በ2021 እ.ኤ.አ. ባሃኢዎች በአለም አቀፍ ደረጃ የአብዱል-ባሃ ዕርገትን 100ኛ አመት ያከብራሉ። በዓላቱ ከህዳር 27-28 በመላው አለም በከፍተኛ ድምቀት ይከበራል፡፡
የአምላክ መልእክተኛ ከዚህ ዓለም ሲለይ፣ የሃይማኖቱ መሪነት በመቀጠል ማን ላይ እንደሚያርፍ ያለው ጥያቄ ለሁሉም እምነቶች ወሳኝ ነበር። ይህንን ጉዳይ ለመፍታት አለመቻል ወደ ግጭት መምራቱና እና ሃይማኖቱ እንዲከፋፈል ማድረጉ አይቀሬ ነው። ለምሳሌ ከክርስቶስ እና መሐመድ በኋላ በክርስትና እና በእስልምና ሃይማኖተቶቹን ማን እንደሚመራቸው ግልጽ አለመሆኑ በየሃይማኖቶቹ ውስጥ መቃቃርን ፈጥሯል፣ ይህም ሊፈቱ ያልቻሉ ጥልቅ አለመግባባቶችን አስከትሏል።
ባሃኡላህ የሃይማኖቱን መከፋፈል ለማስወገድ፣ እርሱ ከዚህ ዓለም ሲለይ የመሪነት ስልጣን በበኩር ልጁ አብዱል-ባሃ ላይ እንዲያርፍ በቃለኑዛዜው ግልጽ መመሪያን አስቀምጧል፡፡ ከባሃኡላህ እርገት፣ 1892 እ.ኤ.አ. ጀምሮ፣ አብዱል-ባሃ በ1921 እ.ኤ.አ. ከዚህ ዓለም እስካለፈበት ጊዜ ድረስ የባሃኢ ማህበረሰብን ጉዳዮች መርቷል። በቅድስናው፣ በታላላቅ የበጎ አድራጎት ስራውና አገልግሎቱ ዝናን በማትረፍ፣ የባሃኡላህ እውነተኛ ተከታይ መለያ የሆነውን የመንፈስ ባህሪ አሳይቷል።
የአብዱል-ባሃ ስብዕና
‘አብዱል-ባሃ የባሃኡላህ የበኩር ልጅ ነበር፣ለባሃኢዎች እንደ ፍፁም አርአያ እና የእግዚአብሔር ምስጢር፣ የባሃኡላህ ትምህርት ህያው መገለጫ ነው።
አብዱል-ባሃ በልጅነቱ የአባቱን፣ የባሃኡላህን፣ መታሰርን አይቷል፤ እንዲሁም ከቤተሰቡ ጋር ከትውልድ አገራቸው ኢራን ወደ ባግዳድ ከዚያም ወደ የኦቶማን እስር ቤት ወደ ነበረው አቆር ተግዟል። በባሃኡላህ እስር ጊዜ አብዱል-ባሃ ቤተሰቡን እና ተከታዮቹን ተንከባክቧል፣ አባቱን በመጠበቅ አግዟል፣ እንዲሁም ድሆችን እና ችግረኞችን ተንከባክቧል። ባሃኡላህ ከእርሱ እርገት በኋላ ተከታዮቹ ወደ አብዱል-ባሃ እንዲዞሩ አዟቸዋል።
የአብዱል-ባሃ የእስር እና የግዞት ጊዜ ከወጣት ቱርክ አብዮት ጋር በተያያዙ ክስተቶች በ1908 እ.ኤ.አ. አብቅቷል። ወደ ግብፅ፣ አውሮፓ እና ሰሜን አሜሪካ ታሪካዊ ጉዞ አድርጓል። የእርሱ የአደባባይ ንግግሮች የባሃኢ እምነትን ዋና መልእክቶችን አስተላልፈዋል፣ እንዲሁም የሰላምን፣ የሴቶች እና የወንዶች እኩልነት፣ የዘር እኩልነት፣ ማህበራዊ ለውጦችን እና ሃይማኖት በህብረተሰብ ውስጥ ያለውን ሚና አላማ አጽንኦት በመስጠት ከሰው ልጅ አንገብጋቢ ፍላጎቶች ጋር አያይዘውታል።
የአብዱል-ባሃ ህልፈት
‘ኣብዱል ባሃ፣ በሃይፋ፣ ኅዳር 28 ቀን 1921 እ.ኤ.አ. ከሌሊቱ 1፡00 ሰዓት ላይ ከዚህ ዓለም ተለየ። የእርሱ ያለፈበት ቀን በየዓመቱ እንደ ባሃኢ ቅዱስ ቀን ይዘከራል።
የእርሱን ሕልፈት በተመለከተ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች ላይ ወጥቷል፡፡ በሃይፋ በተደረገው ስርዓተ ቀብሩ ላይ አይሁዶች፣ ክርስቲያኖች፣ ሙስሊሞች፣ ድሩዞች፣ ግብፃውያን፣ ግሪኮች፣ ቱርኮች፣ ኩርዶች እና አሜሪካዊያን፣ አውሮፓውያን እና ሌሎች ጓደኞቹን ጨምሮ ወደ አስር ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ተገኝተዋል።
ከአብዱል-ባሃ ህልፈት በኋላ የባሃኢ ማህበረሰብ ዕድገት
የአብዱል-ባሃ ጽሁፎች ከእርሱ እልፈት በኋላ የባሃኢ ማህበረብ የመርኆ ምንጭ መሆናቸውን ቀጥለዋል፡፡ በአለም ዙሪያ ለሚገኙ ባሃኢዎች፣ የባሃኢ አስተምሮቶችን ገጽታዎች የሚያብራሩ፣ የባሃኢ ማህበረሰብን መስፋፋት የሚያራምዱ፣ የአካባቢ ባሃኢ ተቋማትን ምስረታ የሚያበረታቱና በጅማሮ ደረጃ ያሉ ትምህርታዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስራ ተነሳሽነቶችን አቅጣጫ የሚያመላክቱ እጅግ በርካታ ደብዳቤዎችን ጽፏል፡፡
የአብዱል-ባሃ ቃለኑዛዜና ኪዳኑ የባሃኢ ማህበረሰብ አስተዳደራዊ ስርዓት መሰረት ሆኗል፡፡ በዚያ ውስጥም አብዱል-ባሃ የልጅ ልጁን፣ ሾጊ ኤፌንዲን፣ የባሃኢ እምነት ሞግዚትና መሪ አድርጎ ሰይሞታል፡፡ ስለ አመራራጡ ሁኔታና ስለስልጣኑ ተፈጥሮ በመዘርዘር የአለም አቀፍ ቤተ ፍትህ ምስረታ የሚዳስሱ የባሃኡላህን ጹሁፎች አብራርቷል፡፡ ቃለኑዛዜውና ኪዳኑ የየአገሩ የብሔራዊ መንፈሳዊ ጉባዔዎችን ምስረታ ራዕይ ፈጥሯል፡፡ ከአብዱል-ባሃ እልፈት በኋላ የባሃኢ እምነት በሁሉም አገሮች ውስጥ ተመስርቶ በተቋማትም ተዋቅሯል፡፡ በየአመቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የአካባቢ ባሃኢ ምርጫዎች ይዳሄዳሉ በተጨማሪም ብሔራዊ ጉባዔዎች ከ180 በሚበልጡ አገራት ይመረጣሉ፡፡
Interesting blog? Like it on Facebook, +1 on Google, Tweet it or share this article on other bookmarking websites.