀትና በትምህርት ላቅ ወደአለና ወደተሻለ ደረጃ እንደሚያደርሰን ተናግረዋል፡፡
ባሃኡላህ ሲያስተምረን የሃይማኖቶች ሁሉ ምንጭ አንድ ነው ይላል፡፡ በማንኛውም ት/ቤት የሚማረው አማኝ ዋና አላማው እውነተኛና ሩህሩህ ለመሆን ነው፡፡ ወደ ከፍተኛ ደረጃ በምንሸጋገርበት ጊዜ እነዚህ መሰረታዊ ሕግጋት አይለወጡም፡፡ ነገር ግን በአንደኛ፤ በሁለተኛና በሶስተኛ ደረጃ እነዚሁ መለኮታዊ ፀጋዎች ሁልጊዜ ይመሰገናሉ፡፡ እነዚህ እውነተኝነታቸው በጊዜ ብዛት የማይለወጥና ዘላለማዊነት ያለው መሰረቶች ናቸው፡፡ ሆኖም መሰረት ብቻውን በቂ አይደለም፡፡በዚህ መሰረት ላይ በየጊዜው የሚያስፈልጉን አንዳንድ ነገሮች መገንባት አለባቸው፡፡ ሃይማኖትም የሚያስተምረው ይህንኑን ነው፡፡ ሃይማኖት የሰውን እውቀትና ችሎታ ወደከፍተኛ ደረጃ እንዲያደርስ ያደርገዋል፡፡ ይህንንም ሲያደርግ ህግጋቱን የሚገነባው ቀደም ካሉት የእግዚአብሔር መልዕክተኞች ባገኘው እውቀት መሰረት ላይ ነው፡፡ ይህም ማለት በልጅነታችን ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ የሚሰጠው የሂሳብ ትምህርት መሰረቱን የሚያገኘው በዝቅተኛ ደረጃ ከተማርነው ትምህርት ነው፡፡
አሁን የምንኖርበት ዘመን ካለፉት ዘመናት የሰው ሃይልና ችሎታ በከፍተኛ ደረጃ የሚለይበት ጊዜ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር እውቀት በብዛት ለመካፈል ዛሬ እድል አግኝተናል፡፡ ይሄውም የዘመኑ የእግዚአብሔር ክስተት/ መልእክተኛ/ በሆነው በባሃኡላህ ( ክብረ አምላክ) አማካኝነት ነው፡፡
ባሃኡላህ የእግዚአብሔር አንድነት፤ የሃይማኖት አንድነት እና የሰው ልጆች አንድነትን ያስተምራል፡፡ እርሱም ያለፉትን የእግዚአብሔር መልእክተኞችን ያመሰግናል፡፡ የእግዚአብሔር መልእክተኞች ወርቃማ ሰንሰለት በባሃኡላህ አማካኝነት ተያይዟል፡፡ ይህም የሚያስደንቅ ታሪክ ነው፡፡
READ MORE: http://www.bahai.org/
Interesting blog? Like it on Facebook, +1 on Google, Tweet it or share this article on other bookmarking websites.