ለብዙዎቹ ወደ ሃይማኖት አንድነት ጎዳና ለመድረስ እንቅፋት የሆናቸው በልዩ ልዩ ነቢያት የተሰጠው የተለያየ መልእክት ነው። በአንዱ የተፈቀደው በሌላው የተከለከለ ነው። ስለዚህ ሁለቱም እንዴት ትክክል ይሆናል? እንዴትስ ሁለቱም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ይናገራሉ ሊባል ይቻላል?
እርግጥ ነው፤ እውነት አንድ ናት ልትለወጥም አትችልም። አዎን! ፍጹም እውነት አንድ ነው ሊለወጥም አይችልም፤ ግን ፍጹም እውነት ከሰው ልጆች ጊዜያዊ የመረዳት ችሎታ ወሰን በላይ እጅግ በጣም የራቀ ስለሆነ ለእርሱ ያለን ስሜትና አስተያየት በየጊዜው ያለማቋረጥ መለወጥ አለበት። የእግዚአብሔር ፈቃዱ ሆኖ የቀድሞው ያልተስተካከለ አስተያየት ጊዜው እንደመለወጡ መጠን በበለጠና በተስተካከለ አስተያየት እየተተካ ይሄዳል።
ባሃኦላህ ለአንድ ዞራስተራዊ በላከው መልእክቱ ላይ እንዲህ ይላል፦
“ሰዎች ሆይ! ቃላት የሚገለጹት ጀማሪዎች በመልካም ይራመዱ ዘንድ እንደየችሎታቸው መጠን ነው። የዓለም ህፃን ወደ ኃያሉ መንግሥት ኃብት በአንድነት አደባባይ ቦታውን ይይዝ ዘንድ የሚሰጠው ወተት በልኩ የተመጠነ መሆን አለበት።”
ከበድ ያለ ምግብ ይዋኻደው ዘንድ መጀመሪያ ለሕፃኑ ኃይል የሚሰጠው ወተት ነው። አንድ ነቢይ በአንድ በተወሰነ ጊዜ የሰጠው የተወሰነ ትምህርት ትክክል ነው ማለትና ሌላው ነቢይ ደግሞ ሌላ ትምህርት በሌላ ጊዜ ቢሰጥ ሃሳዊ ነው ማለት አዲስ ለተወለደ ሕፃን ወተት መልካም ምግብ ስለሆነ ይህንኑ ወተት እንጂ ከቶ ሌላ ምንም ዓይነት ምግብ ለአደገ ሰው መስጠት የማያስፈልግና ስህተት ነው እንደማለት ነው!
አብዱል-ባሃ እንዲህ ይላል፦
“እያንዳንዱ መለኮታዊ ግልጸት በሁለት ይከፈላል፦ የመጀመሪያው ክፍል አስፈላጊና የዘለዓለማዊው ዓለም ነው። የመለኮታዊ እውነቶችና አስፈላጊ ሕግጋት መታያና የእግዚአብሔር ፍቅር መግለጫ ነው። ይህ በሃይማኖቶች ሁሉ ያለ፥ የማይለወጥና የማይሻር ነው። ሁለተኛው ክፍል ዘለዓለማዊ አይደለም። ስለዕለት ተዕለት ኑሮ ሂደትና ሥራ ዝርዝር ነገር ስለሆነ እንደጊዜውና በነቢዩ ዘመን እንደሚገኘው የሰው ልጅ የማስተዋል ደረጃ መጠን ይለዋወጣል። ለምሳሌ ... በዘመነ ሙሴ የአንድ ሰው እጅ በትንሽ ስርቆት ምክንያት ይቆረጥ ነበር፤ ዓይን ያጠፋ ዓይኑን፥ ጥርስ የሰበረ ጥርሱን ይጣ የሚል ሕግ ነበር። በክርስቶስ ጊዜ ግን እነዚህ ሕግጋት አስፈላጊ ስለአልነበሩ እንዲሻሩ ተደረገ። በተመሳሳይ ሁኔታ የጋብቻ ፍች ይበዛ ስለነበር አንዳችም የሚቆጣጠረው ሕግ ባለመኖሩ ቅዱሱ ክርስቶስ ፍችን ፈጽሞ ከለከለ።
“እንደጊዜው አስፈላጊነት ቅዱስነቱ ሙሴም ለከፍተኛ ቅጣት አሥር ሕግጋት አወጣ። የእሥራኤል ልጆች በታህ ምድረ በዳ ስለነበሩና በዚያም የተቋቋመ የፍርድ ቤትና እስር ቤቶች ስለአልነበሩ ኅብረተሰቡን ለመጠበቅና የጋራ ጸጥታ ለማስገኘት አስቸጋሪ ነበር፤ በእነዚህም ምክንያት ጥብቅ ትዕዛዛት አስፈለጉ። በክርስቶስ ጊዜ ግን የዚህ ዓይነት ሕግ አላስፈለገም። የሃይማኖት የሁለተኛው ክፍል ታሪክ ስለኑሮ ባህል ስነ ሥርዓት ብቻ የሚናገር ስለሆነ በጣም አስፈላጊ አይደለም። የእግዚአብሔር ሃይማኖት መሠረት ግን አንድ ነው። ቅዱስነቱ ባሃኦላህም ይህንኑ መሠረት አድሶታል።” (ዲቫይን ፊሎሶፊ)
የእግዚአብሔር ሃይማኖት አንድ ነው፤ ሁሉም ነቢያት አስተምረውታል፤ ይህም ማለት ሕይወት ያለውና አዳጊ ነገር እንጂ ሕይወት አልባ፥ የማይለወጥ አይደለም። በሙሴ ትምህርት ሙሽራውን፥ በክርስቶስ ደግሞ አበባውን በባሃኦላህም ፍሬውን እናያለን። አበባው ሙሽራውን አያጠፋውም፤ ፍሬውም አበባውን አያበላሸውም። ማጥፋቱ ሳይሆን የሚቀጥለውን ደረጃ መፈጸሙ ነው። አበባው ይፈነዳ አንድ የሙሽራው ቅርፊት መውደቅ አለበት። ፍሬውም ያድግና ይበስል ዘንድ የአበባው ቅጠል መርገፍ አለበት። ስለሆነም የሙሽራው ቅርፊትና የአበባው ቅጠል የረገፉት ጥቅም ስለአልሰጡ ነውን? አይደለም! ሁለቱም በጊዜያቸው ትክክልና አስፈላጊዎች ነበሩ፤ ያለእነሱ አንዳችም ፍሬ ባልተገኘ ነበር። የነቢያት ትምህርቶችም እንደዚሁ ናቸው፤ የውጭ አካላቸው በየጊዜውና በየዘመኑ ይለወጣል፤ ግን እያንዳንዱ መገለጥ የፊተኛው ፍጻሜ ነው፤ የተለያዩና የማይገናኙም አይደለም፤ ግን የአንዱ ሃይማኖት ታሪክ የተለያዩ ደረጃዎች ሲሆኑ እነርሱም በበኩላቸው እንደዘር፥ እንደሙሽራና እንደአበባ ሆነው በአሁኑ ዘመን ወደ ፍሬነት ደረጃ ደርሰዋል።
የነቢያት ስህተት-አልባነት
ማንኛውም የነብይነት ደረጃ የታደለ ለመልእክቱ በቂ መረጃ እንደተሰጠው፥ ሰዎችም ሁሉ እንዲያዘዙለት፥ ከእርሱ በፊት የነበረውንም ትምህርት የመሻር፥ የመለወጥና የመጨመር ሥልጣን እንዳለው ባሃኦላህ ያስተምራል። ኢቃን ከተባለው መጽሐፍ የሚከተለውን እናነባለን፦
