ሥጋ ለበስ ሕይወት የኑሮአችን የመጀመሪያው ደረጃ ሲሆን ፥ የነፍስ ከሥጋ መለየት ደግሞ የተሟላና ነፃ የሆነ ኑሮ የሚጀመርበት አዲስ መወለድን ይመስላል ሲል ባሃኦላህ ያስተምረናል።
እንዲህም ሲል ጽፎአል፦
“ነፍስ ከሥጋ ከተለየች በኋላ ፈጣሪዋ ዘንድ እስክትደርስ ድረስ የዘመናትና የምዕተ ዓመታት መለዋወጥ፥ እንዲሁም የዚህ ዓለም ለውጥና አጋጣሚ ሁሉ በማይለውጠው አኳኋን እድገትዋን የምትቀጥል መሆኗን በእውነቱ እወቅ። የእግዚአብሔር መንግሥት ሉዓላዊነቱ፥ ገዥነቱና ሥልጣኑ እስከአለ ድረስ ትኖራለች። የአምላክን ምልክቶችና ባሕርያቱን ትገልጻለች፥ ፍቅር የተመላበት ደግነቱንና ቸርነቱንም ታሳያለች። የዚህን የተከበረ ደረጃ ከፍተኛነትና ጸጋውን በሚገባ ለመግለጽ በሚሞክርበት ጊዜ የብዕሬ እንቅስቃሴ ይቆማል። የመሐሪው እጅ ለነፍስ የሚያጎናጽፋትን ክብር ምንም አንደበት በሚገባ ለመግለጽ እንዲሁም ምንም ምድራዊ ወኪል ሊተነትነው አይችልም። ከሥጋ በምትለይበት ሰዓት ከዓለም ሕዝቦች ከንቱ አስተሳሰብ ነፃ ሆና የተገኘች ነፍስ የተባረከች ናት። እንዲህ ያለች ነፍስ የምትኖረውና የምትንቀሳቀሰው በፈጣሪዋ ፈቃድ ስለሆነ፥ ወደ ፍጹም ከፍተኛው ገነት ትገባለች። የእጅግ በጣም ታላቁ ቤት ነዋሪዎች የሆኑት የመንግሥተ ሰማይ ድንግሎች ያጅቧታል፤ የእግዚአብሔር ነቢያትና የእርሱ ምርጦች ጓደኝነቷን ይሻሉ። ያች ነፍስ ከነርሱ ጋር በሙሉ ነፃነት ታወጋለች፥የዓለማት ሁሉ ጌታ በሆነው በእግዚአብሔር መንገድ እንድትችለው የተደረገችውን ሁሉ ታጫውታቸዋለች። በምድርና በሰማይ ዙፋን ንጉሥ በአምላክ ዓለማት፥ ይህችን ለመሰለች ነፍስ የተዘጋጀላት ነገር ለማንም ሰው ቢነገረው፥ ይህንን እጅግ በጣም የተከበረ ፥ ይህን የተቀደሰና የተዋበ ደረጃ ለማግኘት በጣም ከመመኘቱ የተነሳ መላ ሰውነቱ ከመቅጽበት በተቀጣጠለ ነበር... ከሞት በኋላ የነፍስ ሁኔታ ምን እንደሆነ ሊገለጽ ፍጹም አይቻልም፤ ሁኔታውን በሙሉ ለሰዎች ዓይኖች መግለጹ ተገቢም፥ የሚፈቀድም አይደለም። ነቢያትና የእግዚአብሔር መልእክተኞች ወደዚህ ዓለም የተላኩት ፥ የሰውን ዘር ወደ ቀጥተኛው የዕውነት ጎዳና ለመምራት ዓላማ ብቻ ነው። የግልጸታቸውም ዋና ዓላማ የሰው ልጆች በንጽሕናና በቅድስና፥ ከከንቱ ፍላጎትም በመገለል ኖረው፥ በሞት በሚለዩበት ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ከፍተኛ ዙፋን ለመቅረብ እንዲችሉ ለማስተማር ነው። ዓለም እንድታድግና ሕዝቦቿም እንዲበለጽጉ የሚያደርገው፥ እነዚህ ነፍሶች የሚያፈልቁት ብርሃን ነው። እነርሱ ለፍጥረተ ዓለም ሕይወትን እንደሚሰጡ እርሾዎች፥ እንዲሁም የዓለም ኪነ-ጥበብ ድንቅ ነገሮች የሚገለጹባቸው ኃይልና ሕይወት ሰጭ ኃይሎች ናቸው። በእነርሱ አማካይነት ደመናዎች በረከታቸውን ያዘንባሉ። ምድርም ፍሬዋን ትሰጣለች። ሁሉም ነገር ምክንያት፥ አንቀሳቃሽ ኃይልና ሕይወት የሚሰጥ አንቀሳቃሽ መሠረታዊ ሕግ እንዲኖረው ያስፈልጋል። እነዚህ የመላቀቅ ምልክቶች የሆኑት ነፍሶች በፍጥረተ ዓለም ውስጥ የመጨረሻ ከፍተኛ አንቀሳቃሽ ኃይል የሰጡና መስጠታቸውንም የሚቀጥሉ ናቸው። ይህ ዓለም ገና በእናቱ ማሕጸን ካለው የሕፃን ዓለም እንደሚለየው ሁሉ፥ የወዲያኛው ዓለም ከዚህኛው ዓለም የተለየ ነው።” (ከባሃኦላህ ጽሑፎች ቅስማት ገጽ 126-128 ቁጥር 81)
አብዱል-ባሃም ተመሳሳይ መልስ ጽፎአል፦
“ሰው በምድራዊ ዓለም ስውር የሆነበት በሰማያዊው ዓለም ይገለጽለታል። የእውነትንም ምስጢር የማወቅን ዕድል ያገኛል። አብረውት ይኖሩ የነብሩትን ሰዎች በበለጠ ያውቃል። አእምሮ የተሰጣቸው፥ አስተዋይ ዓይን ያገኙ ቅዱሳን ነፍሶች በብርሃን መንግሥት ሁሉንም ምስጢር ያውቃሉ። የታላላቅ ነፍሶችንም ጸጋ ለማወቅ ይሻሉ። በዚያም ዓለም የእግዚአብሔን ውበት በግልጽ ያያሉ። እንደዚሁም ደግሞ ጥንትም ሆነ በቅርብ ጊዜ የኖሩትን የእግዚአብሔርን ወዳጆች በመንግሥተ ሰማያዊ ሸንጎ ላይ ያገኙዋቸዋል።
“በሰው ልጆች መካከል ያለው ልዩነትና ደረጃ ከዚህ ዓለም ሲለዩ በግልጽ ይታወቃል። የእግዚአብሔር መንግሥት በጊዜና በቦታ የማይወሰን በመሆኑ ይህ ልዩነት በቦታ ሳይሆን በነፍስና በህሊና ደረጃ የሚለይ ነው። የእግዚአብሔር መንግሥት ሌላ ዓለምና ሁለንተን ዓለም በመሆኑ ከጊዜና ቦታ የነጻ ነው። በመለኮታዊው ዓለም በመንፈሳዊ ፍቅር የተሳሰሩት እርስ በርሳቸው ከመተዋወቅም በላይ በበለጠ መቀራረብን እንደሚሹ በእርግጠኝነት እወቅ። ይህም መንፈሳዊ አንድነት ነው። እንደዚሁም በዚህ ቁሳዊ ዓለም ያሳለፍነው ኑሮም ሆነ የወደድነው ሰው ቢኖር በዚያኛው መንግሥት ከቶ አይረሳም።” (ታብሌት ኦፍ አብዱል-ባሃ ቮል.1 ገጽ 204)
Interesting blog? Like it on Facebook, +1 on Google, Tweet it or share this article on other bookmarking websites.