የባሃኢ ሃይማኖትን በኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ያበሰሩት ሳብሪ ኤሊያስ በሚባሉ ግብፃዊ አማኝ አማካኝነት ነው። እኝህ ሰው በወጣትነታቸው እ.ኤ.አ በ1933 ዓ.ም በውስን አቅማቸውና የኢትዮጰያን ቋንቋዎችን ባለማወቃቸው ሳይገቱ የባሃኢ ሃይማኖትን ለማስተማር ወደ ኢትዮጵያ መጡ።
በልብስ ስፌት ስራም እየተዳደሩ ጎን ለጎን ሃይማኖቱን ማስተማር ጀመሩ። ከብዙ ጥረት፣ ልፋትና ፈተናም በኋላ አንዳንድ የኢትዮጵያ ሰዎች ሃይማኖቱን መቀበል ጀመሩ። ከዚያም እ.ኤ.አ በ1934 ከባሃኢ ሃይማኖት የአስተዳደር ተቋም ከሆኑት አንዱ የሆነውን “የአካባቢ መንፈሳዊ ጉባዔ” የተሰኘውን ተቋም ለመጀመሪያ ጊዜ ለማቋቋም አስቻሉ። የአካባቢ መንፈሳዊ ጉባኤ በአንድ አካባቢ፣ መንደር ወይም ከተማ ያሉ የባሃኢ ማህበረሰብን ጉዳዮች የማስተዳደር ሃላፊነት ያለው አስተዳደራዊ እና መንፈሳዊ አካል ነው። ይህ ተቋም ዘጠኝ አባላት ያሉበት ሲሆን በዓመት አንድ ጊዜ ከ21 ዓመት እና ከዚያ በላይ ባሉ አማኞች ይመረጥ ነበር። (ከ2021 እ.ኤ.አ. ጀምሮ አለም አቀፍ ቤተፍትህ ይህንን ዕድሜ ወደ 18 አውርዶታል፡፡)
እ.ኤ.አ በ1935 በጣሊያን ወረራ አማካኝነት በሃገሪቱ በተከሰተው ብጥብጥና አለመረጋጋት ሳቢያ ሳብሪ ኤሊያስ ወደ ትውልድ ሀገራቸው ግብፅ ለመመለስ ተገደዱ። ነገር ግን እ.ኤ.አ በ1944 ሳብሪ ኤሊያስ ከባለቤታቸው ወ/ሮ ፋሂማ ያኩት እና ከሁለት ወንድ ልጆቻቸው ሁሴንና ሳፋ ጋር ወደ ኢትዮጵያ ለመኖር መጡ። በዚህ ጊዜ ሃገሪቱ በጣሊያን ወረራ ምክንያት ብዙ ችግር ውስጥ ገብታ ስለነበረች ሁሉንም ነገር ቀድሞ እንደነበሩት ሊያገኙት አልቻሉም።
እሳቸው በነበሩበት ወቅት እምነቱን የተቀበሉትን ሰዎች ሊያገኟቸው አልቻሉም። እምነቱን እንደገና በዚህች የተቀደሰች ሃገር ለማስፋፋት ጥረት ጀመሩ። ወዲያውኑም የጃንሆይ (ንጉስ ሃይለስላሴ) ፍርድ ሸንጎ የህግ ሰው የነበሩት ቀኝ አዝማች ጊላ ሚካኤል ባህታ የተባሉ ሰው እምነቱን ተቀበሉ። እኚህም ሰው የእምነቱ ጠንካራ አማኝና አገልጋይ ሆኑ። በጥቂት ወራት ውስጥ የአማኞች ቁጥር እየጨመረ ሄደ።
በ1953 እ.ኤ.አ በአለም ዙሪያ የሚገኙ የባሃኢ ማህበረሰቦች የ10ዓመት እቅድ (ከ1953 – 1963) የተሰኘውን፣ እምነቱን በዓለም ሙሉ ለማስፋፋትና ለማጠናከር የተቀረፀውን የመጀመሪያውን አለማቀፋዊ እቅድ በይፋ ጀመሩ። በእነዚህ አስርት ዓመታት ውስጥ ባሃኢዎች በፕላኔቷ እያንዳንዷ ጫፍ ውስጥ እምነቱን ለማስፋፋትና ለማጠናከር ተሰራጩ። እ.ኤ.አ በ1953 ገደማ በርካታ ባሃኢዎች ከግብፅ፣ ከአሜሪካና ከኢራን ወደ ኢትዮጵያ ለዚሁ አላማ አገር አቅኚ (pioneer) ሆነው መምጣትጀመሩ።
እ.ኤ.አ በ1963 የሲቪል አቪየሽን፣ የዩንቨርስቲና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች እምነቱን በብዛት መቀበል ጀመሩ ። ለእነዚህ አዳዲስ አማኞችም የጥልቀት ትምህርት በእነዚህ አገር አቅኚዎችና ነባር አማኞች አማካኝነት መሰጠት ተጀመረ። ከዚህ በኋላ ጠንካራ የባሃኢ ማህበረሰብ መፈጠር ጀመረ።
እ.ኤ.አ በ1960 የአዲስ አበባ ማህበረሰብ በከፍተኛ ሁኔታ ማደግ በመጀመሩ ከባሃኢዎች መኖሪያ ቤቶች ወጥቶ በባሃኢ ማእከል ውስጥ እንቅስቃሴዎቹን ማካሄዱ የግድ ሆነበት። እ.ኤ.አ በ1962 ለባሃኢ ማእከል መስሪያ የሚሆን የመጀመሪያውን መሬት በግዢ አገኘ። በ10ዓመት ጊዜም የመጀመሪያው ብሔራዊ የባሃኢ ማእከል ተገንብቶ እ.ኤ.አ በ1972 ተመረቀ። በመቀጠልም የባሃኢ ማህበረሰቦችን ለማስፋፋትና ለማጠናከር በቢሾፍቱ፣ አዳማ፣ አምቦ፣ ሰበታ፣ ሆለታ፣ ወሊሶ፣ ሃዋሳ እና ጅማ ጥረት ተጀመረ።
ከሳብሪ ኤሊያስ ታላቅ ስኬት መካከል “ባሃኡላህና አዲሱ ዘመን” የተሰኘውን መፅሀፍ በ1934 እ.ኤ.አ ወደ አማርኛ ለማስተርጎምና ማሳተም መቻላቸው ነው። የመፅሀፉም ቅጅ በጊዜው ለነበሩ ቤተ መጽሃፍቶችና በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ባሃኢዎች ተሰራጭቷል። በ1936 እ.ኤ.አ የመፅሃፉ ቅጂ በወቅቱ የኢትዮጵያ መሪ ለነበሩት ንጉስ ሃይለስላሴ እየሩሳሌም በነበሩበት ወቅት ወ/ሮ ሎሮል ስቸፐፍሎቸር በተባሉ ካናዳዊ ባሃኢ አማካኝነት ተበርክቶላቸዋል።
ሳብሪ ኤሊያስ
Interesting blog? Like it on Facebook, +1 on Google, Tweet it or share this article on other bookmarking websites.