“ለፍጡራን መሪ ይሆን ዘንድ ከብዙዎች መካከል አንዱን መርጦ ሰፊ መለኮታዊ ምስጢሩን መደበቅ፥ በሌላ በኩል ደግሞ በእርሱ ለተመረጠው መመራት ያልፈቀዱትን ከባድ ቅጣት ማውረድ፥ ከለጋሱ ከእግዚአብሔር በረከት፥ ከመውደዱና ከይቅርታውም ጸጋ ምንኛ የራቀ ነው! የፍጡራን ሁሉ ጌታ፥ አያሌ በረከቱ ሁልጊዜም በክስተቶች አማካይነት በመለኮታዊ ሚስጢሩ ምድርንና በውስጧም ያሉትን ሁሉ አጠቃሎ ይዟል።
“... ደግሞስ፥ የእያንዳንዱስ ክስተት ምክንያት የሰውን ልጅ ጠቅላላ ባህርይ ለመለወጥ፥ ይህም ለውጥ በውስጥና በውጭ የሚታይ የውስጥን ህይወትና የውጭውንም ሁኔታ የሚነካ እንዲሆን አይደለም? የሰው ልጅ ባህርይም ካልተለወጠ የእግዚአብሔር ክስተቶች ሁሉ ከንቱነት ይገለጣል።” (ኪታቢ ኢቃን ገጽ 14 እና 240)
እግዚአብሔር ብቸኛው ስሕተት አልባና የሁሉም በላይ ነው። ነቢያቶቹም መልእክታቸው ከእግዚአብሔር ለዓለም የተላከ ስለሆነ ስሕተት አልባ ናቸው። ያም መልእክት በዚያው ወይም በሌላ ነቢይ ካልተለወጠ በስተቀር ምንጊዜም ቋሚ ነው።
የዓለምን በሽታ መርምሮ ትክክለኛ መድኃኒቱን ሊያዝ የሚችል ታላቁ ሐኪም እግዚአብሔር ብቻ ነው። ለአንድ ዘመን ታዞ የነበረው መድኃኒት የበሽተኛው ሁኔታ በተለወጠበት በሌላው ጊዜ ሊያገለግል አይችልም። ሐኪሙ ሌላ መድኃኒት ካዘዘ በኋላ አሮጌው መድኃኒት ላይ ሙጥኝ ማለት በሐኪሙ ላይ እምነት ማጣትና እንዲያውም አለመተማመን ነው። ሙሴ ከሦስት ሺህ ዘመናት በፊት ለዓለም በሽታ ፈውስ ያዘዘው ዛሬ ያረጀና የማይስማማ ነው ተብሎ ለአንድ አይሁድ ቢነገረው ያስደነግጠው ይሆናል። አንድ ክርስቲያንም ክርስቶስ በአዘዛቸው ትዕዛዛት ላይ ሙሐመድ የሚያክለው አስፈላጊና ጠቃሚ ነገሮች አሉ ቢሉት ያንኑ ያህል ይደነግጥ ይሆናል፤ እንዲሁም ደግሞ እስላሙ ባብ ወይም ባሃኦላህ የሙሐመድን ትዕዛዛት ለመለወጥ ሥልጣን እንዳላቸው ማመንና መቀበል ያዳግተዋል። ግን እንደባሃኢ አስተያየት በእውነት ለእግዚአብሔር መታመን ነቢያቱን ሁሉ ማክበርንና በአዲሱ ነቢይ ለዘመናችን የተሰጡትን ትዕዛዛት አክብሮ መቀበልን ያጠቃልላል። እውነተኛ አንድነት በእንዲህ ዓይነት ቅንነት ብቻ ሊገኝ ይችላል።
ታላቁ ክስተት እንደሌሎች ነቢያት ሁሉ ባሃኦላህ መልእክቱን ፍጹም በማያጠራጥር መንገድ ይገልጻል። በተለይ ለክርስቲያኖች በተላከው ሎውኢ-አቅዳስ በተባለው መልእክቱ እንዲህ ይላል፦
