እግዚአብሔር አንድ ነው የሚለውን ትምህርት መሠረት በማድረግ፥ የባሃኢ ሃይማኖት ሠይጣናዊ አዎንታዊ አሳሳች (positive evil) መንፈስ ሊኖር እንደማይችል ያስተምራል። ወሰን አልባ የሆነ አንድ ኃይል ብቻ ነው። በፍጥረት ዓለማት ልዩ ከዚህ ሌላ ወይንም ይህን የሚቃወም ኃይል ቢኖር ያ ኃይል ወሰን አልባ ነው ሊባል አይቻልም። ጨለማ የብርሃን መታጣት ወይንም መደብዘዝ እንደመሆኑ መጠን፥ ክፋትም የደግነት መታጣት ወይንም ማነስ ነው ይህም የደግነት ባሕርይ አልዳበረም ማለት ነው። መጥፎ ሰው የሚባለው ከተፈጥሮ ባሕርይው ጠቃሚ ክፍሎችን ያላዳበረ ማለት ነው። ራሱን ወዳድ ሰው እንኳን ቢሆን ጥፋቱ እራሱን ከመውደዱ አይደለም። የማናቸውም ፍቅር የራስ መውደ እንኳ ቢሆን ጥሩና መለኮታዊ ነው። ክፋቱ፥ ደካማው፥ በቂ ያልሆነና የተሳሳተ ራስ መውደድ የሞላበት፥ ለሌሎችና ለእግዚአብሔር ፍቅር የሌለው መሆኑ ነው። ራሱን እንደ አንድ ከፍተኛ እንስሳ ብቻ አድርጎ በመቁጠር፥ ለማዳ ውሻን እንደሚንከባከብ ሁሉ፥ የራሱን ዝቅተኛ ባሕርይ ከውሻው ሁኔታ አብልጦ ያታልላል።
አብዱል-ባሃ ከመልእክቶቹ በአንዱ እንዲህ ይላል፦
“አብዱል-ባሃ ፥ መጥፎ መንፈስ የለም ብሏል ስለአላችሁት፥እርግጥ ነው፥ እንዲህ ያለ ነገር የለም። መጥፎ መንፈስ ማለት የሰዎች ከመልካም ጎዳና መውጣትና ከእውነትም መራቅ ነው። ስህተት የመመሪያ ማጣት፥ ጨለማ የብርሃን አለመኖር፥ ድንቁርና የዕውቀት መታጣት፥ ውሸት የእውነት መጥፋት፥ መታወር አለማየት፥ ደንቆሮነትም ያለመስማት ነው። ስለዚህ ስህተት እውርነት፥ ደንቆሮነትና መሃይምነት የሌሉ ነገሮች ናቸው።”
እንደገናም እንዲህ ይላል፦
“በፍጥረት ክፉ ነገር የለም፤ ሁሉም መልካም ነው። በአንዳንድ ሰዎች ውስጥ በተፈጥሮ የሚገኙናአስወቃሽ የሚመስሉ አንዳንድ ባሕርያት በእውነቱ ግን አስወቃሽ አይደሉም። ለምሳሌ በአንድ ገና በእንክብካቤ ሥር በሚገኝ ሕጻን ልጅ ላይ ከሕይወቱ መጀመሪያ ጀምሮ የፍላጎት ስሜት፥ የቁጡነትና የግልፍተኝነት ጠባዮች ልታዩበት ትችላላችሁ። ከዚህም በመነሳት፥ መልካምነትና ክፋት በሰው እውነታ ውስጥ ሲፈጠር ጀምሮ አብሮት የተፈጠረ ነው፥ ይህም ከተፈጥሮና ከፍጥረት ሙሉ በሙሉ መልካምነት መሠረተ ሃሳብ ጋር ይቃረናል እንል ይሆናል። ለዚህ መልሱ፥ አንድን ነገር ጭማሪ መጠየቅ የሆነው ፍላጎት፥ በተገቢ መንገድ ጥቅም ላይ እስከዋለ ድረስ የሚመሰገን ባሕርይ የመሆኑ ሐቅ ነው። ለምሳሌ፥ አንድ ሰው ሳይንስንና ዕውቀትን ለመገብየት፥ ወይም ሩኅሩኅ፥ ለጋስና ትክክለኛ ለመሆን ፍላጎት ቢኖረው በከፍተኛ ደረጃ የሚመሰገን ጠባይ ነው። ቁጣውንና ንዴቱን ፥ እንደጨካኝ የዱር አራዊቶች በሆኑት ደም በጠማቸው ግፈኞች ሰዎች ላይ ቢጠቀምባቸው በጣም አስመስጋኝ ጠባ ነው፤ ነገር ግን እነዚህን ባሕርያት በትክክለኛው መንገድ ካልተጠቀመባቸው አስወቃሾች ናቸው። የሕይወት መሠረት በሆኑት በሌሎችም የሰው ተፈጥሮአዊ ባሕርያት ሁሉ እንዲሁ ነው፤ ከሕግ ውጪ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ ከዋሉና ቢተገበርባቸው አስወቃሾች ይሆናሉ። ስለዚህ ፍጥረት በመሠረቱ መልካም መሆኑ ግልጽ ነው።” (መልስ የተሰጣቸው ጥያቄዎች ቁጥር 57 ገጽ 215-216 አንቀጽ 12 እና 13
እርኩስ መንፈስ ሁልጊዜ ያልተስተካካለ ኑሮ ነው። አነስተኛው ባህርያችን ሲያመዝን ተመዛዛኝ ኑሮን ለማግኘት ማድረግ ያለብን ደግ የመሥራትን ጠባይ ማዳበር ነው እንጂ ከአናስተኛው ባህርያችን መቀነስ አይደለም። ክርስቶስ “ሕይወትን በበለጠ ታገኙ ዘንድ መጥቼአለሁ” ብሏል። ይህም ሁላችንም የምንፈልገው ነገር ነው። ሕይወት፥ የበለጠ ሕይወት፥ ኑሮ ሊባል የሚቻለውን ነው የምንሻው! የባሃኦላህ መልእክት ከክርስቶስ መልእክት ጋር ተመሳሳይ ነው። “ዛሬ ይህ አገልጋይ በእርግጥ ለዓለም ሕይወትን ሊሰጥ መጥቷል።” ይላል። (ታብሌት ቱ ራኢስ) ለተከታዮቹም ‘ኑ ለዓለም ሕይወት ሰጭዎች እናደርጋችሁ ዘንድ’ ይላል። (ታብሌት ቱ ዘ ፖፕ)
Interesting blog? Like it on Facebook, +1 on Google, Tweet it or share this article on other bookmarking websites.