“እናንት የአንድ ዛፍ ፍሬዎች፥ የአንድ ቅርንጫፍ ቅጠሎች የአንድ አትክልት ሥፍራ አበቦች ናችሁ።” ይህ ከባሃኦላህ መሠረታዊ ትምህርቶች አንዱ ነው።
አንዱ ሌላው ደግሞ እንዲህ ይላል፦
“ክብር የእርሱ የእራሱን አገር የሚወድ አይደለም። ክብር የእርሱ መሰል ወንድሙን የሚወድ ነው እንጂ።”
አንድነት፥ የሰው ልጆች አንድነት በእግዚአብሔር የተፈጠሩ ነገሮች ሁሉ አንድነት የትምህርቱ ዋና መልእክት ነው። እዚህም ላይ የእውነተኛ ሃይማኖትና ሳይንስ መጣጣም ግልጽ ነው። ሳይንስ እያደገ ሲሄድ የሁለንተን ዓለም አንድነትና የልዩ ልዩ ክፍሎችም ተደጋጋፊነት በበለጠ ግልጽ እየሆነ ሄዷል።
የከዋክብት ጥናት አዋቂው መስክ ከፊዚክስ ጥናቱ ሊቅ ክልል በማይለያይ ሁኔታ የተሳሰረ ነው፥ የፊዚክስ ሊቁም መስክ ከቅመማው ጥናት ሊቅ፤ የቅመማው ጥናትም ሊቅ ከባዮሎጂ ጥናት ሊቅ፥ የባዮሎጂውም ሊቅ ከነፍስ ጥናት ምርምሩ ሊቅ የእርሱም እንዲሁ ከሌሎች ጋር የተያያዘ ነው። ማንኛውም በአንዱ ጥናት መስክ የተገኘ አዲስ ጥበብ ሌላውን ለማጥናት አዲስ ብርሃን ይሰጣል። የቁስ አካላዊ ሳይንስ ምንም ያህል ረቂቅ ወይንም ሩቅ ቢሆን በሁለንተን ዓለም ውስጥ የሚገኝ የአንድ ነገር አካል በሌሎች አካሎች ላይ የስበት ወይንም የተጽእኖ ኃይል እንዳለው ለማሳየት እንደቻለ ሁሉ በሁለንተን ዓለም ውስጥ አንድ ነፍስ በሌላው ላይ ኃይልና ተጽዕኖ እንዳለው በማግኘት ላይ ነው።
ልል ክሮፓትኪን “ሚውቹዋል ኤይድ” በተባለው መጽሐፉ በታናናሽ ፍጥረቶች መካከል እንኳን ሕይወት ይገኝ ዘንድ የጋራ መረዳዳት እንደሚያስፈልግ በግልጽ ያሳያል፤ በሰው ዘር ዘንድ ደግሞ ለሥልጣኔ ዕድገት ከእርስ በርስ ጥላቻ ይልቅ የጋራ መረዳዳት እንደሚያስፈልግ እንረዳለን። “እያንዳንዱ ለሁሉ፥ ሁሉም ለእያንዳንዱ” በሚል ዓላማ ነው አንድ ሕብረተሰብ ሊበለጽግ የሚችለው።
የአንድነት ዘመን
በጊዜው የሚታዩት ምልክቶች ሁሉ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ወደ አዲስ ዘመን ጎህ ሽግግር ላይ እንዳለን ያሳያሉ። እስካሁን ድረስ፥ የሰው ዘር ወጣቱ ንስር፥ በእራስ ወዳድነትና በዓለማዊ ፍላጎት ቋጥኝ ላይ ጎጆውን ሠርቶ ኖሯል። ክንፎቹን እንዲጠቀምባቸው ያደረገው ሙከራ ፍርሃት የተሞላበትና ጊዜአዊ ነበር። እስካሁን ያልደረሰበትን ነገር አለ አንዳች እረፍት ለማግኘት ሲናፍቅ ቆይቷል። በጥንቱ እምነትና አስተሳሰብ ግዞት ውስጥ በመተሻሸት ተወስኖ ቆይቷል። አሁን ወደ ከፍተኛው መንፈሳዊ ፍቅርና የእውነት መንግሥት ሊመጥቅ ይችላል። ክንፎቹ ሳያድጉ በፊት እንደነበረው ሁሉ በመሬት ተወስኖ አይቀርም። እንዳሻው ሰፊ የሃሳብ ዕይታና ታላቅ ነፃነት ወዳለበት ሥፍራ ሊበር ይችላል። ሆኖም በረራው እርግጠኛና የማያቋርጥ ይሆን ዘንድ አንድ የሚያስፈልግ ነገር አለ። ይኸውም ክንፎቹ የሚያስፈልጋቸው ብርታት ብቻ ሳይሆን ሚዛናዊና አንድነት ባለው ሁኔታ መብረር ጭምር ነው።
አብዱል-ባሃ እንዲህ ይላል፦
“በአንድ ክንፍ ብቻ ሊበር አይችልም። በሃይማኖት ክንፍ ብቻ ለመብረር ቢፈልግ በከንቱ እምነት አዘቅት ውስጥ ያርፋል፤ በሳይንስ ክንፍ ብቻ ለመብረር ቢሞክር ደግሞ ከዓለማዊ ፍላጎት አሰቃቂ ማጥ ውስጥ ይወድቃል።” (ዊዝደም ኦፍ አብዱል-ባሃ ገጽ 132
ለሰው ልጅ ከፍተኛ ሕይወት የሳይንስንና የሃይማኖትን አንድነት ማወቅ ግዴታው ነው። ይህ ሲሆንና እያንዳንዱም ሕፃን ሳይንስና ኪነ ጥበብን ብቻ ሳይሆን የሰውን ልጅ ማፍቀርንና በዘገምተኛ ለውጥ (በኤቮሉሽን) በነቢያት ትምህርት የሚገለጹትን የእግዚአብሔርን ፈቃድ በደስታ መቀበልን ሲማር፥ የዚያን ጊዜ የእግዚአብሔር መንግሥት ትመጣለች፥ ፈቃዱም በሰማይ እንደሆነች እንዲሁም በምድር ትሆናለች። ይህ ሲሆን ብቻ እጅግ ታላቁ ሰላም በረከት ለዓለም ይሰጣል። ካልሆነ ግን አይሰጥም።
“ሃይማኖት ከከንቱ እምነትና፥ ከከንቱ አስተሳሰብ ተላቆ ከሳይንስ ጋር አንድነትን ሲያሳይ ጦርነትን፥ አለመግባባትን፥ጭቅጭቅንና ትግልን ከፊቱ የሚያጠፋ አንድ አስማሚ ታላቅ ኃይል ይፈጥራል። የዚያን ጊዜ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ፍቅር ኃይል አንድ ይሆናል።” (ዊዝደን ኦፍ አብዱል-ባሃ ገጽ 135)
Interesting blog? Like it on Facebook, +1 on Google, Tweet it or share this article on other bookmarking websites.