“በእውነቱ አብ መጥቶ በእግዚአብሔር መንግሥት የተሰጣችሁን ተስፋ ፈጽሟል። በአካባቢው የነበሩትን ሁሉ በዚያን ጊዜ ሊቀበሉት ከችሎታቸው በላይ መሆኑን ሲገለጽላቸው ወልድ የሰወረው ይህን ቃል ነው። የተወሰነው ጊዜ በተፈጸመና ሰዓቱም በደረሰ ጊዜ ግን ቃል ከእግዚአብሔር ፈቃድ አድማስ አበራ። ተጠንቀቁ የወልድ ሠራዊት ሆይ! (ክርስቲያኖችን ሲል ነው) ወደኋላ ገሸሽ አታድርጉት፤ ተቀበሉት እንጂ። በፊታችሁ ከምታዩት ሁሉ ይህ ለእናንተ በጣም የበለጠ ነው! ... በእርግጥ እርሱ የእውነት መንፈስ ወደ እውነት ሁሉ ሊመራችሁ መጥቷል። በእውነቱ እርሱ ከእራሱ አይናገርም፤ ሁሉን ከሚያውቀው ከጠቢቡ ከእግዚአብሔር እንጂ፤ ወልድ ያከበረው እርሱ ነው። ... የዓለም ሰዎች ሆይ! ከፊት ለፊታችሁ ያለውን ነገር ተዉ፤ በእርሱ በታማኙ፥ በኃያሉ የታዘዛችሁትንም ተቀበሉ።”
እ.ኤ.አ. በ1867 ዓ.ም. ከአድሪያኖፕል ለሮማው ጳጳስ በጻፈው መልእክት እንዲህ ይላል፦
“ተጠንቀቅ የክብር ስሜት ከተከበረው፥ ስግደትም ከሚሰገድለት እንዳያግድህ! ኃያሉን፥ ሁሉን አዋቂውን ጌታ ተመልከት! ለዓለም ፈውስ ለመስጠትና በውስጧ የሚኖሩትንም ሁሉ አንድ ለማድረግ መጥቷል። እናንት ሕዝቦች ሆይ! ወደ መልእክቱ ጎህ ሥፍራ ኑ! ለአንዲት ሰዓት እንኳን አትዘግዩ! ወንጌልን የተማራችሁ ሁናችሁ የጌታን ክብር ማየት ተሳናችሁን?
“ይህ የሚገባችሁ አይመስልም፤ እናንት ምሁራን ሆይ! እንግዲያውስ ይህን ነገር ካልተቀበላችሁ በምን መረጃ እግዚአብሔርን አመናችሁ? መረጃችሁን አቅርቡ...”
ለክርስቲያኖች የወንጌልን ተስፋ መፈጸም በዚህ ዓይነት ጽሑፎች እንዳስታወቀ ሁሉ ለእስላሞች፥ ለአይሁዶች፥ ለዞራስቲሪያኖችና ለሌሎች ሃይማኖት ተከታዮች የየቅዱሳት መጻሕፍቶቻቸው ተስፋ መፈጸሙን አውጇል። የሰው ልጆች ሁሉ በልዩ ልዩ ክፍሎች እንደተከፋፈሉና በልዩ ልዩ ከለላዎች እንደተጠለሉ መንጋዎች የእግዚአብሔር በጎች ይቆጥራቸዋል። የእርሱም መልእክት ጊዜው በደረሰ ሰዓት “አንድ መንጋና አንድ እረኛ ይኖር ዘንድ” ማናቸውንም እንቅፋት አስወግዶ የተበታተኑ በጎችን አንድ መንጋ ይሆኑ ዘንድ የእግዚአብሔር የመልካሙ እረኛ ድምጽ ነው ይላል።
Interesting blog? Like it on Facebook, +1 on Google, Tweet it or share this article on other bookmarking websites.