"እናንተ ሁላችሁም የአንድ ዛፍ ፍሬዎች፣ የአንድ ቅርንጫፍ ቅጠሎች፣ የአንድ አትክልት ሥፍራ አበቦች ናችሁ።” ባሃኡላህ
የባሃኢ እምነት ዋነኛ አላማው፥ ዘር፣ ብሔር፣ ሀገር፣ ፆታ፣ እንዱሁም ሀይማኖት ሳይለይ የመላው የሰው ዘርን አንድነት እና ሁለንተናዊ ሰላም መመስረት ነው። የግለሰቦችን መንፈሳዊ ሕይወት በማሳደግ ከራስ ወዳድነት የነፃ አገልግሎት ለሰው ልጆች እንዲያበረክቱ ለማስቻል ያለመ ነው። የማህበረሰቡ አባላት ለህብረተሰቡ ደህንነት እና እድገት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማድረግ በአገልግሎት ተግባራት ላይ በንቃት ይሳተፋሉ። የባሃኢ እምነት በዚህ ዘመን የሰው ልጅ በአዲስ የመንፈሳዊ እና የማህበራዊ እድገት ዘመን ውስጥ እንዳለ ያስተምረናል። ስለዚህ በሀገሮች እና ህዝቦች መካከል አንድነት እና ትብብር፣ ዓለም አቀፋዊ ሰላም ለመመስረት ጊዜው አሁን ነው።
የኢትዮጵያ ባሃኢዎች ልክ እንደ አለም አቀፉ የባሃኢ ማህበረሰብ ሁሉ በሚገባ በተቀናጁ ጥረቶቻቸው እና ዓለምን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ከሚተጉ ከብዙ ሰዎች ጋር በመተባበር በአንድነት ላይ የተመሰረቱ ንቁ ማህበረሰቦችን ለመገንባት ጥረት ያደርጋሉ። እድሜ፣ ጾታ ወይም ሀይማኖት ሳይለይ እያንዳንዱ የማህበረሰብ ክፍል ለራሱ እና ለአካባቢው እድገት ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ የሚያስችሉትን የተለያዩ አስተምህሮቶችን እና ስልቶችን የባሃኢ እምነት ለአለም እያበረከተ ይገኛል።
የባሃኢ ማህበረሰብ ትምህርታዊ ጥረቶች የሚያተኩሩት በሁሉም የእድሜ ክልል የሚገኙ ግለሰቦችን መንፈሳዊ እና አእምሯዊ ችሎታዎቻቸውን በማሳደግ ለሚኖሩበት ማህበረሰብ አዎንታዊ አስተዋፅዖ እንዲያበረክቱ ለማስቻል ነው። ትምህርታዊ ሒደቶቹም፥ የህፃናት መንፈሳዊ ትምህርት፣ የታዳጊ ወጣቶች ፕሮግራም እና የጥናት ክበቦች ናቸው።
ለእግዚአብሔር ማደር መሰል ፍጡራንን ማገልገል ማለት ነው። ከዚህ በስተቀር በምንም መንገድ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ልንሆን አንችልም። ለመሰል ወንድሞቻችን ጀርባችንን ብንሰጥ ለእግዚአብሔርም እንዲሁ ማድረጋችን ነው።
ጸሎት አንዲት ነፍስ፡ ከፈጣሪዋ ጋር የምትገናኝበት፣ ለመንፈሳዊ እድገቷም መሰረት የሆነ የዕለት ተዕለት ምግቧ ነው። በግለሰብም ሆነ በማኅበረሰብ ወይም በተቋማት ደረጃ፣ ጸሎት የማህበረሰቡ የአምልኮ ሕይወት ዋነኛ መገለጫ እንደሆነ የባሃኢ እምነት ያስረዳል።
አለም አንድ ሀገር ናት
እርሱ አገሩን ስለወደደ መኩራራት የለበትም፥ ይልቁንም መላውን አለም እንጂ። ምድር አንድ አገር ናት የሰው ልጆችም ዜጎቿ ናቸው።
ባሃኡላህ
የሰው ዘር አንድነት
እናንተ ሁላችሁም የአንድ ዛፍ ፍሬዎች፥ የአንድ ቅርንጫፍ ቅጠሎች፥ የአንድ አትክልት ሥፍራ አበቦች ናችሁ።
ባሃኡላህ